ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሾልከው የወጡ መረጃዎች አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት ኃላፊ ላይ ትሰልል እንደነበር ጠቆሙ
የአሜሪካ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የሩስያን ፍላጎት ለማስተናገድ ፈቃደኛ ናቸው ብሎ እንደሚያምን ከፔንታጎን ሾልከው የወጡ ሚስጥራዊ ሰነዶች ይፋ አደረጉ።
እነዚህ ሚስጥራዊ ሰነዶች የአሜሪካ መንግሥት የድርጅቱን ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝን በቅርበት ሲከታተል እንደነበርም አመላካች ናቸው።
ሾልከው የወጡት ሰነዶች በዋና ጸሃፊው ጉተሬዝ እና በምክትትላቸው የነበሩ ግላዊ ውይይቶችንም አካትተዋል።
ከፔንታጎን ሾልከው የወጡ ሰነዶችን ምንጭ ለማግኘት የአሜሪካ ባለስልጣናት እየተፍጨረጨሩ ባለበትም ወቅት ነው ይኸኛው መረጃ ይፋ የሆነው።
ሰነዶቹ በዩክሬን ስላለው ጦርነት እንዲሁም ስለ በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ጉተሬዝ የሰጡትን ትክክለኛ ምልከታ ይዘዋል።
የዩክሬንን ጦርነት ተከትሎ በአለም ላይ በተከሰተው የምግብ ቀውስን ለመቅረፍ በተባበሩት መንግሥታት እና በቱርክ የተደረሰውን ከዩክሬን እህል በጥቁር ባህር የማሻገር ስምምነት ላይ ያተኮረ መረጃም ተገኝቷል።
ጉቴሬዝ ይህንን ስምምነት እንዳይፋረስና ለመጠበቅ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው የሩሲያን ጥቅም ለማስተናገድ ፈቃደኛ እንደነበሩ ይጠቁማል።
“ጉቴሬዝ ሩሲያ [ከአገሯ እንዲሁም በዩክሬን ከተቆጣጠረቻቸው ስፍራዎች] የምታደርገውን የወጪ ንግድ አቅምን ለማሻሻል ትኩረት ሰጥተዋል” ይላል ሰነዱ “ይህም ማዕቀብ የተጣለባቸው የሩሲያ ተቋማትን ወይም ግለሰቦችንም ያካተተ ነው” ብሏል።
በሰነዱ ግምገማ መሰረት ዋና ጸሃፊው በየካቲት ወር ፈጸሟቸው የተባሉ ድርጊቶች “ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ ለፈጸመቻቸው ድርጊቶች ተጠያቂነት ለማስፈን የተደረገውንም ጥረት ያኮሰመነ ነው”።
ዋና ጸሃፊው በሩሲያ ላይ የለሰለሰ አቋም አሳይተዋል የሚለው አስተያየት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣናትን አስቆጥቷል።
ሾልከው በወጡ ሰነዶች ላይ ምንም አስተያየት ከመስጠት የተቆጠቡት አንድ የተባበሩት መንግሥታት ባለለስልጣን፣ ተመድ “የዩክሬን ጦርነት በዓለም ድሃ በሆኑ ህዝቦች ላይ የሚያደርሰውን ተፅእኖ ለመቀነስ እየሰራ ነው” ብለዋል።
"ይህም ማለት የናረውን የምግብ ዋጋ ለመቀነስ የምንችለውን ማድረግ እና ማዳበሪያ በከፍተኛ ሁኔታ ለሚያስፈልጋቸው አገራት ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ ነው" ብለዋል።
ሩሲያ በማዳበሪያ እና እህል ላይ የምታደርገው ወጪ ንግድ በዓለም አቀፉ ማዕቀብ እየተጎዳ ነው ስትል ቅሬታዋን በተደጋጋሚ ያቀረበች ሲሆን ስጋቷ እልባት እስካላገኘ ድረስም ከጥቁር ባህር ስምምነት ትብብር ራሷን እንደምታገል ዝታለች።
የሩሲያ እህል እና ማዳበሪያ በአለም አቀፍ ማዕቀብ የተካተቱ ባይሆንም የሚላክባቸው የመርከብ የመድን ዋስትናን በማግኘት ረገድ እክሎች እንዳጋጠሟት አስታውቃለች።