አስራት አያሌው፡ አእዋፍን እያደነ ፎቶ የሚያነሳው ኢትዮጵያዊ

በተለይ የትዊተር አዘውታሪዎች ‘ያ ወፍ የሚቀርፀው ሰውዬ’ በሚል መጠሪያ ያውቁታል።

አስራት አያሌው ፎቶ አንሺ ነው። 42 ዓመት ሞልቶታል።

‘የነፍሱን ጥሪ’ ያገኘው በቅርቡ ነው።

ፎቶ ማንሳት ወይ የተማረው ወይ ለዓመታት የቆየበት ሙያ አይደለም። በአጋጣሚ ነው የገባበት።

ትምህርቱም፣ የቀድሞ ሥራውም ከፎቶግራፍ ጋር አይገናኙም።

በሶሲዮሎጂ ተመርቆ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሠርቷል።

እርግጥ ከልጅነቱ ጀምሮ ፎቶ ማንሳት ጊዜ ማሳለፊያው፣ መደሰቻው ነበር።

ተፈጥሮ ይወዳል። ጸጥ ወዳለ ቦታ መጓዝ ያዘወትራል። ያገኘውን ፎቶ ማንሳት ልማዱ ነው።

ከዩኒቨርስቲ ወጥቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ገቢ ሲያገኝ የገዛው ካሜራ እንደነበር ያስታውሳል።

ፎቶ ማንሳትን ሙያው እንደሚያደርገው ግን አላሰበም።

የሕይወት አቅጣጫው የተለወጠው የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ከባለቤቱ ጋር ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር ሲያቀኑ ነበር።

በባሕር ዳር ተፈጥሮ ለመማረክ ጊዜ አልወሰደበትም።

ጣና ሐይቅን፣ ዓባይ ወንዝን ፎቶ ያነሳ፣ ቪድዮ ይቀርጽ ጀመር።

ከተማዋን “ያልተዋወቀች” ሆና እንዳገኛት ይናገራል።

እናም ፎቶዎቹን ትዊተር ላይ እየለጠፈ ከተማዋን ያስተዋውቅ ጀመር።

በዚህ መሀል ነው ብዙ አይቷቸው የማያውቅ የአእዋፍ ዝርያዎችን ያስተዋለው።

“ጨርሶ አይቻቸው የማላውቅ ነበሩ” ይላል አስራት።

ስለ አእዋፉ የበለጠ ለማወቅ መረጃ ሲያስስ በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር የተዘጋጀ መጽሐፍ አገኘ።

መጽሐፉ ዕውቀት ያስጨብጣል። ግን በመጽሐፉ የተካተቱት ፎቶዎች አእዋፉ በአካል ሲታዩ ያላቸውን ገጽታ የሚወክሉ ሆነው አላገኛቸውም።

ከሩቅ የተነሱ፣ የደበዘዙ፣ የጠቆሩ ናቸው።

አስራት ተፈጥሮንም ፎቶግራፍንም እንደሚወድ ሰው የተሻሉ ፎቶዎች ለማንሳት ወሰነ።

“ሁለት ዓመትም ይፍጅ ሦስት በባሕር ዳር ዙርያ ያሉ አእዋፍን ፎቶዎች ላሰባስብ ብዬ ወሰንኩ” ይላል።

ዛሬ ስብስቡ 265 ዝርያዎች ደርሷል። አእዋፉ በባሕር ዳርና በዙሪያዋ የሚኖሩ ናቸው።

በአጋጣሚ የገባበትን ሙያ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት አጥብቆ ይዞታል።

የሙሉ ጊዜ ሥራው ባሕር ዳርና አካባቢው ያሉ አእዋፍን ፎቶ ማንሳት ነው።

በእግሩ አልያም በሳይክል እየተዘዋወረ ፎቶ ያነሳል።

የአእዋፉን ስም፣ ባህሪ፣ አኗኗርና ሌላም መረጃ የያዘ መጽሐፍ እያገባደደ እንደሆነ ይናገራል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከፈጠረው ድባቴ እፎይታ ማግኛ መንገዱም ነበር ፎቶ ማንሳት።

ኋላ ላይ ግን ደስ ወደሚለው ሙያ ጠቅልሎ መግባትና አንዳች አስተዋጽኦ ማበርከት ወደደ።

ይህ ሽግግር “ቀላል አልነበረም” ይላል አስራት።

ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራን በዚህ ዘመን እርግፍ አድርጎ መተው ቀላል ውሳኔ ሊሆን አይችልም።

