ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የመሬት መንቀጥቀጦች አስከፊ የሚሆኑባቸው 7 ምክንያቶች
ማክሰኞ ታኅሣሥ 29/2017 ዓ.ም. ቻይና ቲቤት ውስጥ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በርካታ ሰዎች ሞተዋል። በርዕደ መሬት መለኪያ 7.1 የተመዘገበው የመሬት ነውጥ በአውሮፓውያኑ 2019 አሜሪካ ከተከሰተው ጋር ይመሳሰላል።
በአሜሪካ ግን አንድም ሰው አልሞተም። ከሰዎች ሞት እና ንብረት ውድመት አንጻር የመሬት መንቀጥቀጥ የሚያደርሰውን ጉዳት የሚወስኑ ሁኔታዎችን እንመልከት።
1. ርዕደ መሬቱ መጠን እና የሚቆይበት ጊዜ
የመሬት መንቀጥቀጥ የሚለካው በሞመንት ማግኒትዩድ ስኬል ሲሆን፣ ይህም ሬክተር ስኬልን የተካ መለኪያ ነው።
ርዕደ መሬቱ የሚሰጠው ቁጥር በምን ያህል ኃይል ምን ያህል ርቀት እንደተጓዘ ይጠቁማል።
ከ2.5 ያነሰ ከሆነ በመለኪያ መሣሪያ እንጂ ለሰዎች ላይሰማ ይችላል።
እስከ 5 ሲደርስ ግን ሰዎችም ይሰማቸዋል፣ ጉዳትም ያደርሳል።
የቲቤት የመሬት መንቀጥቀጥ 7.1 የደረሰ ሲሆን፣ አምና በቱርክ እና ሶሪያ የተከሰተው 7.8 ተመዝግቧል።
ይህ መጠን ከስምንት ከፍ ያለ ከሆነ "አደገኛ" ይባላል። በተከሰተበት አካባቢም ውድመትን ያስከትላል።
ርዕደ መሬቱ ከጥንካሬው ባሻገር መንቀጥቀጡ የቆየበት ጊዜም ይታያል። ምክንያቱም ጉዳት የሚያደርሰው በቆየበት ጊዜ ልክ በመሆኑ ነው።
የፓስፊክ ኖርዝዌስት ሴስሚክ ኔትወርክ "አነስተኛ ርዕደ መሬት ጥቂት ሰከንድ ይወስዳል። በ2004 በሱማትራ [ኢንዶኔዢያ] የተከሰተው ዓይነት ሲሆን ደግሞ እስከ ሁለት ደቂቃ ይቆያል" ይላል።
2. የርዕደ መሬቱ ጥልቀት
አንድ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚሸፍነው ቦታ ብቻ ሳይሆን የሚነሳበት የመሬት ክፍልም ምን ያህል አደገኛ እንደሚሆን ይወስነዋል።
ሞሮኮ ውስጥ የደረሰው ርዕደ መሬት የተነሳው ከምድር 18 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ላይ ነበር።
ይህም የዓለማችን ትልቁን ተራራ ኤቨረስትን እጥፍ የሆነ ርቀት ማለት ነው። የሥነ ምድር ባለሙያዎች ግን ይህን ከፍተኛ ጥልቅት አድርገው አይወስዱትም።
የእሳተ ገሞራ አጥኚ እና የሥነ ምድር ባለሙያ ዶ/ር ካርመን ሳሎና "ይህ ርዕደ መሬት እምብዛም ጥልቅ አይደለም። ኃይሉ እና ንዝረቱ በመሬት የላይኛው ክፍል ተሸፍኗል" ትላለች።
ከሁለት ዓመት በፊት በኢንዶኔዥያ የተከሰተው የመሬት ነውጥ 6.2 የንዝረት መጠን [ማግኒትዩድ] እንዳለው ተመዝግቧል። ይህም ጥልቀቱ 168 ኪሎ ሜትር ሲሆን የሞተ ሰው ግን አልነበረም።
3. ርዕደ መሬቱ የተከሰተበት ሰዓት
የመሬት መንቀጥቀጥ የሚከሰትበት ሰዓት የሚያስከትለውን አደጋ ይወስናል።
በማዕከላዊ ሞሮኮ የተከሰተውን ርዕደ መሬት በመጥቀስ ዶ/ር ካርመን እንደምትለው፣ ሰዎች በተኙበት ሰዓት ቢነሳ የከፋ ጉዳት ይከተላል።
በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት በብዛት የሚሞቱት ሰዎች ከሕንጻ መውጣት ባለመቻል ነው።
