የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ተወካዮች በናይሮቢ እየተወያዩ መሆኑ ተነገረ

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ከፍተኛ ተወካዮች ለሦስት ቀናት የሚቆይ የምክክር ስብሰባ በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ እያደረጉ ነው።

ከዛሬ ረቡዕ ታኅሣሥ 12/2015 ዓ.ም. ጀምሮ አስከ አርብ ድረስ እንደሚካሄድ የተነገረው ንግግር ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም፣ ደቡበ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ የተፈረመውን ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ትግበራን የሚመለከት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ) ቃለ አቀባይ ኑር መሃመድ ሼክ በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች አዛዦች መካከል የምክክር ስብሰባ በናይሮቢ እየተካሄደ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

"በፕሪቶሪያ የተፈረመው ስምምነት ያለምንም እንቅፋት ተፈፃሚነት እንዲኖረው ኢጋድ ከሁለቱ ወገኖች፣ ከአፍሪካ ህብረት እና ከአጋሮች ጋር በንቃት እየሰራ ነው።" የሚልም መልዕክት አስፍረዋል። ለሦስት ቀናት በሚቆየው ስብሰባ ላይ ሁለቱ ወገኖች የትጥቅ ማስፈታቱ ሂደት ትግበራ፣ የአፍሪካ ኅብረት ለሚያካሂደው የስምምነቱ ትግበራ ቁጥጥር ማስፈጸሚያ ነጥቦች ላይ ውይይት በማድረግ ያጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቀደም ሲል ናይሮቢ ውስጥ ድርድር በተደረገበት ስፍራ ላይ ለቀጣዮቹ ቀናት የሚካሄደው ይህ ሦስተኛ ዙር ውይይት በዝግ የሚደረግ ሲሆን በማጠቃለያው ላይ መግለጫ እንደሚሰጥ ተነግሯል።

በስብሰባው ላይ የአፍሪካ ኅብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ)፣ የአሜሪካ መንግሥት ተወካዮች የሚሳተፉ ሲሆን የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታም እንደሚገኙበት ተገልጿል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የትግራይ ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በድርድሩ ላይ የሚሳተፈውን ቡድን መልሶ በማዋቀር 11 አባላት ያሉት ተደራዳሪዎችን ይፋ አድርጓል።

በዚህም የቡድኑ ስምንት አባላት ስም የተገለጸ ሲሆን በተጨማሪም ሁለት አባላት ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ እና በክልሉ ካሉ ተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንድ ተወካይ እንደሚካተት ተገልጿል።

በፕሪቶሪያ ተከትሎም ናይሮቢ ላይ በሁለቱ ወገኖች መካከል ግጭት ለማቆም፣ ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ እና የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ ከስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።

ሁለት ወር ሊሞላው የተቃረበውን ስምምነት ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው የእርዳታ አቅርቦት መሻሻል እንደታየበት የተነገረ ሲሆን፣ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ እና የስልክ አገለግሎቶች መልሰው መጀመራቸው ተዘግቧል። በተጨማሪም በዚህ ሳምንት ባንኮች ሥራ እየጀመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የስምምነቱ አንድ አካል የሆነው የኤርትራ ሠራዊት መውጣት ጉዳይ ተግባራዊ እንዳልሆነ በትግራይ ባለሥልጣናት በኩል ባለፉት ሳምንታት በተደጋጋሚ ሲሰማ ቆይቷል።

በተመሳሳይም የህወሓት ኃይሎች ከበርካታ የጦርነት ግንባሮች መውጣታቸው የተነገረ ቢሆንም የትጥቅ መፍታት ሂደቱ አስካሁን ስለመጀመሩ የተባለ ነገር የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ባለፈው ቅዳሜ ታኅሣሥ 08/2015 ዓ.ም. በኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት በኩል ባወጣው መግለጫ ላይ የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጾ ነበር።

ነገር ግን እሁድ ዕለት የህወሓት ሊቀመንበር እና የክልሉ ፕሬዝዳንት ዶክተር ድብረጽዮን ገብረሚካኤል ግን መቀለ በተካሄደ ስብሰባ ላይ በስምምነቱ መሠረት ከመንግሥት በኩል የሚጠበቀው ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

መንግሥት በመግለጫው “ለአገር እና ለሕዝብ ሲባል በተደረሰው የሰላም ስምምነት የገባውን ቃል ሳይውል ሳያድር እና ሳያንጠባጥብ በመፈጸም ላይ ይገኛል” ብሏል።

ደብረጽዮን (ዶ/ር) የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ወዲህ በትግራይ በኩል ሁሉም የሰላም ስምምነቱ ጥያቄዎችን እየፈጸሙ መሆናቸውን ጠቅሰው “በፌደራል መንግሥት በኩል ከሰብአዊ እርዳታ አንፃር አበረታች ጉዳዮች ቢኖሩም በተቀሩት የሰላም ስምምነቱ ነጥቦች ዙርያ ግን መንግሥት በቃሉ መሠረት አልፈጸመም” ብለዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ከቀናት በፊት እንዳሳወቀው የመከላከያ ሠራዊት ባልደረሰባቸው መቀለን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተደራጀ የዝርፊያ ድርጊቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን በመግለጽ፣ መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ያለበትን ኃላፊነት ለመፈጸም አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አመልክቷል።

ሁለት ዓመት ያስቆጠረውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በመንግሥት እና በህወሓት አመራሮች መካከል በመጀመሪያ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተደረገውን ድርድር ተከትሎ ዘላቂ ግጭት የሚያስቆም እና ትጥቅ የመፍታት ስምምነት ተደርሶ ነበር።

በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በተደረሰው ስምምነት ግጭት ማቆም፣ የሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ እና ከፌደራሉ ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ ስምምነት

ሁለት ዓመት የደፈነው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የኤርትራ ሠራዊት የፌደራል መንግሥቱን በመደገፍ በግጭቱ ውስጥ ሲሳተፍ መቆየቱ ሲዘገብ የቆየ ቢሆንም፣ በሁለቱ ወገኖች በተደረሰው ስምምነት ላይ ግን የኤርትራ ስም በግልጽ አልተጠቀሰም።