“መጀመሪያ ላይ ምንም ገቢ ስለማያስገኝ አስቸጋሪ ነበር” ይላል።

ሌሎች ባለሙያዎችም በኢትዮጵያ ለአእዋፍ ፎቶ ፍላጎቱ ስለሌለ ሥራው መተዳደሪያ እንደማይሆን ያምኑ ነበር።

አሁን ግን ፎቶዎቹን በመሸጥ ገቢ ማግኘት ጀምሯል። “ትልቅ ገቢ ባይገኝም መተዳደሪያ ይሆናል” ይላል።

ጎጃም ነው ያደገው።

አባቱ የአንደኛ ደረጃ መምህር ኋላ ላይም ርዕሰ መምህር ነበሩ። በየሦስት፣ አራት ዓመቱ ቤተሰቡ የሚኖርበትን አካባቢ ይቀይር እንደነበር ያስታውሳል።

አስተዳደጉም ከአእዋፍ ጋር የተገናኘ እንደነበር ያወሳል።

አንዱ ወደ ሙያው ለመግባቱ ምክንያቱ አስተዳደጉ ሳይሆን አልቀረም።

ባሕር ዳር የውብ አእዋፍ መኖሪያ መሆኗም ሳይጠቀስ አይታለፍም።

እሱ ብቻ አይቶ ውበታቸውን ከሚያጣጥም ከብዙኃኑ ጋር መጋራትን መርጧል።

መጽሐፉ አእዋፉን “በአይን እንደማየት ያህል ከነሙሉ ውበታቸው” የሚያሳይ እንደሚሆን ያወሳል።

ፎቶዎቹን ያለ አንዳች ስስት ትዊተር ገጹ ላይ በማጋራት አስራት ይታወቃል።

ሁሉም ነገር ለገበያ በሚቀርብበት ዘመን ለምን ይሆን ፎቶዎቹን በየቀኑ በነጻ ለማጋራት የመረጠው?

“እኔ ፎቶ ስላነሳኋቸው ነው እንጂ ለሁላችንም የተሰጡ የተፈጥሮ ፀጋ ናቸው። መታየት አለባቸው። ምርጥ የምላቸውን ደብቄ በነጻ የምለቀው ሁለተኛ ሦስተኛውን ሳይሆን በጣም ቆንጆ የሆነውን መርጬ ነው የምለቀው። ሁሉም ሰው አይቷቸው ቢደሰት የኔም ደስታ ነው።”

ነጻነት እና አእዋፍ

አእዋፍን ከነጻነት፣ ከሰላም፣ ከወሰን አልባነት፣ ከሙዚቃ ጋር የሚያስተሳስሩ አሉ።

አስራት ድንበር የማይገድባቸው ፍጡሮች ይላቸዋል።

ከአላስካም ይሁን ከአንታርክቲካ በርረው በየዓመቱ አፍሪካ ይደርሳሉ። ቀዝቃዛውን ጊዜ አሳልፈው ቤታቸው ይመለሳሉ።

“የነጻነት ተምሳሌት ናቸው። እንደፈለጉ ቦታ ሳይገድባቸው ይኖራሉ” ሲል ይገልጻቸዋል።

ከአብሮነት ጋርም ያስተሳስራቸዋል።

ከዓመት ዓመት ጣና የሚኖሩ አእዋፍን ምሳሌ ያደርጋል።

አካባቢው ውሃማ፣ ረግረግ ነው።

የጣናዎቹ አእዋፍ ከአላስካ ከመጡት ጋር አብረው ተፈጥሮ የሰጣቸውን ሃብት ይጋራሉ።

‘የኔ’ ወይም ‘መጤ’ አእዋፍ ጋር አለመኖሩ ነው አስራትን የሚማርከው።

“የእኩልነት ተምሳሌቶች፣ የተፈጥሮ ድንቅ ስጦታዎች ናቸው። ከዚህ በላይ ልገልጻቸው አልችልም” ይላል።

መልካቸው፣ ባህሪያቸው ያስደንቀዋል።

“የአንድ ወፍ ቆንጆ ፎቶግራፍ ሳገኝ የሚሰማኝን ስሜት ልገልጽልሽ አልችልም” ይላል።

ሥራው ቀላል ሆኖ አይደለም። በየቀኑ ማልዶ መውጣት፣ ዘለግ ላለ ሰዓት መጠበቅ፣ መመላለስም ያስፈልጋል።

“መፈለግ ይጠይቃል። የፈለጉት ደግሞ ቶሎ አይገኝም። ተገኝቶም ቆንጆ ፎቶ ማግኘት ድካም ይጠይቃል። ትልቅ ትዕግስትም የሚጠይቅ ነው። ግን ቆንጆ ፎቶ ያንን ሁሉ ድካም የሚያስረሳ ደስታ ይሰጣል።”

