ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፌደራል ሠራዊት ወደ አዲግራት ከተማ መግባቱን ነዋሪዎች ተናገሩ
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ወደቆየችው የአዲግራት ከተማ መግባታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጹ።
ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ በስተሰሜን ከ115 ኪሎ ሜትሮች በላይ በሚሆን ርቀት ላይ የምትገኘው አዲግራት በህወሓት ተዋጊዎች ቁጥጥር ስር ከቆዩት ከተሞች አንዷ ነበረች።
ለሁለት ዓመታት የቆየውን ጦርነት ባስቆመው ስምምነት መሠረት የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት ወደ አዲግራት ከተማ ማክሰኞ ጥር 09/2015 ዓ.ም. መግባቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተውበታል የተባለውን ጦርነት ለማብቃት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት በተደረገው ድርድር የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ተቋማትን እንዲቆጣጠሩ ተስማምተዋል።
በዚህም መሠረት ከሳምንታት በፊት የፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች ወደ መቀለ በመግባት የአየር ማረፊያውን እና ሌሎች ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን መጠበቅ መጀመራቸው ይታወሳል።
በህወሓት ተዋጊዎች ቁጥጥር ስር ከነበሩት ትላልቅ ከተሞች መካከል አንዷ ወደ ሆነችው አዲግራት ከተማ ሠራዊቱ የገባው በእግር፣ በአውቶቡሶች እና በከባድ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፍጹም የተባሉ የአዲግራት ነዋሪ ከተማዋ የተረጋጋች መሆኗን በመገልጽ “ከዚህ በፊት ከተከሰተው ነገር ጋር በተያያዘ ፍርሃት ቢኖርም፣ አስካሁን ግን ምንም የተከሰተ ነገር የለም” በማለት ማክሰኞ ምሽት ለቢቢሲ ተናግሯል።
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በትግራይ ክልል ውስጥ ካሉ ትላልቅ ከተሞች መካከል አንዷ ወደሆነችው አዲግራት ከተማ በመግባት መሰማራታቸውን በተመለከተ ከፌደራል መንግሥቱም ሆነ ከትግራይ ባለሥልጣናት የተባለ ነገር የለም።
ወታደሮቹ በአዲግራት ውስጥ የሚገኙ መሠረተ ልማቶች እና ከጦርነቱ መቀስቀስ በፊት የነበሩ ወታደራዊ ካምፖችን እንደሚቆጣጠሩ ይጠበቃል።
ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ የተለያዩ መሠረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠውባት የቆየችው ትግራይ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ የአየር ትርንስፖርት፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ እና የባንክ አገልግሎቶች በተለያዩ ስፍራዎች ሥራቸውን ጀምረዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ረቡዕ ዕለት የገባባት አዲግራት ከተማ አስካሁን ከስልክ አገልግሎት ውጪ ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች አለመጀመራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ መልሶ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በርካታ የትግራይ አካባቢዎች በፌደራል መንግሥቱ እና በኤርትራ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ገብተው የቆዩ ሲሆን፣ አዲግራት ግን በህወሓት ተዋጊዎች ቁጥጥር ስር ነበር የቆየችው።
የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት የእርዳታ አቅርቦት ወደ ክልሉ ያለችግር እንዲገባ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች ሥራ እንዲጀምሩ እና ከአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ እንዲሁም የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ እንዲፈቱ ተስማምተዋል።
በክልሉ ውስጥ ያሉ የፌደራል መንግሥቱ የሚያስተዳድራቸው ተቋማት በመከላከያ ሠራዊቱ ቅጥጥር ስር እንዲሆኑ በተስማሙት መሠረት ነው ወታደሮች ወደ አዲግራት የገቡት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራ ሠራዊት እስካሁን ከትግራይ ክልል እንዳልወጣ የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
አቶ ጌታቸው ይህንን ያሉት በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን ስምምነት የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ ሆነው ያሸማገሉት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለአንድ ጋዜጣ የተናገሩትን ተከትሎ ነው።
አቶ ጌታቸው ኦባሳንጆ ለፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ “የኤርትራ ወታደሮች ድንበር ላይ ናቸው” ማለታቸው ትክክል እንዳልሆነ በማንሳት ይልቁንም “የኤርትራ ወታደሮች እስካሁን ከትግራይ የመውጣት ፍላጎት የላቸውም” በማለት ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።