ከአሜሪካ የመባረር አደጋ ላይ ያሉ ስደተኞችን የምትረዳው ቀይዋ ካርድ

"ቀይ ካርዷን ሁሌም መያዜ የበለጠ ደኅንነት እንዲሰማኝ ያደርጋል።"

ከፊሊፒንስ የመጣችው እና ሰነድ አልባዋ ቬሮኒካ ቬላስኬዝ አነስ ያለችውን ቀይ ካርድ ከቦርሳዋ አትነጥላትም።

አንዳንዶች "መብታችሁን እወቁ" ሲሉ ይጠሯታል ካርዷን።

እንደ ቬሮኒካ ያሉ ሰነድ አልባዎች በአሜሪካ ውስጥ ሲኖሩ መብቶቻቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ የሚያደርጉ መረጃዎችን እጭቅ አደርጋ የያዘች ናት።

በተለይም አይስ እየተባለ የሚጠራው የአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ወኪሎች ጋር ሲያገኟቸው ምን ማድረግ እንደሚችሉ መመሪያዎችን ይዛለች።

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ነበር ካርዷ በስደተኞች የሕግ መገልገያ ማዕከል (አይኤአርሲ) በተሰኘው ተቋም የታተመችው።

በአሁኑ ወቅት በ19 ቋንቋዎች ተተርጉማለች።

በአገሪቱ ያሉ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ጠራርጌ አስወጣለሁ ሲሉ ቃል የገቡት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የካርዷ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

"ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከተደረገበት ከጥቅምት 26 ጀምሮ ዘጠኝ ሚሊዮን ካርዶች አቅርቡልን ጥያቄዎች ደርሰውናል። ይህም አሃዝ ካለፉት 17 ዓመታት በድምሩ የሚበልጥ ነው" ብሏል አይኤልአርሲ።

መብቶች እና መመሪያዎች

በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ማናቸውም ሰዎች የስደት ሁኔታቸውም ምንም ይሁን ምን በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ውስጥ የተረጋገጡ መብቶች አሏቸው።

በአሜሪካ ውስጥ የመባረር አደጋ ላይ ያሉ ስደተኞች የኢሚግሬሽን ወኪሎች በመኖሪያ ቤታቸው ቢመጡ ሊያደርጉ የሚገባቸውን ተግባራት ከምሳሌዎች ጋር ቀይ ካርዶቹ ይዘዋል።

ለምሳሌ ያህል ስደተኞቹ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን መብታቸውን በመጠቀም ከኢሚግሬሽን ወኪሎች ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ አለመስጠት ወይም ዝምታን መምረጥ ይችላሉ። ይህም ግለሰቦች ራሳቸውን እንዲወነጅሉ ከመገደድ የሚጠብቃቸው ነው።

እንዲሁም በዳኛ የተፈረመ የፍተሻ (የእስር) ማዘዣ የማይዙ የኢሚግሬሽን ወኪሎችን ስደተኞቹ ወደ ቤታቸው እንዳይገቡ ካርዷ ትመክራለች። ይህም በሕገ መንግሥቱ ላይ የመንግሥት አካላት ምክንያታዊ ያልሆነ ፍተሻ እና ቁጥጥር እንዳያደርጉ ለመከላከል የሚያዘውን ዋቢ በማድረግ ነው።

ቀይዋ ካርድ መነሻ ቀለሟን የወሰደችው በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ጥፋት የሚፈጽሙ ተጫዎቾችን ከሜዳ ለማስወጣት ዳኞች የሚጠቀሙባትን ቀይ ካርድን ነው።

መቀመጫውን ካሊፎርኒያ ያደረገው አይኤልአርሲ የዚህችን ካርድ ሃሳብ ያመነጨው የኢሚግሬሽን ወኪሎች ሕገወጥ ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል በበርካታ ስፍራዎች ላይ "ማኅበረሰቡን ያሸበሩ" ወረራዎችን በአውሮፓውያኑ 2007 መፈጸማቸውን ተከትሎ ነው።

ተቋሙ ካርዶቹን ለትርፍ ላልተቋሙ ድርጅቶች እና የንግድ ተቋማት በትምህርት ቤቶች፣ በአብያተ ክርስቲያናት፣ በክሊኒኮች፣ ወይም በምግብ ባንኮች እንዲሁም ከስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጋር ለሚሰሩ ጠበቆች በማደል እንዲሰራጩ ያደርጋል።

በተጨማሪም ማንኛውም ሰው ከተቋሙ ድረ ገጽ አውርዶ ማተም ይችላል።

ካርዷ በአንደኛዋ ጎን በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሌላኛው በኩል ደግሞ በተጠቃሚዎቹ የአፍ መፍቻ ቋንቋ መረጃን ይዛለች። ስፓኒሽ፣ ፖርቹጊዝ፣ አረብኛ፣ ክሪዎል፣ ሩስኪ፣ ዩክሬን፣ ቬትናም እንዲሁም የቻይናን ቋንቋ ጨምሮ ሌሎችንም ይዛለች።

በአሜሪካ 11 ሚሊዮን ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች እንዳሉ ፒው የተሰኘው የምርምር ማዕከል በአውሮፓውያኑ 2022 ያወጣው መረጃ ያሳያል።

ይህም አሃዝ በአሜሪካ ውስጥ ካሉ ስደተኞች 23 በመቶ እንዲሁም ከጠቅላላው ሕዝብ 3.3 በመቶውን የሚሸፍን ነው።

ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉት ከሜክሲኮ፣ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከኤል ሳልቫዶር፣ ከሆንዱራስ እና ከጓቲማላ የመጡ ናቸው።

በተጨማሪም ከእስያ አገራት ከሕንድ 725 ሺህ እና ከቻይና 375 ሺህ የመጡ ሰነድ አልባ ስደተኞች ይኖራሉ። ከአፍሪካ የመጡ ደግሞ 375 ሺህ ሰነድ አልባዎች አሉ።

ለአብዛኞቹ ለእነዚህ ሰነድ አልባ ስደተኞች በቀይ ካርድዋ ላይ የተዘረዘሩትን መብቶች አስረግጦ ማስከበር በአገር ውስጥ መቆየት ወይም መባረርን ያህል ልዩነት እንደሚያስከትል ተሟጋቾች ይናገራሉ።

"ቀላል መሳሪያ ናት ነገር ግን ከፍተኛ ተጽእኖ ልታሳድር የምትችል" የሚሉት በካሊፎርኒያ የሚገኘው ኮስትላይን ዩኒቨርስቲ ድሪም ፕሮጀክት የተሰኘው ማዕከል ባልደረባ ዳሊያ ዘቲና ናቸው።

"ይህችን ካርድ የያዘ ሰው ከቤት ሲወጣ ወይም ወደ ሥራ ሲሄድ የበለጠ ደኅንነት እንዲሰማው ትረዳለች" የሚሉት ዳሊያ "አንድ ወኪል ቢያገኛችሁ ልትደናገጡ ትችላላችሁ። በዚህ ወቅት ካርዷን አውጥቶ ማንበብ ወይም በቀጥታ ለወኪሉ መስጠት ይችላሉ" ብለዋል።

እሳቸው የሚሰሩበት ማዕከል እስካሁን 700 ካርዶችን ማደል ችሏል።

የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣናት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና በጎ ፈቃደኞች ሰነድ አልባ ስደተኞች የኢሚግሬሽን ወኪሎችን "ትዕዛዝ እንዳይቀበሉ" እየረዷቸው ነው ሲሉ ይነቅፋሉ።

"መብታችሁን እወቁ ሲሉ ካርዷን ይጠሯታል። እኔ ደግሞ 'ከመታሰር እንዴት ማምለጥ ይቻላል' እለዋለሁ" ሲሉ ስደተኞችን የማባረር ዋነኛ ኃላፊነት የተሰጣቸውን እና የትራምፕ "የድንበር ጥበቃ ዋነኛ ኃላፊ" የሚባሉት ቶም ሆማን ተናግረዋል።

"ወንጀለኛ ስደተኞችን ከማባረር የሚያግደን ምንም ነገር የለም" ሲሉም ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

ስደተኞችን እንደሚያባርሩ እየማሉ የመጡት ትራምፕ ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ሕጋዊ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ለመያዝ በሚል በመኖሪያ ቤቶች እና በሥራ ቦታዎች የሚደረጉ ወረራዎች ተባብሰዋል።

አዲሱ አስተዳደር የሚያደርጋቸውን ተግባራትም ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ይጠቀማል።

ዋይት ሐውስ፣ የሀገር ውስጥ ደኅነት ቢሮ እና አይስ በየቀኑ በቁጥጥር ስር የሚውሉ ስደተኞችን ምሥሎችን ያትማሉ። አንዳንዶቹም እግራቸው እና እጃቸው በካቴና ታስሮ በአውሮፕላን ሊሳፈሩ ሲገደዱ የሚያሳዩ ናቸው።

የአሜሪካ መንግሥት እነዚህ እርምጃዎች እየተወሰዱ ያሉት ለአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት እንደሆነ እና "ወንጀለኞችን ወደ አገራቸው እየመለስን ነው" ይላል።

ሆኖም በቁጥጥር ስር ከዋሉት ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ምንም ዓይነት የወንጀል ሬከርድ እንደሌላቸው ኤንቢሲ የዜና ወኪል ያገኘው መረጃ ያሳያል።

በየካቲት ወር የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በኢሚግሬሽን ወኪሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉት 4 ሺህ 422 ስደተኞች መካከል 1800 (41 በመቶ) ምንም ዓይነት የወንጀል ክስ የሌላቸው ወይም ያልተመሠረተባቸው መሆኑን የዜና ወኪሉ አረጋግጧል።