ሂደቱንም ውጤቱንም ይወደዋል። ድካሙንም ሳይቀር።

ወፍ ጥበቃ

አእዋፍ ፎቶ አንሺያቸውን ቆመው የሚጠብቁ ፍጡራን አይደሉም።

ታዲያ አስራት ምን ያህል ቀናትና ሰዓታት ይጠብቃቸው ይሆን?

አንድ ወፍ ፎቶ ለማንሳት የቆየበት ረዥሙ ጊዜ ሦስት ወር ነው። ይህም የሰማይ ቀበሮ ወፍን (African fish eagle) ፎቶ ለማንሳት ነበር።

ዋናው ሥራ የት ቦታ እንደሚያዘወትሩና መቼ እንደሚመጡ ማወቅ ይሆናል።

ረግረግ፣ ሜዳ፣ ውሃ ዳር፣ ጫካ፣ ቁጥቋጦና ሌላም ሌላም ቦታ የሚመቻቸውን አእዋፍ ይለያል። የሚመርጡትን ወቅትም ያጠናል።

ይህ ሥራውን በተወሰነ መልኩ ቢያቀለውም፣ ይሄን ማወቅ ብቻ ሄዶ አእዋፉን ለማግኘት አይረዳም።

በአብዛኛው ጥሩ ፎቶ ማግኘት “የአጋጣሚና ዕድለኛ የመሆን ጉዳይ ነው” ሲል ይገልጻል።

ሳያስብና ሳያቅድ ያገኛቸው አእዋፍ፣ ብዙ አስጠብቀውት የተገኙ አእዋፍም አሉ። አንዴ ብቻ አግኝቷቸው ከነጭራሹ የጠፉበትም መኖራቸውን ያስታውሳል።

“ሁለት ዓመት ሙሉ ፈልጌያቸው እስካሁንም የሚያስደስተኝ ፎቶ ያላነሳኋቸውም አሉ።”

አንዱ እርኩም የተባለው ወፍ ነው። እርኩምን በልጅነቱ አብዝቶ ያየው ነበር። አሁን ቁጥሩ ተመናምኗል።

ከሁለት ዓመት በፊት በባሕር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ግራና ቀኝ ባለ እርሻ ውስጥ እንደ አጋጣሚ እንዳየው ያስታውሳል።

“አንድን ወፍ አንድ ቦታ ካየሽው እዛ ቦታ መልሰሽ የማየት ዕድልሽ ሰፊ ነው። ያንን ቦታ መርጠው ስለሚቀመጡ” ይላል።

ቢሆንም ግን እርኩምን ከዛ ወዲህ ወደ አካባቢው እየተመላለሰ ቢፈልግም እስካሁን አላገኘም።

አእዋፉ እንደተገኙ ፎቶ ይነሳሉ ማለት አይደለም። ቀስ ብሎ ነው መጠጋት የሚቻለው።

“ለረዥም ጊዜ ማላመድ ያስፈልጋል። አእዋፍ እንደ ሰው ለረዥም ጊዜ ባዩሽ ቁጥር ይቀርቡሻል” ይላል አስራት።

ሰውን ከሰው እንደሚለዩም ያምናል።

መጀመሪያ ቀን ሲያዩት የሸሹት አእዋፋት ከሳምንታት ወይም ከወራት በኋላ ለነሱ አደጋ እንዳልሆነ ሲገነዘቡ እንደሚለምዱ ነው የሚገልጸው።

የሚያስፈራ ወይም የሚያሰጋ ነገር እስካላዩ ድረስ ቀስ በቀስ ይላመዳሉ።

የሰማይ ቀበሮ የሚባለው ወፍ መጀመሪያ አካባቢ ከ300 ሜትር ርቀት ይሸሸው የነበረ ቢሆንም ከሦስት ወራት በኋላ እስከ 100 ሜትር መጠጋት ችሏል።

