ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትሬቨር ኖዋ ከዴይሊ ሾው አዘጋጅነቱ ሊለቅ ነው
ደቡብ አፍሪካዊው 'ኮሜዲያን' ትሬቨር ኖዋ ከተወዳጁ የዴይሊ ሾው የቴሌቪዥን ፕሮግራም አሰናጅነቱ ሊለቅ መሆኑን አስታወቀ።
ትሬቨር እስካሁን ለመጣበት የስኬት ጉዞው አመስግኖ ሌላ መከተል የሚፈልገው የሕይወቱ ክፍል እንዳለም ተናግሯል።
የ38 አመቱ ትሬቨር በቀልድና የተዋዙ ፖለቲካዊ አስተያየቶችንና ማኅበራዊ ትችቶችን የሚያቀርበውን ዴይሊ ሾው የተሰኘውን የአሜሪካ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ከጆን ስቱዋርት በአሰናጅነት የተረከበው በአውሮፓውያኑ 2015 ነው።
የሚለቅበት ጊዜ ይፋ እንደሚሆንና እስከዚያው ድረስ ግን የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን በአዘጋጅነት እንደሚቀጥል ተናግሯል።
ትሬቨር የሙያ ሕይወቱ የተጀመረው በትውልድ አገሩ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሲሆን የተለያዩ ኮሜዲ ሥራዎችን በመድረክ ላይ በማቅረብ እንዲሁም ቶክ ሾው በማዘጋጀት ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2011ም ኑሮውን በአሜሪካ አድርጓል።
በኮሜዲ ሴንትራል ኔትወርክ የሚተላለፈውን ዴይሊ ሾው በአሰናጅነት እንዲረከብ ሲመረጥ በምዕራባውያኑ ዘንድ ብዙም ያልታወቀ ነበር።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግን በሚያቀርባቸው ስራዎች ዓለም ዓቀፍ እውቅናዎችን የተጎናጸፈ ሲሆን በርካታ ሽልማቶችንም አግኝቷል።
ትሬቨር የመልቀቁን ዜና ያስታወቀው ትናንት ሐሙስ ምሽት ባቀረበው ዝግጅት የመጨረሻ ሰዓት ላይ ሲሆን በስቱዲዮው ታዳሚዎች ዘንድም ድንጋጤን ፈጥሯል።
ለባለፉት “አስደናቂ ሰባት ዓመታት” የዝግጅቱን ቡድን አባላት እና ታማኝ አድናቂዎቹን አመስግኖ “አስገራሚ ነበር፤ በእውነቱ ገራሚ ነው” ብሏል።
“መጀመሪያ ስንጀምር አስታውሳለሁ፤ በርካቶች አላመኑብንም ነበር። እኔን እንደ አዘጋጅነት ማምጣት ትልቅ እብደት ፣ ቁማር ተደርጎም ነበር የታየው። አንድ ዝም ብሎ አፍሪካዊ”
“ላለፍኩበት ጉዞ ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ።በጣም የሚያስደንቅ ነው። ይህ ፈጽሞ ያልጠበቅኩት ነገር ነው።" ብሏል ትሬቨር።
የዶናልድ ትራምፕን የፕሬዚዳንትነት እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ በርካታ ክስተቶች የተስተናገዱበት ወቅት እንዳሳለፈ ገልጾ፣ አሁን ለመልቀቅ ጊዜው እንደሆነ ተናግሯል።
“ይህንን ዝግጅት እወደዋለሁ። በሕይወቴ ከገጠሙኝ ዋነኛ ፈተናዎቼ እንዲሁም ደስታዎቼ አንዱ ነው። ከሰባት ዓመታት ቆይታ በኋላ ጊዜው እንደሆነ ይሰማኛል” ብሏል።
“በሕይወቴ ውስጥ ለማየት የምፈልጋቸው ሌሎች ነገሮች እንዳሉ ተረድቻለሁ። ሌሎች ቋንቋዎችን መማር ናፈቀኝ፣ ወደ ሌላ አገር ሄጄ ዝግጅቶችን ማሳየት። ወደ ሁሉም ስፍራዎች መሄድ እና ሁሉንም ማድረግ ይናፍቀኛል” ሲል ፍላጎቱን ገልጿል።
“በዚህኛው የዓለማችን ክፍል ማንም የማያውቀውን ኮሜዲያን በአዘጋጅነት በማምጣት ላመነብኝ ለኔትወርኩ ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብሏል።