ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"...ይጨክናሉ ብዬ አላሰብኩም ነበር" ሁሉን ነገር ጨርሶ ከነቤተሰቡ ወደ አሜሪካ የመሄድ ዕድሉ የጨነገፈበት ኢትዮጵያዊ
ብርሃነ በ2021 በትግራይ ኃይሎች እና በፌዴራል መንግሥታት መካከል የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ነው ሀገር ጥሎ የተሰደደው።
ብርሃነ እና ቤተሰቦቹ አዲስ አበባ ላይ ታዋቂ ምግብ ቤት ነበራቸው። በሌሎች የንግድ መስኮችም ተሰማርተው ይሠሩ ነበር።
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች በርካታ የትግራይ ተወላጆች በፀጥታ ኃይሎች ሲታሰሩ እሱም ከአንድም ሁለት ጊዜ ለእስር መዳረጉን ይናገራል።
"በማንነታችን ምክንያት ለእስር ተዳረግን። ብዙ ገንዘብ ከፍለን ነው ከእስር የተለቀቅነው። ምግብ ቤታችንም ተዘጋ። ነገሮችን ሲደራረቡኝ ያለኝን ነገር ሁሉ ሸጬ ሚስቴ እና ልጆቼን ይዤ ለመውጣት ወሰንኩ" ይላል።
ብርሃነ ከሚስቱ እና ከልጆቹ ጋር ወደ ጎረቤት ሀገር ኬንያ መዲና ናይሮቢ መጥቶ ኑሮን እንደ አዲስ ጀመረ።
ናይሮቢ ከመጣ በኋላም እስር እና እንግልት አልቀረለትም። ሕጋዊ ወረቀት ስላልነበረው በነፃነት መንቀሳቀስ አልቻለም።
"ፖሊስ መንገድ ላይ ያስቆመንና ወረቀት ይጠይቀናል። ሕጋዊ ዶኩመንት አልነበረንም። በቁጥጥር ሥር ከዋልንበት ለመውጣት ለፖሊስ ገንዘብ መክፈል ነበረብን። ልጆቼም ተቸግረው ነበር።"
እርጉዝ ሳለች ወደ ናይሮቢ የመጣችው ሚስቱ ደግሞ ልጅ በሰላም ተገላገለች።
በመከራ ያልተረታው ብርሃነ ያለውን ጥሪት ሰባስቦ ከባለቤቱ ጋር በመሆን ምግብ ቤት ከፈተ።
"የ40 ቀን ጨቅላ ይዘን ነው ሥራ የጀመርነው። ልጆቼ የሰው እጅ እያዩ እንዲያድጉ ስለማልፈልግ ነው ሚስቴ ሳትጠነክር ሥራ ለመጀመር የወሰንነው። ሚስቴ ጀግና ናት። እንዴት እንደምገልፃት ቃላት ያጥረኛል።"
ምግብ ቤቱ ደንበኞች ማፍራት ጀመረ። ሥራቸውም ጥሩ መንገድ ያዘላቸው።
በ2023 የባይደን እና ካማላ ሐሪስ አስተዳደር "ዌልካም ኮር" የተባለ አሜሪካውያን ዜጎች ስደተኞችን ስፖንሰር አድርገው ወደ አሜሪካ መውሰድ የሚችሉበት ፕሮግራም ይፋ አደረገ።
እነዚህ ስፖንሰር የሚደረጉ ሰዎች በተባበሩት መንግሥት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ስደተኛ መባል አይጠበቅባቸውም።
በፕሮግራሙ መሠረት ስፖንሰር የሚያደርጉ አሜሪካውያን ዜጎች ስደተኞችን ብቻ ሳይሆን መስፈርት የሚያሟሉ ሰዎችን መውሰድ ይችላሉ።
ይህ ፕሮግራም ጥር 2023 ይፋ ሲደረግ ብርሃነ እና ቤተሰቦቹ ስፖንሰር የሚያደርጋቸው አሜሪካ የሚኖር ዘመድ አገኙ። ከአንድ ዓመት በኋላ ተሳክቶላቸው ፈቃድ ተሰጣቸው።
"ያለንን ሁሉ ሸጠን ባዶ ቀረን"
አስፈላጊውን ሒደት በሙሉ ተከትለው ስኬታማ ስለነበሩ ባለፈው ሳምንት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መግባት የሚያስችላቸው ወረቀት መጣ።
ከናይሮቢ ቦስተን የሚደርሱበትን ሰዓት ያውቁታል። መቼ ተነስተው መቼ እንደሚደርሱ የሚጠቁመው ቲኬት ደርሷቸዋል።
"ሁሉም ነገር ስላለቀልን ዶኩመንታችንን ለመንግሥት አስረክበን ያለንን ዕቃ ሁሉ ሸጥን። ወደ ስፖንሰራችን እንግዶቹ ለመቀበል "ዝግጁ ናችሁ?" የሚል ኢሜል ደረሳቸው። እዚያ ሊቀበሉን ተዘጋጅተው ነበር" ይላል ብርሃነ።
አሜሪካ የሚሄዱበት ቀን በሚቀጥለው ሳምንት ጥር 27/2017 ዓ.ም. ነበር።
ልጆቻቸው ከተማሪ ጓደኞቻቸው ሽኝት ተደረገላቸው። ምክንያቱም በችግራቸው ጊዜ አቅፋ ደግፋ ያስተናገደቻቸውን ናይሮቢ ሊሰናበቱ ነውና።
ነገር ግን አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን መጥተው ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዝ አስተላለፉ። ትዕዛዙ ማንኛውም ወደ አሜሪካ የሚመጡ ስደተኞችን የሚመለከት ነው።
በዚህ ምክንያት ብርሃነ እና ቤተሰቡ ኑሯቸውን ለመለወጥ እና አዲስ ሕይወት ለመጀመር ወደ አሜሪካ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ ባላሰቡት መንገድ ተጨናገፈ።
ብዙ ያሳለፈው ብርሃነ "ያለንን ነገር ሁሉን ሸጠን ባዶ እጃችንን ቀረን" ይላል።
"ጉዟችን ተቋረጠ። ልጆቼ ትምህርት አቋርጠዋል። ምን እንደምናደርግ አላውቅም።"
ትራምፕ ሥልጣን በጨበጡ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ነው በርካታ ፕሬዝደንታዊ ትዕዛዞች ያስተላለፉት። በተለይ ደግሞ ወደ አሜሪካ የሚመጡ ስደተኞችን በሚመለከት ጠንከር ያለ መመሪያ አውጥተዋል።
ይህን መመሪያ ተከትሎ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ አሜሪካ ለመምጣት ፈቃድ ያገኙ ስደተኞችን እና 'ኢንተርቪው' ለመስጠት ቀጠሮ ያላቸውን ስደተኞችን ሒደት ሰርዟል።
በባይደን ዘመን መንግሥት ተግባራዊ መደረግ የጀመረው በስፖንሰር ወደ አሜሪካ የመግባት ሒደትም ተቋርጧል። ይህ በተለይ ጦርነትን ሸሽተው አሜሪካ መጠለል ለሚፈልጉ ጥሩ አማራጭ ነበር።
ትራምፕ ቃለ መሐላ ፈፅመው ዋይት ሐውስ ሲገቡ "ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ የሚመጡ ስደተኞች ጉዳይ ለአሜሪካውያን የሚጠቅም አይደለም" ብለው ነበር።
በአሁኑ ወቅት ወደ አሜሪካ ለማቅናት ሕልም የነበራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሕልማቸው የጨለመ ይመስላል።
አብዛኛዎቹ የሚጠበቅባቸውን መስፈርት አሟልተው፣ ፈቃድ ተሰጥቷቸው የመሄጃ ቀናቸውን እየተጠባበቁ ነበር።
የአሜሪካ የስደተኞች ጉዳይ ባለሥልጣናት እንደሚሉት "ወደ አሜሪካ የሚመጡ ስደተኞች ጉዳይ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጧል።"
ብርሃነ እንደሚለው ይህ የትራምፕ ውሳኔ ልጆቹ እና ቤተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እና ድንጋጤ ፈጥሯል።
"በቃላት መግለፅ ይከብደኛል። እናቴን ካየኋት ቆይቻለሁ። ቤተሰቦቼን ካየሁ ዓመታት ተቆጥረዋል። ብዙ መከራ አሳልፈናል። ልጆቼ ብሩህ ተስፋ ነበራቸው። መልካም ሕይወት መምራት ይችሉ ነበር። ከመከራ የራቀ ኑሮ መኖር ነው ሕልማችን።"
በዌልካም ኮር ፕሮግራም መሠረት አምስት ሰዎች ተሰባስበው 2275 ዶላር በማዋጣት ወደ አሜሪካ ለሚመጣው ቤተሰብ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ወራት ኪራይ እና መሠረታዊ ፍላጎት የሚያሟላ ሁኔታን ይፈጥራሉ።
ስፖንሰር የሚያደርጉት ሰዎች አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው እና ቋሚ የነዋሪነት ፈቃድ ያላቸው መሆን ይችላሉ።
በስፖንሰር የሚመጡ ሰዎች ልክ እንደ ስደተኞች የኋላ ታሪካቸው ይጠናል፤ የተጠየቁትን መረጃ ማቅረብም ይኖርባቸዋል።
ብርሃነና ቤተሰቡ ለአንድ ዓመት ያክል ይህን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
"የአሜሪካ ምርጫ ቀን ልጄ ኢንተርቪው የሚደረግበት ቀን ነበር። ትራምፕም ሆኑ አሜሪካውያን እዚህ ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ ብዬ ጠብቄ አላውቅም ነበር" ይላል።
"ብቻዬን ብሆን ችግር አልነበረውም። እወጣው ነበር። ነገር ግን ስድስት ነን - ማን ማንን ያጽናናል። ልጆቼ መማር አይችሉም፤ ምክንያቱም ዶኩመንታቸውን አስረክበዋል። ምን እንደማደርግ አላውቅም።"