“የልጆቼን ጥያቄ ባለመመለሴ . . እንደ እናት መከታ አልሆንኳቸውም ብዬ ራሴን እወቅሳለሁ" ሚለን ኃለፎም

ከሁለት ዓመት በፊት ኬንያ ውስጥ “በጸጥታ ኃይሎች” የተወሰደው አቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል ደብዛው እንደጠፋ ነው።

ባለቤቱ ሚለን ኃለፎም እስካሁን ድረስ ባለቤቷ የት እንዳለ የሰማችውም ነገር እንደሌለም ለቢቢሲ ተናግራለች።

“. . . ተስፋ አይቆረጥም ብለን ነው እንጂ እየታገልን ያለነው እስካሁን ድረስ ያለበትንም ሆነ በምን ሁኔታ እንዳለ አናውቅም።”

አቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል ከሁለት ዓመት በፊት ነበር በኬንያ መዲና ናይሮቢ፣ ኪሌለሽዋ በተባለ አካባቢ የግል መኪናውን ሲያሽከረክር ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች መንገድ በመዝጋት ከመኪናው አስወርደው ወደ ወደሌላ ተሽከርካሪ አስገብተው የወሰዱት።

በመንገደኞች ተቀርጾ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለቀቀ ቪዲዮም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ያሳያል።

አቶ ሳምሶን ለ19 ዓመት በኖረባት ኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ ታግቶ ደብዛው ከጠፋ በኋላ፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን አቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል የት እንዳለ አለመታወቁን በመቃወም ሰልፍ ማካሄዳቸው ይታወሳል።

ሁለት ዓመት ሙሉ የባለቤቷን መገኛ ለማወቅ በኬንያ እና በኢትዮጵያ ላይ ታች የምትለው ሚለን “እኔን የሚደክመኝ የልጆቼን ጥያቄ መመለስ ባለመቻሌ ነው” ትላለች።

“የልጆቼን ጥያቄ ባለመመለሴ በጣም ይደክመኛል። በጣም ራሴን እወቅሳለሁ። እንደ እናት መከታ አልሆንኳቸውም ብዬ አዝናለሁ። . . . ሳሚን የመፈለጉ መንገድ እየረዘመ፣ እያደከመኝ ቢሄድም ተስፋ አልቆርጥም” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

አክላም ከእኔ ይልቅ ትላለች የሳምሶን ባለቤት ሚለን “ልጆቼ የአባታቸው ነገር ላይ ተስፋ እንደመቁረጥ ነገር አይባቸዋለሁ።”

“ ሁሌም ጭንቅላታቸው ላይ ትልቅ ጥያቄ የፈጠረ ነገር ነው። በተስፋ መቁረጥና ባለመቁረጥ መካከል ውስጥ ናቸው”

የአቶ ሳምሶን ባለቤት ሚለን ኃለፎም፣ የባለቤቷን ባልታወቁ ሰዎች መታገት በማስመልከት በኬንያ ክስ መስርታ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዟል።

የባለቤቷ የአቶ ሳምሶን ጉዳይ ከባለፈው ዓመት ይልቅ አሁን ያለበት ደረጃ ጥሩ መሆኑን የምትናገረው ሚለን፣ ፖሊስ ምርመራ አድርጎ ፋይሉን ወደ አቃቤ ሕግ መርቶታል ትላለች።

እርሷም ሆነች በወቅቱ በስፍራው የነበረው የትራፊክ ፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተው ቀጣይ ቀጠሮ ላይ ችሎት የሚወስነውን ለመስማት እየተጠባበቀች መሆኑን ትናገራለች።

አቃቤ ሕግ የደረሰው ፋይል ሳምሶን ሲታገት በቪዲዮው ላይ የሚታዩት የጸጥታ አካላት ‘ለክስ ይቅረቡ ወይስ አይቅረቡ’ የሚለው ላይ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ እየጠበቀች መሆኑን ታስረዳለች።

ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ደግሞ የአቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል ቤተሰቦች የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላይ ክስ ለመመስረት እንቅስቃሴ መጀመራቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቦ ነበር።

ኢትዮጵያ ላይ ያቀረበችው አቤቱታ እንደነበር ያስታወሰችው ሚለን፣ “ለጊዜው ገታ አድርጌዋለሁ” ብላለች።

ይህ የሆነበትን ምክንያት ስታስረዳም፣ ባለቤቷ አቶ ሳምሶን የታገተው ናይሮቢ ውስጥ በመሆኑ እና ጉዳዩ በአቃቤ ሕግ ተይዞ እየታየ በመሆኑ በአንድ ሃሳብ የፍርድ ቤት ውሳኔን ከሰማሁ በኋላ “የዛኛው ይቀጥላል” ብላለች።

ሳምሶን በኬንያ የጸጥታ አካላት ስለመታገቱ እርግጠኛ መሆኗን የምትናገረው ሚለን፣

“የቢዝነስ አጋሮች፣ ሌቦች ናቸው ያገቱት ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ምክንያቱም ትራፊክ ፖሊሱ በሩን እየከፈተላቸው እየረዳቸው እያስወጣው ይታያል[ቪዲዮው ላይ]። ስለዚህ ያንን ነገር ሲያደርገው ከመንግሥት የመጣ ካልሆነ በስተቀር በዚህ ደረጃ የሚያግት ሌባም ሆነ አጋች ይኖራል ብዬ አላስብም” ብላለች።

ሳምሶን የተወሰደው በኬንያ የጸጥታ ኃይሎች መሆኑን የምትናገረው ባለቤቱ ወ/ሮ ሚለን፣ በሕግ የሚፈለግ ከሆነ በሕግ አግባብ እንዲጠየቅ በማለት እንደምትጠይቅ ትናገራለች።

“ሳምሶን እንደማንኛውም ሰው፣ ሰው ነው፤ ጥፋት ሊያጠፋ ይችላል። ጥፋት አጥፍቶ ከሆነ ለህግ ይቅረብ እያልን ነው የሚመለከተውን አካል የምንማጸነው።”

እስካሁን ድረስ ለምን ታፍኖ ቆየ? የሚለው የእርሷም የዘወትር ጥያቄ መሆኑን የምታስረዳው ሚለን፣ አጥፍቶ ከሆነ ለምን እስካሁን ፍርድ ቤት ቀርቦ በጥፋቱ መሰረት አይጠየቅም ለሚለውም እርሷም መልስ እንደሌላት ታስረዳለች።

ይህ ነው የሚል ማስረጃ ማቅረብ ባልችልም በሁለቱም ወገን [በኬንያም በኢትዮጵያም] በአንዳንድ ወዳጆቻችን በኩል ደህና እንደሆነ እንሰማለን ስትል ባለቤቷ አሁንም በሕይወት ስለመኖሩ ወሬዎችንም እንደምትሰማ አክላለች።

"እንደ ባለቤቱ፣ እንደ ቅርብ ሰው ደግሞ እኔ አንድ ቀን በሩን አንኳኩቶ እንደሚመጣ ሙሉ ተስፋ ነው ያለኝ።"

በሕይወት እንዳለ እርግጠኛ ከሆንሽ ለምንድን ነው እስካሁን ድረስ ድምጹን መስማት ያልቻልሽው፣ እርሱን ቤተሰቡን ማግኘት ያልቻለው ሲል ቢቢሲ ላቀረበላት ጥያቄ ስትመልስም፣

“እኛም እስካሁን ድረስ በጣም እየረበሸን ያለው፣ እስከመቼ ነው እንደዚህ የሚሆነው የሚለው ሲሆን፣ በግለሰብ ደረጃ ትንሽ ስለሚከብድ በመንግሥት ደረጃ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት. . . እንዲረዳን እየጠየቅን ነው ያለነው”

ሳምሶን በታገተ ወቅት ኬንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኬንያ መንግሥት አቶ ሳምሶን ያለበትን ቦታ በግልጽ እንዲያሳውቅ በይፋ መጠየቁን አሳውቆ ነበር።

በወቅቱ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ መለስ ዓለም "የኬንያ መንግሥት እና የሕግ አካላት ሳምሶን የት እንዳለ እንዲያሳውቁን ጠይቀናል" ሲሉ ለኬንያ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ መስጠታቸው አይዘነጋም።

ጨምረውም "የተፈጠረው ክስተት ኢትዮጵያን አስደንግጧታል። . . . በማኅበረሰቡ ዘንድ በብዙዎች የሚከበር ሰው እንደመሆኑ ድንገት መጥፋቱ አገሩ ኢትዮጵያን ጎድቷል" ሲሉም አምባሳደሩ በወቅቱ ተናግረው ነበር።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኬንያ መንግሥት ደብዳቤ መጻፉን እንደነገሯት የምታስታውሰው ሚለን፣ አሁንም ከኤምባሲው ጋር በቅርበት እየተነጋገረች መሆኑን ገልጻለች።

“. . . በጥያቄ ደረጃ ነው ያለው። መልስ እንዳልተሰጣቸው እና መልስ እየጠበቁ እንደሆነ እና እስካሁን መልስ እንዳልተሰጠ ነው የማውቀው በኢትዮጵያ በኩል።”

ባለቤቷ አንድ ቀን ከታገተበት ተለቅቆ እንደሚመጣ ተስፋ እንደምታደርግ የምትናገረው ሚለን፣ “. . . እንደሚመጣ አውቃለሁ፥ ለልጆቼ አንድ ቀን መጥቶ ያስደንቀናል እላቸዋለሁ። ይህንን ሲሰሙ ያው ተስፋቸው ይለመልማል ። ያምኑኛል። ነገር ግን ሁሌ ይህንን ስለማልላቸው ውስጣቸውን እንደተረበሸ ነው።”

ይህም ቢሆን ግን ባለቤቷን ያለ ተጨባጭ ተስፋ ሁለት ዓመት በፍለጋ መባዘን ከባድ መሆኑን አልሸሸገችም።

“ከባድ ነው ከልጆች ጋር፣ ትልቅ ፈተና ነው”

አቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል በናይሮቢ በጋዝ ንግድ ላይ ተሰማርቶ ሁለት አስርታት ለሚጠጋ ዓመታት በኬንያ ኖሯል።