ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት ታሪካዊ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በአደጋ ላይ ናቸው-ተመድ
በዩክሬን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሁለት ታሪካዊ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና ገዳም አደጋ ላይ መውደቃቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ እና የባህል ማዕከል ዩኔስኮ አስታወቀ።
ዩኔስኮ ከሩሲያ ጋር ባለው ጦርነት የመውደም አደጋ ተጋርጦባቸዋል ያላቸው ታሪካዊ ቅርሶች በሁለት ከተሞች ይገኛሉ።
በመዲናዋ የምትገኘው የቅድስት ሶፊያ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በኪየቭ ፔሰርስክ የምትገኘው እና በመካከለኛው ዘመን የተገነባው ላቭራ ገዳም ናቸው።
በሊቪቭ ከተማ የሚገኝ ታሪካዊ ማዕከልም በዩኔስኮ አደጋ ከተጋረጠባቸው የዓለም ቅርሶች መዝገብ ተካትቷል።
እነዚህን ታሪካዊ ስፍራዎች ለመጠበቅ ሁኔታዎችን ማሟላት ፈተና እንደሆነበትም ነው ዩኔስኮ የገለጸው።
በሁለቱ ከተሞች ላይ እየደረሰ ባለው የቦምብ ጥቃት እነዚህ ታሪካዊ ቅርሶች በቀጥታ የመመታት ስጋት ተጋላጭ መሆናቸውንም ነው ዩኔስኮ በማጠቃለያው የገለጸው።
ዩኔስኮ እነዚህን ታሪካዊ ቅርሶቹ በአደጋ ላይ መሆናቸውን በድረገጹ ዝርዝር ውስጥ ለማካተት የመረጠበት ዋነኛም ምክንያትም የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ለቅርሶቹ ጥበቃ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መሆኑንም አመላክቷል።
በተጨማሪም ለቅርሶቹ ጥበቃ እንዲሆን የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ “በር ይከፍታል” ብሏል።
ሩሲያ በነዚህ ቅርሶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የታጠቁ ኃይሎቿ “አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን” እየወሰዱ መሆኑን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አረጋግጣለች።
ይህንን ግን ዩክሬን አልተቀበለችውም።
ዩኔስኮ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከምትፈጽመው የቦምብ ጥቃት ጋር ተያይዞ ወቀሳዎችን አሰምቷል።
ተቋሙ ከወራት በፊት ታሪካዊ ከሆነችው ሊቪቭ ወጣ ብሎ በሚገኝ ህንጻ ላይ የደረሰውን የቦምብ ጥቃት አውግዟል።
ከተማዋ የተቆረቆረችው በመካከለኛው ዘመን ሲሆን ከ13ኛው እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ባለው ጊዜ አስተዳደራዊ፣ ሃይማኖታዊ እና የንግድ ማዕከልነቷንም ጠብቃ ቆይታለች።
በኪነ ህንጻዎቿ እና በቅርሶቿ የምትታወቀው ይህች ጥንታዊ ከተማ በአውሮፓውያኑ 1998 በዓለም ቅርስነት ተመዝግባለች።
የቅድስት ሶፍያ ካቴድራል በበኩሏ የተገነባችው በ11ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን በወቅቱ የቁስጥንጥንያ አካል ከነበረችው ሃጊያ ሶፍያ ጋር እንድትወዳደርም በማሰብ ነበር።
በዚያ ዘመን ከተገነቡት እና ካልወደሙት ህንጻዎች ውስጥ አንዷ ናት። የኪዬቭ ፔቨርስክ ላቭራ ወይም የኪየቭ የዋሻዎች ገዳምም ከካቴድራሏ ጋር በተመሳሳይ ወቅት ነው የተገነባው።