መርሳት ጥቅም አለው? ሰዎች ዕድሜያቸው ሲገፋ የሚረሱትስ ለምንድን ነው?

ፍፁም ያልሆነ የማስታወስ ችሎት እና የተጣረሰ ትዝት የጤናማ አእምሮ መገለጫዎች ናቸው ይላሉ ኒውሮሳይንቲስቱ ቻራን ራንጋናት በቅርቡ ባሰተሙት መፅሐፍ። እንዴት?

“የማስታወስ ችሎት” ማለት ይላሉ ኒውሮሳይንቲስቱ “ኋይ ዊ ሪመምበር” ብለው ባሳተሙት መፅሐፋቸው፤ “የማስታወስ ችሎታ ያለፈውን ትውስታ አጠራቅሞ ከመያዝ ያለፈ ትልቅ ነገር ነው። ራሳችንን እና ዓለምን የምናይበት መንገድ መገለጫም” ነው።

ራንጋናት በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ትምህርት ፕሮፌሰር ናቸው። ላለፉት 30 ዓመት የሰውን ልጅ አእምሮ የማስታወስ እና የመርሳት ችሎታን ሲመረምሩ ቆይተዋል።

እሳቸው እንደሚሉት ስለማስታወስ ችሎት ያለው የጋራ ግንዛቤ የተዛባ ነው። እንዲያውም አአምሯችን የሚፈጥረው ስህተት በጣም ጠቃሚ እና ለመኖራችን አስፈላጊ ነው ይላሉ።

ይህ የምሑሩ ግኝት ፍፁም ያልሆነውን አእምሯችንን ለተሻለ ነገር እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን የሚለውን ሳይንስ የሚተነትን ነው።

ትውስታ የሚፈጠረው በአእምሯችን ውስጥ ያሉ ኒውሮኖች እየጠነከሩ ሲመጡ በሚፈጠረው ለውጥ ምክንያት ነው። ነገር ግን ይህ ትስስር ሁሌም ጠቃሚ ነው ማለት አይደለም። አንዳንድ ለውጦች ጠንካራ እና ውጤታማ ሊሆኑ ይችላሉ።

በስህተት የተሞላ የመማር ችሎታ ማለት አንድን ነገር ለማስታወስ ስንሞክር አእምሯችን የሚያመጣልን ትውስታ ፍፁም ያልሆነ ነው ማለት ነው።

ሳይንሱ እንደሚለው አእምሯችን ለማስታወስ ሲሞክር ከእውነተኛው መረጃ ጋር ለማነፃፀር እየሞከረ ነው። ይህ ግንኙነት ጠንካራ ያልሆኑ ገመዶችን ሲያዳክም ደኅና የሚባሉትን ደግሞ ያጠናክራል።

ይህ ማለት አንድን ነገር ለማስታወስ የበለጠ በሞከርን ቁጥር ደካማ የሚባሉትን ግንኙነቶች ያጋልጣል፤ በዚህ ጊዜ አእምሯችን ለማስታወስ ያለውን ኃይል ያጠናክራል።

ለዚህ ነው ጠንካራ የሚባሉ የማስታወስ ችሎታዎች፤ ለምሳሌ ጉግል ማፕ ተመልክቶ ከመንዳት ይልቅ መንገድ አስታውሶ ለመንዳት መሞከር አሊያም ፅሑፍ ደጋግሞ ከማንበብ ይልቅ ለማታወስ መመኮር ውጤታማ ያደርጋሉ የሚባለው።

አብዛኛዎቻችን አንድ ነገር ለማስታወስ ሞክረን ስንቸገር እንረበሻለን፤ ነገር ግን ምሑሩ መርሳት አንዳንዴ ሊጠቅም ይችላል ይላሉ። እንዴት?

ይህን ጥያቄ በምሳሌ የሚመልሱት ኒውሮሳይንቲስቱ “ቤትህ መጥቼ እንዴት የሚያስፈልጉህን ነገሮች ከምረህ አታስቀምጥም? ብዬ ብጠይቅህ ማለት ነው ይላሉ። መርሳት ባንችል ኖሮ ሁሉንም ነገር ከምረን እናስቀምጣለን ማለት ነው። ይህ ደግሞ የምንፈልገውን ነገር በአስፈላጊው ጊዜ ለማግኘት እንዲከብደን ያደርጋል።

“አሁኔ እኔ ሆቴል ነው ያለሁት” ይላሉ ራንጋናት። “ከዛሬ ሁለት ሳምንት በኋላ የሆቴል ክፍሌን ቁጥር ማስታወሴ ምንም ጥቅም የለውም። መንገድ ላይ የማያቸውን ሰዎች ሁሉ ለማስታወስ መሞከር እንደማለት ነው። የአልፎ ሂያጁን ፊቱ ሁሉ ማስታወስ ይጠበቅብኛል?” በማለት የመርሳት ወይም ነገሮችን የመተውን ጠቀሜታ ያነሳሉ።

ሰዎች ሲያረጁ የሚረሱት ለምንድን ነው?

