የፎቶ አውደ ርዕይ የማዘጋጀት አላማ ያለው ዓይነ ሥውሩ የፎቶ ባለሙያ

መቼም ፎቶ ቤት ገብተው ወይም በሌላ አጋጣሚ ፎቶው መነሳት ፈልገው ፎቶግራፈሮች ሁኔታዎን እየተመለከቱ 'እስኪ ትንሽ ዘንበል፣ አዎ ፈገግ ፈገግ በል/በይ' እያሉ የተዋጣለት ፎቶ ለማንሳት 'ላይ ታች' ሲሉ ገጥሞት ሊሆን ይችላል።

አሊያም በእንቅስቃሴዎች መሀል ጥሩ ፎቶ ይገኝበታል ባሉት ቅጽበት የማንሻውን ቁልፍ ይጫናሉ። ታዲይሄ ሁሉ የሚሆነው ባለሙያዎቹ ነገሮችን በአይናቸው እየተከታተሉ በአዕምሯቸው ቅጽበቶቹን ሲወስኑ ነው።

የዓይነ ሥውሩ የፎቶ ባለሙያ፣ አብዱ ሰይድ ግን ከዚህ የተለየ ነው።

ፎቶ የማንሻውን ቅጽበት የሚወስነው በጆሮው ተመልክቶ ነው። አዎ በጆሮው!

በትክክል ባልታወቀ ምክንያት በልጅነቱ እይታውን ያጣው አብዱ "እሱ ነው ወይ ያነሳው?" የሚስብሉ በርካታ ፎቶዎችን አንስቷል። እንዴት?

'በጆሮው የሚያየው' ፎቶግራፈር

በአዲስ አበባ የተወለደው አብዱ፣ እይታውን በከፊል ያጣው የ2 ዓመት ልጅ እያለ ነበር። ታዲያ ከጊዜ በኋላ እይታውን ሙሉ በሙሉ አጣ። ሰበታ በሚገኘው የዓይነ ሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታተለ።

10ኛ ክፍል እስኪደርስና ሙሉ በሙሉ ዓይነ ሥውር እስኪሆን ድረስ በተለያዩ አጋጣሚዎች አይቷቸው የነበሩ ፎቶዎች አእምሮው ውስጥ መቅረቱን ይናገራል።

ትምህርቱን ቀጥሎ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ስነ ጽሑፍ ተመረቀ። በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ውስጥ ስራ ጀመረ። የተቀጠረውና አሁንም እየሰራ ያለው በሪፖርተርነት ቢሆንም አጋጣሚው ግን አብዱ ከፎቶ ካሜራ ጋር የሚገናኝበትን ዕድል ፈጠረለት።

"ሪፖርተር ስለ ነበርኩኝ ከካሜራማኖች ጋር የመውጣት ነገር ነበረኝ። ከዛ በኋላ ካሜራዎችን የመነካካት፣ ከካሜራዎቹ ጋር የመተዋወቅ" አጋጣሚን ማግኘቱን ያስታውሳል።

'ዕቃው [የፎቶው ካሜራው] ማየት ለሚችሉ ሆኖ ቢሰራም እኔ ደግሞ ለራሴ የሆነ ነገር ፈለኩለት' የሚለው አብዱ፣ የካሜራውን የተለያዩ ክፍሎች በማዳሰስና ሰዎችን በመጠየቅ ካሜራው ላይ ያሉ ቁልፎች ያላቸውን ተግባር መረዳት ጀመረ።

"ትልቁ የምጠቀምበት መሳሪያ ጆሮ ነው" ሲል የሚገልጸው አብዱ ፎቶ ሲያነሳ ለተነሺው የተለያየ ጥያቄዎችን እንደሚሰነዝር ይናገራል።

ይህም ፎቶ የሚነሳው ሰው ምላሽ ሲሰጥ ድምጹን በመከተል ለፎቶ ዝግጁ መሆኑን ለመረዳት ነው።

መጀመሪያ ቁመቱ እነዴት ነው የሚለውን ነክቼ ነው የማያው - ለማንሳት የፈለኩትን ነገር። ወይም ህንጻ ከሆነ የማነሳው ህንጻው ስንት ወለል እንዳለው ቁመቱን ስፋቱን በግምት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል እጠይቃለሁ።

በሰው ደረጃ ግን [ፎቶ የሚነሳው/የምትነሳው] ፊት ለፊት ይቆማል። አወራዋለሁ።

ስሙን እጠይቃለሁ - ትኩረቱ ወደኔ እንዲሆን ድምጹ እንዲሰማኝ ማለት ነው። እና በዛ ነው የምጠቀመው" ሲል ተናግሯል።

ከዚህም አልፎ አብዱ የፎቶ ተነሺዎቹን ሁኔታና ስሜት በጆሮው ይረዳል።

በአጭሩ ፎቶ እያነሳዎት ገፅታዎን ተረድቶ 'ፈገግ በሉ' ሊልዎት ይችላል። "ከሚያወጣው ድምጽ [ፎቶ ከሚነሳው] ብዙ ነገር እረዳለሁ" ይላል።

ቢቢሲ- እስኪ እናፍታታው አንድ ሰው ፎቶ ሊነሳ ነው - ባንተ። ገጽታውን ያለእይታ እንዴት ትረዳለህ?"

አብዱ- ፊትለፊት ቁም እለዋለሁ [ተነሺውን] መጀመሪያ ደረጃ ስምህ ማነው እላለሁ። ወይም ስምህን ንገረኝ ወይም ደሞ እኔ ምን እያደረኩ ነው እላለሁ፤ ከዚያ የሚወጣ የድምጽ እንቅስቃሴ አለ። በዛ መኮሳተሩን፣ መሳቁን ወይም የሆነ ነገር ውስጥ መሆኑን እኔ እረዳለሁ። በመቀጠል [ኮስተር ካለ/ለች] ፈገግ በል እላለሁ ወይም ፎቶ ሲያነሱ የሚጠቀሙበት ቴክኒኮች አሉ አይደል? - እንዲስቅ ወይም የሆነ ነገር እንዲያደርግ እናገራለሁ። ፈገግ እንዲሉ የሚያደርጉ ቃላትን እጠቀማለሁ።"

በተጨማሪም የምስሉን የእይታ ጥራት [focus መሆኑን]፣ ቀለሙንና ፍሬሙን ትክክለኝነት ለማረጋገጥም ድምጽን እንደሚከተል የሚገልጸው አብዱ "ብዙ ልምምድ ስላላኝ target [ኢላማዬን/ ማንሳት ያለብኝን ነገር] አልስትም" ሲልም ይጠቅሳል።

ሆኖም ድምጽን በትክክል ለመረዳትና ፎቶ ለማንሳት አዳጋች የሚሆንበት አጋጣሚዎች አሉ።

ለአብነት አዳራሽ ውስጥ በድምጽ ማጉያ የሚከናወኑ ስብሰባዎች ላይ ተናጋሪው ሰው የት እንዳለ በትክክል ለመረዳት እንደሚያስቸግር ይገልጻል።

ይሁን እንጂ አብዱ ለዚህም መፍትሄ አያጣም። የአንድ ወቅት አጋጣሚውን ይናገራል። ፎቶ ለማንሳት ከአንድ አዳራሽ ይገባል።

"መድረክ ላይ ያሉት ዓይነ ሥውር መሆኔን አያውቁም። ፎቶ ማንሳት አለብኝ ብዬ ሆን ብዬ ነው የገባሁት። ድምጹ ግራና ከቀኝ ስለሚመጣ [ሰብሳቢው] የት ጋር እንዳለ ማወቅ አልቻልኩም። አጠገቤ ያለውን ሰው 'ድምጽ ማጉያውን እንደማብራትና ማጥፋት አድርገው' አልኩት። ሰውዬው ድንገት ከማይክ ውጪ ሲያወራ የት ጋር እንዳለ አገኘሁት" ሲል ይገልጻል።

