የገንዘብ ሽልማት ለማሸነፍ ሴት መስሎ በቼዝ ውድድር ላይ የተሳተፈው ወጣት ተያዘ

የ25 ዓመቱ ኬንያዊ ወጣት ስታንሊ ኦሞንዲ በቀላሉ የገንዘብ ሽልማት አሸንፋለሁ በሚል እንደ ሴት ለብሶ አገር አቀፍ የቼዝ ውድድር ላይ በሴቶች ዘርፍ ሲሳተፍ ተያዘ።

ወጣቱ ስታንሊ እንደ ሙስሊም ሴት ከራስ ፀጉሩ አስከ እግሩ ድረስ የሚሸፍነውን ልብስ በመልበስ፣ እንዲሁም መነጽር አድርጎ ሚሊሰንት አዉር በሚል የሴት ስም ነበር ለውድድር የቀረበው።

ነገር ግን ኦሞንዲ በውድድሩ ላይ በሚያስመዘግበው ውጤት አዘጋጆቹ ከዚህ በፊት የማያውቋት የቼዝ ጥበበኛ ከየት መጣች ብለው ጥርጣሬ ተፈጠረባቸው።

የኬንያ ቼዝ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በርናርድ ዋንጃላ እንዳሉት “ሂጃብ መልበስ የተለመደ ነገር በመሆኑ፣ በመጀመሪያ ላይ ምንም አይነት ጥርጣሬ አልነበረንም” ብለዋል።

ውድድሩ ቀጥሎ እየተካሄደ ሳለ ግን ሴት መስሎ የቀረበው ኦሞንዲ ታዋቂ ሴት የቼዝ ተጫዋቾችን ማሸነፍ ቻለ። ይህን ጊዜ ጥርጣሬ መፈጠር ጀመረ “ከዚህ በፊት በውድድሩ ላይ ያልተሳተፈች አዲስ ሴት ጠንካራ የቼዝ ተጫዋቾችን ማሸነፏ ጥያቄ ፈጠረብን” ሲሉ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግረዋል ዋንጃላ።

በተጨማሪም የሚያደርገው ጫማ እና በውድድሩ ወቅት ምንም አለመናገሩ የበለጠ ጥርጣሬያቸውን አጎላው።

“የበለጠ እንድንጠራጠር ያደረገን አንዱ ነገር የሚያደርጋቸው ጫማዎች ነበሩ። በአብዛኛው የሴት ሳይሆን የወንድ ጫማዎችን ማድረጉ ጥያቄ ፈጠረብን።”

ዋንጃላ ጨምረውም ተወዳዳሪው የመለያ ወረቀቱን ሲወስድ እና በውድድር ላይ ምንም ቃል አይተነፍስም “የቼዝ ጨዋታ ከተፎካካሪ ጋር ንግግር የሚደረግበት የወዳጅነት ጨዋታ ነው፤ እሱ ግን አይናገርም።”

ይህ ሁሉ ጥርጣሬ ቢኖራቸውም የውድድሩ አዘጋጆች በለበሰው ሃይማኖታዊ ልብስ ምክንያት መገለል እና እንግልት አደረሳችሁ ተብለን እንከሰሳለን በሚል ስጋት እስከ አራተኛው ዙር ድረስ በውድድሩ እንዲቀጥል ፈቀዱ።

ዋንጃላ እንዳሉት “ከባድ ፉክክር አድርጎ በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር ሲያልፍ ጠራነው፣ ምንም የመደናገጥ ነገር አልታየበትም።”

ጥያቄ በቀረበለት ጊዜም ወንድ መሆኑን አመነ። በውድድሩ ላይ ሴት መስሎ የተሳተፈውም የገንዘብ ችግር ስላለበት ማሸነፍ ከቻለ የሚያገኘው የሽልማት ገንዘብ ይረዳኛል በሚል መሆኑን አስረዳ።

በኬንያ አገር አቀፍ የቼዝ ውድድር ላይ ከ400 በላይ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ በሴቶች ዘርፍ 99 ተወዳዳሪዎች ተመዝግበው አሸናፊ የምትሆነው ከሦስት ሺህ ዶላር በላይ የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላታል።

ለፈጸመው ጥፋት መጸጸቱን በመግለጽ ይቅርታ እንዲደረግለት መጠየቁን የገለጹት የኬንያ የቼዝ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት፣ እስከ መጨረሻው በቼዝ ውድድር ፈጽሞ እንዳይሳተፍ የሚያደርግ ቅጣት ባይጣልበት እንኳን፣ “ለበርካታ ዓመታት” ሊታገድ እንደሚችል ተናግረዋል።

የኬንያ የቼዝ ውድድር በየዓመቱ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን፣ የዚህ ዓመቱ ባለፈው ሳምንት ተካሂዷል።

ኦሞንዲ ጎበዝ የቼዝ ተጫዋች ቢሆንም በወንዶች ዘርፍ ከባድ ፉክክር ይኖርብኛል ብሎ በማሰቡ፣ ሴት መስሎ በመወዳደር የሽልማቱን ገንዘብ ለማሸነፍ የተሻለ ዕድል ይኖረኛል በሚል ነው በሴቶች ዘርፍ ለመወዳደር የቀረበው ሲሉ ዋንጃላ ተናግረዋል።

የኬንያ ቼዝ ፌዴሬሽን በሚያካሂዳቸው ውድድሮች ላይ የዕድሜ ማጭበርበሮች የሚያጋጥሙት ሲሆን፣ የአሁኑ አይነት የጾታ ማጭበርበር ግን የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

የኦሞንዲ ጉዳይ ለስፖርቱ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የተመራ ሲሆን በቀጣይ ቀናት ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ለበርካታ ዓመታት ከስፖርቱ ሊታገድ ይችላል።

በተጨማሪም የኦሞንዲ ጉዳይ ለዓለም አቀፉ የቼዝ ፌዴሬሽን እንደሚተላለፍ የኬንያ ቼዝ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት በርናርድ ዋንጃላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።