እያረጀን ስንመጣ የማስታወስ ችሎታችን ይሟጠጣል ማለት አይደለም። በምትኩ ማስታወስ የሚገባንን ነገር ብቻ እናስታውሳለን ማለት እንጂ።

ዕድሜያችን እየገፋ ሲመጣ ብዙም አስፈላጊ ያልሆኑ የምንላቸውን ነገሮች እየረሳን ነገር ግን ጠቃሚ ናቸው ብለን የምናስባቸውና ግድ የምንሰጣቸው ነገሮች ላይ ብቻ እናተኩራልን።

ለዚህ ነው አንድ ነገር ለማስታወስ ስንሞክር አእምሯችን መረጃ ለማግኘት የሚቸገረው።

ራንጋናት የተሻለ የማስታወስ ችሎታ እንዲኖረን ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን ማሟላት አለብን ይላሉ። አንደኛው ለይቶ ማስቀመጥ ነው። ትውስታዎቻችን እርስ በርስ ይፎካከራሉ። ስለዚህ አንዳንድ ትውስታዎችን ለይቶ እንዲወጡ ማድረግ ሊጠቅም ይችላል።

ግልጥ ብለው የሚታዩ ከዕይታ፣ ከድምፅ እና ከስሜት ጋር የሚገናኙ ትውስታዎች አእምሯችን ውስጥ ለረዥም ጊዜ የመቆየት አቅም አላቸው። ስለዚህ ስሜታዊ የሚባሉ ዝርዝሮች ላይ ማተኮር የማስታወስ ችሎታችንን ያግዘዋል።

ሁለተኛው መላ ትውስታችንን የበለጠ ስሜት እንዲሰጡ አድርጎ አሰናድቶ ማስቀመጥ ነው። ይህ የሚያስረዱት ፀሐፊው “ሚሞሪ ፕሌስ” የተባለውን መንገድ ይጠቁማሉ። መመዝገብ የምንፈልገውን መረጃ ከመዘገብነው መረጃ ጋር ማዋሃድ ማለት ነው ይላሉ።

ሦስተኛው መላ መግቢያ ማሰናዳት ነው። አንድን ነገር ለማስታወስ መሞከር ብዙ ጥረት የሚጠይቅ እና ለስህተት ተጋላጭ የሆነ ድርጊት ነው። እንደው ስንፈልግ ቢመነጩልን ደስ ይለናል። ለዚህ ነው መግቢያ የሚያስፈልገን።

ለምሳሌ ሙዚቃ ምን ያህል ጠንካራ ትዝታ ቀስቃሽ እንደሆነ እናውቃለን። አንድን ጊዜ ለማስታወስ ሙዚቃ የሚረዳንን ያክል ለሌችም አጋዥ መሣሪያዎች አሉ።

ለምሳሌ ቆሻሻ በሚጣልበት ቀን ቆሻሻ አውጥቼ መጣል እንዳለብኝ ለማስታወስ ከፈለግኩ ወደ በሩ ስጓዝ አስባለሁ፤ ቀጥሎ የቆሻሻ ማጠራቀሚያውን እመለከታለሁ።

አእምሯችን ሐሰተኛ መረጃ የሚሰጠን ለምንድነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡት ምሑሩ አእምሯችን አንዳንድ ጊዜ ክፍተት ሲፈጠርበት በተሳሳቱ መረጃዎች ይሞላዋል ይላሉ።

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ትውስታዎች በጊዜ ሂደት እየተለወጡ መምጣታቸው ነው። ይህ በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ትውስታችንን በጊዜ ሂደት እያሳደግነው መምጣት ስላለብን ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

ለምሳሌ አንድ ወዳጃችንን ከብዙ ጊዜ በኋላ ካየነው እና ገፅታው ተቀይሮ ካገኘነው አዲስ መረጃ አእምሯችን ውስጥ ይመሠረታል ማለት ነው።

ትውስታችንን ለሌሎች ሰዎች ስናጋራ ከሆነው ነገር ወጣ ሊል ይችላል። እኔ የማስታውሰው እና ለሰዎች የምናገረው ነገር ሙሉ በመሉ ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል።