የጊዜያዊ አስተዳሩን ሥልጣን የመንጠቅ ሙከራ ሊኖር እንደሚችል አቶ ጌታቸው ተናገሩ

የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በድርጅቱ ሊቀመንበር የሚመራው ቡድን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ለመንጠቅ ሙከራ ሊያደርግ እንደሚችል ገለጹ።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያልተሰጠው እና እየተካሄደ ያለው የህወሓት ጉባኤ ክልሉን ወደ አልተፈለገ ችግር ሊያስገባ የሚችል ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፣ የጉባኤው መሪዎች የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣንን ለመንጠቅ ሊያሴሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ካለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. ጀምሮ በመቀለ ውስጥ እየተካሄደ ባለው የህወሓት 14ኛ ጉባኤ ከአመራርነት መነሳታቸው የተገለጸው አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስብሰባውን የሚያካሂዱት አመራሮች የተለያዩ እርምጃዎችን ሊወስዱ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

አቶ ጌታቸው እንዳሉት “ከጀርባችን ደጀን ይሆነናል፣ ይደግፈናል በሚሉት ባልታወቀ የውጭ ኃይል ተማምነው” አራት የድርጅቱ አመራሮች እንዲካሄድ የወሰኑት ጉባኤ “ወደ አልተፈለገ ችግር ሊመራን ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

አቶ ጌታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠታቸው ከሰዓታት በፊት ጉባኤ ላይ የሚገኙት የህወሓት አመራሮች ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጠቅላላ ጉባኤ ራሳቸውን ያገለሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከኃላፊነታቸው እንዳነሳ አሳውቋል።

ይህ በህወሓት ውስጥ ክፍፍልን የፈጠረው የጠቅላላ ጉባኤ ከአቶ ጌታቸው በተጨማሪ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች በዚህ ጉባኤ እንደማይሳተፉ ታውቋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በሰጡት ጋዜጣዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እየተካሄደ ያለው ጉባኤ ህወሓትን ሕገ ደንብ እና ሌሎች የአገሪቱ ሕጐች ያላከበረ እንዲሁም የትግራይ ክልል ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው በማለት ተችተዋል።

በተወሰኑ የድርጀቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው ያሉት ጉባኤው “ትግራይ ከባድ አደጋ ውስጥ እንድትወድቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ከፍተኛ አመራሮችን ወደ ሥልጣን ለመመለስ እየተንቀሳቀሱ ነው” ሲሉም ከሰዋል።

የምርጫ ቦርድ ጉባኤው ከመካሄዱ በፊት ለህወሓት በጻፈው ደብዳቤ ሂደቱ ትክክለኛውን መንገድ የተከተለ አይደለም ያለ ሲሆን፣ አቶ ጌታቸውም ጉባኤው የሁሉም የህወሓት አባላት አይደለም በማለት “ፌደራል መንግሥት ስላለ ብቻ ሳይሆን፣ የፓርቲውን ሕጐችን ስለሚጥስ ነው” ብለዋል።

በመቀለ መካሄድ ከጀመረ አምስት ቀናት ያለፉት ጉባኤ “እንደማይሠራ እና ምንም ውጤት እንደማያመጣ ስለምናውቅ” ምንም እንኳን ሕግን የተከተለ ባይሆንም ያልተፈለገ ግጭት እንዳይፈጠር በሚል እንዳይካሄድ እንዳልከለከሉ ገልጸዋል።

ጉባኤውን እያካሄዱ ያሉት የህወሓት አመራሮች ከጀርባቸው የተማመኑበት ኃይል እንዳለ እና በእርሳቸው እየተመራ ያለውን “ጊዜያዊ አስተዳደር ሥልጣንን ለመንጠቅ የተለያዩ ሴራዎችን እንደሚያደርጉ እንጠብቃለን” ሲሉም ተናግረዋል።

ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ጦርነት ባበቃው የፕሪቶሪያ ስምምነት አማካኝነት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ ይሁንታ እና ድጋፍ ያለው ነው።

አቶ ጌታቸው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በተደጋጋሚ እንዳመለከቱት በደብረጽዮን (ዶ/ር) የሚመራው ቡድን ጊዜያዊ አስተዳደሩን የሚገዳደር ከሆነ ፍጥጫው ሌላ ገጽታ መያዙ አይቀርም። ይህም የፌደራል መንግሥቱን ወደ ውዝግቡ የሚያስገባው ሊሆን ይችላል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ የትግራይ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ከየትኛውም ወገን ጎን ሳይቆሙ ገለልተኛ አቋም የያዙ ሆነው የሚታዩ ሲሆን፣ ይህ ኃይል ከአንደኛው ወገን ጋር የሚቆም ከሆነ ግን በህወሓት ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ በማወሳሰብ ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚወስደው ይሆናል።

በዚም ሳብያ አቶ ጌታቸው በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የትግራይ ፀጥታ ኃይሎች “ሥልጣን ፈላጊዎች” ያሏቸው ተቀናቃኞቻቸው መሳሪያ እንዳይሆኑ አሳስበዋል።