"ሰውን የሚገድለው ርዕደ መሬት ሳይሆን፣ ሕንጻ ነው" የሚባለውም ለዚያ ነው።
ቀን ላይ ሕንጻ ውስጥ ያለው ሰው ቁጥር ሲቀንስ የሚጎዳውም ሰው ይቀንሳል።
4. የሕንጻ አሠራር
መሬት መንቀጥቀጥን መቋቋም የሚችሉ ሕንጻዎችን መገንባት ይቻላል። ሕንጻው ለንዝረት የማይበገር መሆን አለበት።
የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ እንደሚለው፣ ጃፓን ለርዕደ መሬት በመጋለጥ ቀዳሚ ናት። ሕንጻዎች የሚሠሩትም መሬት መንቀጥቀጥ ሲነሳ መቋቋም በሚችሉበት መንገድ ነው።
በቶኪዮ ዩኒቨርስቲ መሃንዲስ እና መምህር የሆኑት ጁን ሳቶ "ሕንጻው ከርዕደ መሬቱ የሚነሳውን ንዝረት የሚቋቋም ከሆነ አይወድቅም" ይላል።
ለዚህ ግንባታ የሚውል ብሎኬት ከ30-50 ሴንቲሜትር ውፍረት ይኖረዋል።
ይህ ዓይነት ግንባታ ውድ ነው። ግብዓቱን መግዛትም ወጪ ያስወጣል።
በሞሮኮ ገጠራማ አካባቢ በአብዛኛው ጉዳት የደረሰባቸው ከአፈር የተሠሩ እና የመሬን መንቀጥቀጥን መቋቋም በማይችሉ ቤቶች ናቸው።
ረዣዥም እና ብዙ ሰው የሚኖርባቸው ሕንጻዎች ተጋላጭነታቸው ሰፊ ነው።
በቱርክ ደካማ ሕንጻዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሕንጻዎቹ ሲፈራርሱ ተጎድተዋል። የሕንጻ አሠራር መመሪያን መተግበርም ከባድ መሆኑ ይገለጻል።
የቱርክ የመሬት መንቀጥቀጥ ከባድ ቢሆንም ሕንጻዎቹ በአግባቡ ቢገነቡ ኖሮ ጉዳቱ ይቀንስ ነበር።
በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ ለንደን የአደጋ ጊዜ ዕቅድ ባለሙያ ፕሮፌሰር ዴቪድ አሌክሳንደር "ርዕደ መሬቱ ከፍተኛ ቢሆንም ሕንጻዎችን አያፈራርስም ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ሕንጻዎች የወደቁት ለመሬት መንቀጥቀጥ ዝግጁ ሆነው ስላልተሠሩ ነው" ይላል።
5. የሕዝብ ብዛት
በአውሮፓውያኑ 2021 በአላስካ 8.2 ማግኒትዮድ የሚደርስ ርዕደ መሬት ተነስቶ ነበር። ይህም በአሜሪካ ታሪክ ሰባተኛው ከፍተኛ ርዕደ መሬት ቢሆንም የተጎዳም የሞትም ሰው የለም።
ይህ የሆነው የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው ሰዎች በብዛት ከሚኖሩበት አካባቢ ርቆ ስለነበር ነው።
የ2010 የሄይቲ ርዕደ መሬት 7.0 ማግኒትዩድ የነበረ ቢሆንም የደረሰው ሞት እና ጉዳት ከፍተኛ ነው። 250,00 ሰው ሲሞት፣ 300,000 ተጎድተዋል፣ 1.5 ሚሊዮን ቤት አልባ ሆነዋል።
በመዲናዋ በፖርት አው ፕሪንስ በስኩዌር ኪሎ ሜትር 27,000 ሰዎች መኖራቸው ከፍተኛ ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰበት ምክንያት ነው።
6. የአፈር ዓይነት
የመሬት ጥንካሬ የርዕደ መሬትን ጥንካሬ ይወስናል።
ውሃ ያላላው አፈር መሬት ሲንቀጠቀጥ መቋቋም አይቻለውም።
አፈራማ የሆነ አካባቢ እንደ ውሃ ሲሆን በርዕደ መሬት ጊዜ ሊኩዲፊኬሽን (liquefaction) ይፈጠራል።
