በኮቪድ 19 ለረጅም ጊዜ የተያዙ ሰዎች ሳምባና ኩላሊታቸው ሊጎዳ እንደሚችል ጥናት አመላከተ

የኮሮና ቫይረስ ለረጅም ጊዜ ጠንቶባቸው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች በወሳኝ የሰውነት ክፍላቸው ላይ ጉዳት ሊኖር እንደሚችል አዲስ ጥናት አመላከተ።

በኮቪድ ለረጅም ጊዜ ተይዘው የነበሩ ሰዎች ሳምባ፣ አእምሮና ኩላሊት ከሌሎች ሰዎች በሶስት እጥፍ ከፍ ችግር እንደገጠማቸው የኤም አር አይ ምርመራ ፍንጭ ሰጥቷል።

ተመራማሪዎቹ ይህ ጉዳት በኮቪድ 19 በተያዙበት ወቅት በሽታው ምን ያህል የከፋ ነው ከሚለው ጋር የሚገናኝ ነው።

ይህ ጥናት በዩኬ እየተደረገ ያለውን በኮሮና ቫይረስ ለረጅም ጊዜ የተያዙ ሰዎች እየተዘጋጀ ያለውን ህክምና ውጤታማ ለማድረግ እንደሚረዳ ታምኖበታል።

ጥናቱ በኮቪድ 19 ተይዘው ሆስፒታል የገቡ 259 ሰዎችን ተሳታፊ አድርጓል።

ታካሚዎች ከ 5 ወራት የሆስፒታል ቆይታ በተደረገላቸው የኤም አር አይ ምርመራ ወሳኝ የውስጥ ሰውነት ክፍላቸው ፈጽሞ በኮቪድ ካልተያዙ 52 ሰዎች ጋር ሲነጻጸር ልዩነት አሳይቷል።

ጉዳቱ ይበልጥ ጎልቶ የታየው ሳምባ ላይ ሲሆን የኤም አር አይ ምርመራው ከሌሎች ሰዎች በ14 እጥፍ ከፍ ያለ የተለየ ሁኔታን አመላክቷል።

ምርመራው በኮሮና ቫይረስ ለረጅም ጊዜ የተያዙ ሰዎች አእምሮው ላይ ሶስት እጥፍ ኩላሊት ላይ ደግሞ ሁለት እጥፍ ከሌሎች የተለየ የጤንነት ሁኔታን አሳይቷል።

ሆኖም በልብና ጉበት ላይ የጎላ ልዩነት እንደሌለ ጥናቱ አይቷል።

ይህንን ጥናት በመሪነት ከሚያካሂዱት መካከል አንዷና የኦክስፎርድ ባልደረባ ዶክተር ቤቲ ራማን ለረጅም ጊዜ ኮሮና ቫይረስ የጠናባቸው ሰዎች ከሌሎች ከፍ ያለ የሰውነት ክፍል ጉዳት ሊገጥማቸው እንደሚችል ግልጽ ነው ብለዋል።

ይህ ምርምር በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች የሚደርስባቸውን የረጅም ጊዜ የጤና ተጽዕኖንን ለማወቅ የሚደረግ ሰፊ የጥናት አካል ነው።

ተመራማሪዎቹ ምርመራ ወቅት የሰውነት አካል ጉዳት ምልክቶች ለረጅም ጊዜ በኮሮና በተያዙ ሰዎች ላይ መታየቱን ገልጸዋል።

ሆኖም ሁሉም ምልክቶች በኮሮና ቫይረስ ለረጅም ጊዜ በመያዝ ብቻ የሚመጣ ላይሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።