ታዲያ የተነሳውን ፎቶ ሰብሳቢ አይቶት "በፍጹም አላመነም። መነጽሬን አስወለቀኝ"ም ብሏል።

የአብዱ ፎቶዎችና የተመልካች አስተያየት

አብዱ ያነሳቸውን ፎቶዎች ብዛት በትክክል ባያስታውስም ቢሮው፣ አካባቢውና ለስራ ሲወጣ "ብዙ" ፎቶዎችን ማንሳቱን ተናግሯል።

አጋጣሚዎች በተመቻቸለት ጊዜ ሁሉ ፎቶ ማንሳቱንም ቀጥሏል።

አይነስውሩ ፎቶ ግራፈር ለመጀመሪያ ጊዜ ፎቶ ያነሳው የስራ ባልደረባውን ነበር።

"ፎቶ አንሺ ነበረች ክፍሉ ላይ ከሷ ልጀምር ብዬ በራሷ ነው የተለማመድኩት" የሚለው አብዱ በተለያየ መንገድ ካሜራውን ከተረዳ በኋላ ያነሳው የመጀመሪያው ፎቶ ብዙዎች ያስገረመ እንደነበር ገልጿል።

"[ፎቶ የተነሳችው ሰው] ለምትቀርባቸው ሰዎች ስታሳያቸው አላመኑም - ስላልተለመደ። እንኳን ይሄ ፎቶ ይቅርና በመደበኛ ስራ ሰው አያምንም" ሲል ያስረዳል።

አንዳንዴ ደግሞ "አውቀህ ነው እንጂ ታያለህ" የሚል አስተያየት ጭምር እንደሚደርሰው ይገልጻል። ለሌላ ግዜ የሰዎች አግራሞት በጣም ከፍ ሲል "እስኪ መነጽርህን አውልቀው" እስከ ማለት የሚደርሱም አሉ።

አብዱ የትራንስፖርት ሚኒስትሯን ዳግማዊት ሞገስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ መንግሥት የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት እሱ በሚሰራበት ቦታ መጥተው ጉብኝት ሲያደርጉ ፎቶ አንስቷቸዋል።

እሳቸውም መገረማቸውና እንዳበረታቱት አስረድቷል። እናም ካሉት ፎቶዎች ሁሉ ለዚህ ፎቶ የተለየ ቦታ እንደሚሰጥ ይገልጻል። ለምን?

"ብዙ ጊዜ በቢሮ ልጆች ወይም'ደሞ አስተዳደር ላይ ባሉ ሰዎች [ፎቶ ለማንሳት] ስለምቀራረብ ያን ያህል አልፈራም። እንዲህ አይነት ድንገተኛ ሰው መጥቶ አንሳ ስባል ፎቶውም ይወጣል አላልኩም። የሚገርመው ነገር ግን አሪፍ ፎቶ ወጣ። የእርሳቸው ፎቶ ያስገርመኛል" ብሏል።

በሌላ በኩል አብዱ ቅጽበቶችን ጠብቆ ፎቶ የሚያነሳበት ጊዜያት እንዳለም ያስረዳል።

"ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብዬ ድንገት ካሜራ አንስቼ እያወሩ ወይ ስራ ስንወጣ የሚላፉም ምንም የሚሉ የሚቀላለዱ ሰዎች ሳይ ድንገት አነሳለሁ" ሲል ተናግሯል።

ያነሳውን ፎቶ 'ጥሩ' መሆን አለመሆኑን 'ስሜቴ ይነግረኛል' ከዛ ውጪ ማንኛውም ፎቶግራፈር ሊፈጥር የሚችለውን ስህተት ልሰራ እችላለሁ ሲል ያክላል።

አብድ ፎቶ ብቻ አያነሳም። ምጣድና የኤሊትሪክ ምድጃ ሌሎች ነገሮችን ይጠግናል። የሚጠግነውን ዕቃ ያለበትን ችግር በመዳሰስ ወይም በማሸት እንደሚሰራና ቤቱ የኤሌክትሪክ ዕቃ ሲበላሽ ለመጠገን ሌላ ሰው እንደማይጠራ ይናገራል።

የአብዱ የፎቶ አውደርዕይ የማዘጋጀት ሀሳብ

በዓይነ ሥውር የተነሱ ፎቶዎች የተሰባሰቡበት የፎቶ አውደ ርዕይ የማዘጋጀት ዕቅድ አለው። አውደ ርዕዩ ከተፈጥሮን ገጽታ እስከ ሀገር መሪዎች የሚያሳዩ ፎቶዎችን የሚይዝ ነው።

ይህንን ዕቅዱንም ለማሳካት እንቅስቃሴዎች ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በኮሮና ወርሽኝ መከሰት ሳይሳካ ቀርቷል። ያ እቅዱ ግን አሁንም አለ።

"ግን ይሄን ነገር ተግባር ላይ ላውለው የምችለው ዕቃው [ካሜራው] ሲኖረኝ ነው። ዕቃው በእጄ ስለሌለ ማከናወን አልቻለም። የመንግሥት ዕቃ ስለሆነ እንደልቤ አላንቀሳቅሰውም። እሱም ቢሆን አሁን ስለተበላሸ እየሰራሁበት አይደለም። ግን ትልቅ ሀሳብ አለኝ።"

ሌላው የአብዱ ዕቅድ በዓይነ ሥውር የተገነባ የፎቶ ስቱዲዮ መገንባት ነው። ከዚያም ሲያልፍ እንደሱ አይነት ችሎታ ያላቸውን ዓይነ ሥውራን ሊደግፍ የሚችል ማዕከል የማቋቋም ሀሳብም በአእምሮ ውስጥ ይመላለሳል።

"አካልጉዳተኛ ከአንድ ፋብሪካ የተመረተ አይደለም"

እንደማንኛው ሰው አይነ ስውራንም የራሳቸው መክሊት አላቸው ሲል የሚገልጸው አብዱ የሚፈልጉትን ነገር ማሳካት ይችላሉ የሚለውን ለማሳየት እንደሚጥር ይናገራል።

"ያ ደግሞ የሚጀመረው ከራሱ ከባለቤቱ ነው። ስለዚህ እኔ ባለቤት ነኝ፤ አይነስውር ነኝ። እኔ እየሰራሁ ካላሳየሁ ማንም ሊያምን አይችልም።"

"አካል ጉዳተኛ ከአንድ ፋብሪካ የተመረተ አይደለም" በማለት በሰዎች ዘንድ እንደሱ ያሉ ሰዎችን በሙሉ ተመሳሳይ እንደሆኑ እንደሚታሰብ ጠቅሷል።

"መለወጥ፣ መስራት፣ የሰውን አመላከት [አይነስውራንን በተመለከተ] መቀየር እንደሚችል በተግባር እኔ ምክንያት ሆኛያለሁ ብዬ አስባለሁ።"

የ33 ዓመት አቡዱ ባለትዳር ሲሆን ሁለት ሴት ልጆች አሉት። ታዲያ ነገሮች በሚመቻችለት ፎቶ ከማንሳት ተሻግሮ ቪዲዮ መቅረጽ እንደሚፈልግ ይገልጻል። ይህም የማይሆንበት ምክንያት የለም የሚል ጹኑ እምነት አለው። ምክንያቱም እንዳ አይስውሩ ፎቶግራፈር አብዱ ገለጻ "ዓይን ማያ እንጂ ማሰቢያ አይደለም!"