ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢላን መስክ መንኩራኩር ለ9 ወራት ሕዋ ላይ የቆዩትን የጠፈር ተመራማሪዎች ለመመለስ ተላከ
ለዘጠኝ ወራት ያህል ሕዋ ላይ የቆዩትን የጠፈር ተመራማሪዎች ቡች ዊልሞር እና ሱኒ ዊልያምስ ወደ ምድር የሚመልስ የስፔስኤክስ መንኮራኩር ተላከ።
ለስምንት ቀናት ብቻ ወደ ዓለም አቀፉ የሕዋ ተቋም (አይኤስኤስ) የሄዱት የጠፈር ተመራማሪዎች ለዘጠኝ ወራት ወደ መሬት መመለስ ሳይችሉ ቆይተዋል።
የተላከው መንኮራኩር አዲስ ባለሙያዎችን የያዘ ሲሆን ለዘጠኝ ወራት የቆዩት የጠፈር ተመራማሪዎች መንኮራኩሩ ሕዋ ላይ በደረሰ በሁለተኛው ቀን ወደ ምድር ጉዞ ይጀምራሉ ተብሏል።
የናሳ የንግድ ክፍል ኃላፊ ስቲቭ ስቲች "ቡች እና ሱኒ ድንቅ ሥራ ሠርተዋል። ወደ ምድር ልንመልሳቸው ጓጉተናል" ብሏል።
የጠፈር ተመራማሪዎቹ ከሩስያ፣ ጃፓን እና አሜሪካ በተውጣጡ ሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው የሚተኩ ይሆናል።
የአይኤስኤስ የፕሮግራም ኃላፊ ዳና ዌግል ለዘጠኝ ወራት የቆዩት ተመራማሪዎች ወደ መሬት የሚያደርጉት ጉዞ እንደሚጀመር ገልጻለች።
"ዋናው የአየር ሁኔታው መስተካከሉ ነው። ምቹ ሁኔታ ካለ ጉዞው ይጀመራል" ብላለች።
የጠፈር ተመራማሪዎቹ ለዘጠኝ ወራት ሲያከናውኑት የነበረውን ሥራ አዲስ ወደ ሕዋ ለተጓዙት ባለሙያዎች ለማስረከብ ሲዘጋጁ ነበር።
የጠፈር ተመራማሪዋ ሱኒ ዊልያምስ "እዚህ ስሆን ደስታ ይሰማኛል" ስትል ቆይታዋን ገልጻለች።
በኦፕን ዩኒቨርስቲ የሚሠራው ዶ/ር ሳይመን ባርበር "ለሳምንት በሚል ወደ ሕዋ ከሄዱ በኋላ ለወራት መቆየት ቀላል አይደለም። የቤተሰብ ሕይወት ላይ ጫና አለው" ይላል።
ሁለቱ ባለሙያዎች እአአ በሰኔ 2024 ነበር ወደ ሕዋ ያቀኑት። ለምርምር ወደ ሕዋ ያቀኑት የስፔስኤክስ ተቀናቃኝ በሆነው ቦይንግ መንኮራኩር ነበር።
ቦይንግ በገጠመው የቴክኒክ ችግር ለቀናት የታቀደው ቆይታ ወደ አንድ ዓመት ገደማ ተራዝሟል።
ናሳ የጠፈር ተመራማሪዎቹ ስኬታማ በሆነ መንኮራኩር ወደ ምድር እንዲመለሱ ወስኗል።
በቦይንግ ስታርላይነር ከመመለስ ይቅር በስፔስኤክስ ተመራማሪዎቹን ለመላክ ናሳ ወስኗል።
ቦይንግ በተቀናቃኙ ተመራማሪዎቹ ወደ ምድር በመመለሳቸው ቅሬታ እንደተሰማው ገልጿል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የስፔስኤክስ ኃላፊ ኢሎን መስክ ተመራማሪዎቹ "ሕዋ ላይ ተትተዋል" ሲሉ ተችተዋል።
"ለስምንት ቀን ሄደው 300 ቀን ቆዩ" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል። መስክ ደግሞ "በፖለቲካ ምክንያት ነው እዛው የተተውት" ብሏል።
ናሳ ግን ተመራማሪዎቹ ተትተው እንዳልሆነና ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው የቴክኒክ ጉዳዮች እንደነበሩ ገልጿል።
የናሳ ባለሙያ ስቲቭ ስቲች "ብዙ አማራጮችን ተመልክተናል። ከአማራⶐቹ የተሻለውን ወስደናል" ብሏል።
በለንደን የስፔስ ሳይንስ ሙዝየም ኃላፊ ዶ/ር ሊቢ ጃክሰን ከናሳ ባለሙያ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ አላት።
"የቡች እና ሱኒ ደኅንነት ነው ዋናው ጉዳይ። ናሳ ውሳኔውን ያሳለፈው በአሳማኝ የቴክኒክ ምክንያት ነው። በሰላም ወደ ምድር ተመልሰው እስከማያቸው ቸኩያለሁ" ብላለች።