ይህንን ‘መተማመን’ በእሱና በወፉ መካከል ለመፍጠር ወደ አካባቢው ደጋግሞ ሄዷል።

ጥሩ ፎቶ ለማግኘት ተጠግቶ ማንሳት ስለነበረበት፣ ወፉን አላምዶ ለመቅረብ “በየቀኑ እሄድ ነበር ማለት ይቻላል” ሲል ነው የሚገልጸው።

የተጎዳው ተፈጥሮ

የአእዋፍ ደኅንነት ከተፈጥሮ ደኅንነት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው።

መኖሪያቸውና የምግብ ምንጫቸውም አደጋ ውስጥ ሲወድቅ ሕልውናቸውም ፈተና ይገጥመዋል።

ጣና ሐይቅን ጨምሮ ሌሎችም የተፈጥሮ ሃብቶች ተገቢው ጥበቃ ሳይደረግላቸው ሲቀር አእዋፍም እንደሚጎዱ አስራት ይናገራል።

“ኑሯቸው የተመሠረተው በአካባቢያቸው ያለው ተፈጥሮ ደኅንነት ላይ ነው” የሚለው ፎቶ አንሺው፣ ብዝኃ ሕይወት ሲጎዳ የአእዋፍ ቁጥር እንደሚመናመን ይገልጻል።

እርኩም የሚባለው ወፍ በዓመታት ውስጥ ቁጥሩ እየቀነሰ መምጣቱ አንድ ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል።

“ሜዳና እርሻ ባለበት ሁሉ እርኩም ሁለት ሁለት ሆነው ሲታዩ በልጅነቴ አስታውሳለሁ” ይላል። ዛሬ ግን ፎቶ ለማንሳት እንኳን ተፈልገው አይገኙም።

ፎቶ ካነሳቸው መካከል ከስምንት እስከ አስር የሚጠጉት የአእዋፍ ዝርያዎች በተደጋጋሚ የማይታዩ ናቸው።

‘ሴክሬተሪ በርድ’ የወፍ ዝርያ በብዛት ይታዩ ከነበሩ አሁን ግን ለዐይን ብርቅ ከሆኑ መካከል ይጠቀሳሉ።

ለዚህም የምግብ እጥረት፣ የአካባቢ መበከል፣ የከተማና እርሻ መስፋፋትና የደን መራቆት በዋናነት ይነሳሉ።

“በዚህ ከቀጠለ አሁን የምናያቸውን አእዋፍም ጨርሶ ላናያቸው እንችላለን። ወደዚህ ሙያ ስገባ ምንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍለኝም አደርገዋለሁ ብዬ እንድወስን ካደረጉኝ ምክንያቶች አንዱ ነው።”

ቢያንስ አሁን ያሉትን ባሉበት ሁኔታ ሰንዶ ለማስቀመጥ የወሰነውም ለዚህ ነው።

‘ውበት ከባህሪ የተሰጣቸው’

ከውበታቸው በተጨማሪ በባህሪያቸውም የሚወዳቸው አእዋፍ ብዙ ናቸው።

በተለይ ቀለማቸው ‘እንዴት ያለ ተፈጥሮ ነው?’ ያሰኘዋል።

‘ቫዮሌት-ፓክት ስታርሊንግ’ ልዩ ቀለማቸው እጅግ ከሚደንቁት መካከል ነው።

አየር ላይ ለደቂቃዎች አቅጣጫ ሳይቀይሩ ክንፋቸውን ብቻ እያርገበገቡ ከውሃ ውስጥ ዓሣ የሚያድነው የወፍ ዝርያ ከሚወዳቸው መካከል ይጠቀሳል።

“ችሎታቸውና ድካማቸው ያስደንቀኛል። ስምንቴ ሞክረው በዘጠነኛው ይሆናል ዓሣ የሚይዙት። ግን ቀኑን ይሞክራሉ።”

ሌላ የሚያስገርሙት ከዝርያቸው ውጭ የሆነ ወፍ ጎጆ ላይ እንቁላል የሚጥሉ አእዋፍ ናቸው።

ሌላኛው ወፍ የነሱን እንቁላል ታቅፎ፣ ከራሱ ጫጩቶች ጋር ፈልፍሎ አብልቶ ያሳድግላቸዋል።

ይህ ‘ብልጣብልጥነት’ ወይም ደግሞ ‘መተማመን’ አስራትን ያስገርመዋል።

‘ባንተ የተነሳ ወፍ ማየት ጀመርን’

ወፍ ፎቶ ማንሳት በኢትዮጵያ ብዙም የተለመደ ሥራ አይደለም። አስራትም ይህንን አውቆ ነው ወደ ሥራው የገባው።

መጀመሪያ ላይ ቤተሰቡን ማሳመን ከብዶት ነበር። ለዓመታት የተማረውንና የሠራበትን ሙያ ትቶ እምብዛም ወደማይታወቅ ዘርፍ መግባቱን ለቤተሰብ ማሳመን ቀላል አልነበረም።

አሁን ነገሮች ተቀይረዋል።

በአካልም በማኅበራዊ ሚዲያም የሚያውቃቸው ሰዎች “በርታ” ይሉታል።

“ስጀምረው ‘ሥራ ፈቶ ነው ወደዚህ የገባው?’ እንዳልባል እፈራ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ማበረታቻና ድጋፍ ነው ያገኘሁት።”

በሙያው እንዲቀጥል ካደረጉት አጋጣሚዎች አንዱ ይህ ነው።

ሥራውን እንደጀመረ አካባቢ ቤዛዊት የሚባል ሰፈር ሌቦች ሳይክሉን ይቀሙታል። ካሜራውን ለመውሰድ ሲታገሉም ካሜራው ተሰበረ።

“ይሄን ሥራ ብሠራ ደስ ይለኝ ነበር። ግን ሌላ ካሜራ የምገዛበት ገንዘብ ስለሌለኝ መቀጠል አልችልም” ብሎ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጻፈ።

ምላሹ ያልጠበቀው ነበር።

ብር እናዋጣልሀለን፣ እናስጠግንልሀለን፣ ካሜራ ገዝተን እንሰጥሀለን ወዘተ. . . ያሉት ነበሩ።

በተለይ አንድ ሰው “ለኔ ሳይሆን፣ ልጆቼ ስለ አእዋፍ እያወቁ እንዲያድጉ ስለምታደርግ ይህን ሥራ እንድታቋርጥ አልፈልግም” ማለቱን አይረሳውም።

ሌላው በዚህ ሥራ የሚያስቀጥለው በሱ ፎቶዎች ምክንያት ‘አእዋፍ ወደድን’ የሚሉት መኖራቸው ነው።

‘ወፍ ማንሳት ቁም ነገር አይደለም’ የሚል ባይጠፋም ‘ባንተ የተነሳ ወፍ ማየት ጀመርን’ የሚሉትም አሉ።

‘ባንተ ምክንያት ወፍ ለማየት ዛፍ ላይ እያንጋጠጥኩ ነው የምውለው’ መባሉን ያስታውሳል።

ፎቶ ሲያነሳ የሚያገኛቸውን ሕጻናትና አርሶ አደሮች በተለየ ይገልጻቸዋል።

ወደ አንድ አካባቢ ሳምንታት ቆይቶ ሲሄድ ‘ባለፈው ሳትመጣ እንዲህ እንዲህ ያለ ወፍ አመለጠህ’ ይሉታል።

“ሰው ትኩረት ስለማይሰጥ ነው እንጂ ትኩረት እንዲሰጥ ካደረግሽው እኛ አገርም ቢሆን ወፎችን የማድነቅ፣ የመመልከት፣ የመጠበቅ ባህሉ ያለ ይመስለኛል። አያት ቅድመ አያቶች ለወፍ ጥሬ ሲበትኑ፣ በገል ውሃ ሲያስቀምጡ ነው የኖሩት።”

የፎቶ ፍርሃት

በኢትዮጵያ የካሜራ ፍራቻም ጥላቻም አለ።

“ምክንያቱ ግን ገብቶኝ አያውቅም” ይላል ፎቶ አንሺው።

‘ፎቶ ማንሳት አይቻልም’ የሚል የክልከላ ማስታወቂያ መለጠፍ የተለመደ ነው። ብዙውን ጊዜ ታዲያ ያለ በቂ ምክንያት ነው።

የጥበቃ ሠራተኞችም ፎቶ የሚያነሳ ሰው ለማባረር ይሽቀዳደማሉ።

ካሜራ በሚከለክሉ ቦታዎች በስልክ ፎቶ ማንሳት መቻሉ የነገሩን ምክንያት አልባነት ያሳያል።

“ካሜራ የጦር መሣሪያ ያህል የሚፈራ ሕዝብ ነው። ከተማ ውስጥ ደግሞ ይብሳል። ፖሊስ ብቻ ሳይሆን አልፎ ሂያጅም ይጠይቃል። ‘ወፍ ፎቶ እያነሳሁ ነው’ ስትይው እንደ ሽፋን እየተጠቀምሽበት ነው የሚመስለው።”