በ1964 በጃፓን፣ ኒጋታ ግዛት የተከሰተውም ይህ ነው።
በቱርክ በ2023 የተከሰተው ርዕደ መሬት ከ50,000 በላይ ሰዎችን ገድሏል።
አደጋው ከደረሰበት 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ኢርዚን ከተማ ውስጥ ግን ምንም ነገር አልተፈጠረም።
የሞተም ሰው የፈረሰም ሕንጻ አልነበረም።
የሥነ ምድር ባለሙያዎች እንደሚሉት የከተማው መሬት ጠንካራ ስለሆነ ንዝረቱን መቋቋም ችሏል።
7. የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት
ድንገተኛ ተፈጥሯዊ አደጋ ሲደርስ ሕይወትን ማዳን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
በጃፓን ትምህርት ቤቶች በርዕደ መሬት ወቅት ምን ማድረግ እንደሚገባ በዓመት ሁለት ጊዜ ተማሪዎች ይለማመዳሉ።
በቤት ውስጥም ሆነ ውጪ ሳሉ አልያም መኪና ውስጥ ሆነው የመሬት መንቀጥቀጥ ቢነሳ ማድረግ ያለባቸውን ይለማመዳሉ።
በታይዋንም በተመሳሳይ ብሔራዊ የርዕደ መሬት ምላሽ ልምምድ ይደረጋል።
የመሬት መንቀጥቀጥ በብዛት በማይከሰትባቸው አገራት ግን ይሄ ልምምድ አይዘወተርም።
በምን ያህል ፍጥነት ምን ያህል የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከአደጋው ስፍራ ይደርሳሉ የሚለው ዋነኛው ነጥብ ነው።
በቱርክ ከአሥር ቀናት በኋላም ሰዎች ከሕንጻ ፍርስራሽ ሥር ሲወጡ ነበር።
የተጎዱ እና በፍርስራሽ የታፈኑ ሰዎች ያን ያህል ቀናት በሕይወት አይቆዩም።
የመሠረተ ልማት ዝርጋታ እና የመሠረተ ልማትን ለማደስ የሚወስደው ጊዜ ቁልፍ ጉዳይ ናቸው።
በሞሮኮ ገጠራማ አካባቢ በመሬት መንሸራተት መንገዶች ሲሰባበሩ ወደ መንደሮች የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች መግባት አልቻሉም ነበር።
ከርዕደ መሬት ጋር በተያያዘ የሕንጻ መፍረስ ብቻ አይደለም ሞት የሚያስከትለው።
በውሃ አቅራቢያ ባሉ ቦታዎች ላይ ማዕበል ይነሳል።
በ2004 በእስያ የተከሰተው የማዕበል ወጀብ (ሱናሙ) 9.1 ማግኒትዮድ የተመዘገበን ርዕደ መሬት ተከትሎ ነበር የተከሰተው። ይህም በብዙ የአካባቢው እና ራቅ ብለው በሚገኙ አገራት ውስጥ ወደ 230,000 ለሚደርሱ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።
በሱናሚው ምክንያት የሕንድ ውቅያኖስን ተሻግሮ ሰዎችን የገደለ ማዕበል ነበር የተከሰተው።
ከፍታማ ቦታዎች ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ የመሬት መንሸራተት ያስከትላል። ቤቶች ከመሬት በታች ይቀበራሉ።
በአውሮፓውያኑ 2015 በኔፓል ወደ 9,000 ሰዎች ሞተዋል። በአካባቢው ከ3,000 በላይ የመሬት መንሸራተቶች ተከስተዋል።
በ1996 የሳን ፍራንሲስኮ ርዕደ መሬት ከ20 እስከ 25 ሰከንድ ቆይቷል። የተነሳው ወጀብ ግን የጋዝ መተላፊያ ትቦዎችን በማፈራረስ የፈሰሰው ጋዝ እሳት እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።