የሶሪያ ጦርነት፡ በአሜሪካ የሚደገፈው ጦር ራቃን ተቆጣጠርኩ አለ

በሶሪያ የሚገኘው በአሜሪካ የሚደገፈው ጦር የአይ ኤስ መቀመጫ የነበረችውን ራቃን መቆጣጠሩንና አሁን የቀሩት ጥቂት ታጣቂዎች ብቻ መሆናቸውን ገልጿል።

የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች አይ ኤስ የሞት ቅጣትን በይፋ ሲያስፈጽምበት የነበረውን የአል-ናይም አደባባይም ተቆጣጥረናል ብለዋል።

ድላቸውም በቅርብ ሰዓታት በይፋ እስኪታወጅ እየተጠባበቁ ነው።

ከ3000 በላይ የሚሆኑ ንጹኃንም ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከአይ ኤስ ነጻ ሆነዋል።

ራቃ አይ ኤስ ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ ከተቆጣጣራቸው ትልልቅ ከተሞች አንዷ ነበረች።

አሁን ግን በከተማዋ ሆስፒታልና ስታዲየም ወደ ሃምሳ የሚጠጉ ታጣቂዎች ብቻ መቅረታቸው እየተነገረ ነው።

ወደ ራቃ የመግባት እድል የገጠመው የበቢሲ ጋዜጠኛም በወራት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለአየር ድብደባ፣ ያለቦምምብ ፍንዳታና ያለተኩስ እሩምታ እንዳገኛት ዘግቧል።

ይልቁንስ የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች በፈራራሱት መንገዶች እየተመላለሱ ነዋሪዎቹ በነጻነት ወጥተው ትኩስ ሾርባ እንዲጠጡ በድምጽ ማጉያ እየጋበዙ ነበር ብሏል።