በመቀለ ለአራተኛ ቀን የቀጠለው የታክሲ ባለንብረቶች እና አሽከሪካሪዎች የስራ ማቆም አድማ

በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ የሚገኙ የታክሲ ባለቤቶች እና አሽከርካሪዎች የመቱት የስራ ማቆም አድማ አራተኛ ቀኑን ይዟል።

የታክሲ አሽከርካሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሰኞ/ ህዳር 3/ 2016 ዓ.ም የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ምክንያት የሆነው መንግሥት ያወጣው የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት የታሪፍ ማሻሻያ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ነው።

በመቀለ ከተማ የታክሲ አሽከርካሪ የሆኑት ከላሊ ሐዲስ የመንግሥትን አሰራርም በመተቸት ‘ፍትሐዊ’ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

“ጥያቄያችን የታሪፍ ጉዳይ ነው። የራሳቸውን ታሪፍ (ተመን) አውጥተው ሰጡን። አያዋጣንም አልናቸው። ሆነም ቀረም ያወጡትን ታሪፍ ቅጂ ያዙ አሉን። [ባልተስማማንበት ታሪፍ] መንገድ ላይ ጠብቀው ከ500 እስከ 1 ሺህ ብር ቅጣት መቅጣት ጀመሩ” ብለዋል።

“ከዚህ ቀደም ተሳፋሪዎችን ብዙ አካባቢዎች የምንወስደው በአስር ብር ነበር። በተሻሻለው ታሪፍ መሰረት ዘጠኝ ብር አድርገነዋል አሉ። አንድ ብር አልመለሳችሁም ብለው ቅጣት ይቀጣሉ። በዚህም ተማረን ከሰኞ ጀምሮ ስራ አቁመናል” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተሻለ አድሐኖምም በተሻሻለው የትራንስፖርት ታሪፍ ቅር ተሰኝቶ ስራ ካቆሙት አሽከርካሪዎች መካከል አንዱ ነው።

“አድማ ሳይሆን ጥያቄያችን ይመለስ ነው እያልን ያለነው። አሁን ያለው የኑሮ ውድነት ጥያቄ በሌሎች ዘርፎች እየተመለሰ ቢሆንም የትራንስፖርት ዘርፉ ችላ ተብሏል። ከወር በፊት የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ አስበን ነበር። የታክሲ ማህበራት ክልል ድረስ ሄደን እየሰራን ጥያቄያችንን እናቀርባለን ሲሉን ተስማማን” ብለዋል።

“ቀደም ብለው የወጡ ታሪፎች ተግባራዊ እንዳይደረጉ የጠየቅንባቸው ናቸው። ነገር ግን አሁን ያወጡት ታሪፍ የመለዋወጫ እና የነዳጅ ዋጋን ያላገናዘበ ነው” ሲሉም ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

በመቀለ ከተማ ሶስት የታክሲ ማህበራት ያሉ ሲሆን እነዚህም ለምለም ኩሃ፣ ህዳሴ እና ሐወልት ይባላሉ።

የታክሲ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲቋረጥ ሶስቱም ማህበራት ለመንግሥት ደብዳቤ ጽፈዋል።

ማህበራቱ ለመቀለ ከተማ ትራንስፖርት አስተዳደር በጻፉት ደብዳቤ የቆመው የትራንስፖርት አገልግሎት ከማህበራቱ እና ከዳይሬክተሮች ቦርድ እውቅና ውጭ እንደሆነም ገልጸዋል።

በመቀለ ከተማ ለአራተኛ ቀን የታክሲ አገልግሎት በመቋረጡም ነዋሪዎች ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸውንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንዳንዶችም በውድ ዋጋ የባጃጅ ኮንትራቶችንም ለመጠቀም ተገደናል ብለዋል። የመቀለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ትብርህ አስገዶም ከመሐል ከተማ መኖሪያ ቤታቸው እስከሚገኝበት ዳኤሮ ድረስ 10 ብር ይከፍሉ የነበሩ ቢሆንም አሁን የታክሲ አገልሎት በመቆራረጡ 30 ብር ለባጃጅ እንዲከፍሉ መጠየቃቸውንም ተናግረዋል።

“ታክሲዎቹ አገልግሎት በማቆማቸው ተጎድተናል። መንግሥት ስርዓት ያስይዝ። የታክሲ አሽከርካሪዎችም ከመንግሥት ጋር ተነጋግረው ይግባቡ። ለባጃጅ 30 ብር ሲመሽ ደግሞ አምሳ ብር ከፍለን አንወጣውም። ያለብን ችግር ይበቃናል” በማለት በምሬት ተናግረዋል።

ትግራይ ከበባ ውስጥ በነበረችበት ጊዜም ሆነ ከሰላም ስምምነቱ በኋላም የታክሲ ትራንስፖርት ስርዓቱን ያልጠበቀ እንደነበር ይነገራል።

ታክሲዎች ከመጠን ባለፈ መልኩ በተጨናነቀ ሁኔታ ተሳፋሪዎችን የሚጭኑ ሲሆን፤ 12 ተሳፋሪዎች መጫን የሚገባቸው እስከ 20 ሰዎችን እና ከዚያም በላይ መጫን የተለመደ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ከታክሲ አሽከርካሪዎች ማህበር ጋር በመመካከር ችግሩን ለመፍታት እና ስርዓት ለማስከበር እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል። ሆኖም ዕርምጃው ከመወሰዱ በፊት ውይይት እና መግባባት ላይ መደረስ እንደነበረበት የታክሲ አሽከርካሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የታክሲ አሽከርካሪዎቹ አድማ እንዳልሆነ ቢናገሩም የከተማው የትራፊክ ፖሊስ አስተባባሪ ሃይለስላሴ ተክሉ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የቆመው የትራንስፖርት አገልግሎት የታክሲ ባለቤቶች እና የአሽከርካሪዎች አድማ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ከማህበሩ አባላት ጋር በቅርበት ተነጋግረናል፣ ታሪፉ ያንሰናል። የተሻሻለው የቅጣት ደንቡ ከብዶብናል ሲሉ ጥያቄዎችን አንስተው ከበደም ቀለለም ህን እንጥሳለን አይባልም፣ ‘ህግ ይከበር’ የሚል ምላሽ ሰጥተናል። እነሱ ግን ታሪፉም ይጨመር። ትርፍም እንጫን” ሲሉም ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ኃላፊውም አክለው “ማህበረሰቡ እየተንገላታ፣ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት ሳይሄዱ እየተጉላሉ ባሉበት ሁኔታ፣ የተራበ ማህበረሰብ ላይ ከታሪፍ በላይ እናስከፍላለን የሚሉበት ሁኔታ ሊያስቡበት ይገባል” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

መንግሥት የትራንስፖንቱን አገልግሎት ያስቆሙት አካላት በቅጣት ስራ እንዲጀምሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በአሁኑ ወቅት ስራ አቁመው ያሉ ታክሲዎች የትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ሄደው የተጣለባቸውን ቅጣት ከፍለው ማስረጃ ይዘው ከመጡ በኋላ ብቻ ስራ መጀመር የሚችሉት ሲሉም ኃላፊው አክለዋል።