ጭቅጭቁና ውጤቱ ተመጣጥኝ ስላልሆነ ከተማ ውስጥ ካሜራ አላወጣም የሚልበት ደረጃ መድረሱን ይናገራል።

ከከተማ ውጭ ግን በነጻነት ፎቶ ያነሳል።

በካሜራ ፍራቻና ጥላቻ ሰበብ ወደ 40 ደቂቃ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ያውቃል።

የወፍ ፎቶ አንሺ ‘ሰምትንም አይተንም አናውቅም’ ተብሎ ለማሳመን ሰዓታት እንደወሰደበት ያስታውሳል።

አንድ ጊዜ ደግሞ ዓባይ ወንዝ ላይ ለሚሠራ ድልድይ የሚሆን ኮንክሪት ማምረቻ ቅጥር ጊቢ በሳይክል እያለፈ ነበር።

የግቢው የሽቦ አጥር ላይ ከዚያ በፊት አይቶት የማያውቅ የወፍ ዝርያ ተመለከተ።

“. . .መቼም ‘እዚጋ ወፍ አይቼ ነው፤ ፎቶ ላንሳው?’ ብለሽ እስክትጠይቂ ወፉ እንደማይጠብቅሽ ግልጽ ነው። ስለዚህ ፎቶውን አንስቼ ኋላ ላይ አብራራለሁ ብዬ ወሰንኩ። ግን ጥበቃዎቹ በጭራሽ ሊያምኑኝ አልቻሉም። ወፍ ማንሳትን እንዴት ‘ሥራዬ’ ብለህ ትዞራለህ። ለሽፋን እየተጠቀምክበት ነው እንጂ እዚ አካባቢ ልታነሳ የፈለግከው ሌላ ነገር አለ አሉኝ።”

‘ያ ወፍ የሚቀርፀው ሰውዬ’

የዛሬ ሁለት ዓመት ፎቶ አንሺነትን በይፋ ሲጀምር ለመጀመሪያ ጊዜ ፎቶ ያነሳውን ወፍ አይረሳውም።

‘ደብል ቱዝድ ባርቤት’ ይባለል። ፍራፍሬ የተተከለበት ቦታ ያዘወትራል።

ያኔ እንደዛሬው ጥሩ ካሜራ አልነበረውም። አሁን ላይ አስራት ከሚለው ስም ጎን ለጎን ‘ያ ወፍ የሚቀርፀው ሰውዬ’ በሚለው ቅጽል ስም ይጠራል።

ስሙን የሰጡት ሕጻናት ናቸው።

ጨረጨራ ፎቶ ማንሳት ከሚያዘወትርባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው።

በተለይም ዓባይ ከጣና የሚወጣበት ደብረ ማርያም የሚባለው አካባቢ በክረምት ረግረግ፣ በበጋ ሜዳ ስለሆነ በባሕር ዳር ብዙ የአእዋፍ ዝርያ ከሚገኝባቸው ቦታዎች መካከል ይጠቀሳል።

እዚያ አካባቢ የሚኖሩ ሕጻናት አስራትን አዘውትረው ያዩታል።

አንዳንዴ ፎቶ ለማንሳት ብሎ ሲንከባለል፣ ጭቃ በጭቃ ሲሆን፣ እስከ ወገቡ ውሃ ውስጥ ሲገባም ያዩታል።

ቀስ በቀስ ምን እንደሚሠራ ገባቸው። ገና ከሩቅ ሲያዩት ‘ያ ሰውዬ መጣ መጣ’ ‘ያ ወፍ የሚቀርፀው ሰውዬ መጣ’ ይባባላሉ።

‘ያ ወፍ የሚቀርፀው ሰውዬ’ ብለው ሲጠሩት ከሰማ በኋላ ነው ስሙን የወሰደው።

ሕጻናቱ የሰጡትን መጠሪያ ትዊተር ላይ ጻፈው። አሁን በየቦታው የሚታወቅበት ስም ነው።

"ስሙን ሕጻናቱ ስለሰጡኝና ስለምወደው እጠቀምበታለሁ። በጣም እወዳቸዋለሁ፣ አከብራቸዋለሁ። ስለ ሥራዬ ከኔ እኩል ነው የሚቆረቆሩት። እኔ በሌለሁበት ያላየሁት የወፍ ዝርያ ከመጣ ‘አይ ሳትመጣ ያ ወፍ አመለጠህ’ ይሉኛል።”