አነጋጋሪ በሆነው የኬንያ የእምነት ቡድን በርካታ ህጻናት በረሃብ እንዲሞቱ መደረጋቸው ተነገረ

በርካታ ሰዎች ለሞት በተዳረጉበት የኬንያው የእምነት ቡድን ውስጥ መጀመሪያ ላይ ህጻናት በረሃብ እንዲሞቱ መደረጋቸውን አዲስ የወጣ ምስክርነት አጋለጠ።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የእምነቱ ተከታዮች ሞተውበታል በተባለው በዚህ የእምነት ቡድን መገኛ ዋነኛ ስፍራ ላይ በተደረገ የፖሊስ ምርመራ አስካሁም 201 አስከሬኖች በቁፋሮ መውጣታቸው ተገልጿል።

የቡድኑ የቀድሞ ምክትል ሰባኪ የነበረው ግለሰብ ለኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እንደተናገረው ህጻናት “ፀሐይ ላይ ሆነው ምንም ምግብ እንዳይቀምሱ በማድረግ በቶሎ እንዲሞቱ” ተትተው መጀመሪያ ላይ መሞታቸውን ገልጿል።

ታይተስ ካታና የተባለው ግለሰብ በሰጠው ምስክርነት ከህጻናቱ ቀጥሎ ሴቶች እና ወንዶች እራሳቸውን በማስራብ እንዲገድሉ እንደተደረገ የእምነቱን እራስን የማጥፋት ዕቅድን ይፋ አድርጓል።

ፖሊስ እያደረገ ያለውን ምርመራ እያገዘ የሚገኘው ይኸው ግለሰብ፣ ህጻናት ምንም አይነት ምግብም ሆነ ውሃ ሳይሰጣቸው በጎጆ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው እንዲቆዩ ተደርገው የጭካኔ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው ለሰንዴይ ታይምስ ጋዜጣ ተናግሯል።

“ከዚያም ሲሞቱ እና አንዳንዶቹም ነፍሳቸው ሳይወጣ ጭምር በብርድ ልብስ እየተጠቀለሉ ተቀብረዋል” በማለት የተፈጸመውን ድርጊት መስክሯል።

በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ በሚገኘው ፓስተር ፖል ማኬንዚ በተባለው ግለሰብ የሚመራው የእምነት ቡድኑ፣ አባላቱ እራሳቸውን አስርበው ከሞቱ በፍጥነት ወደ መንግሥተ ሰማያት እንደሚገቡ እንዲያምኑ እና ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተገደዋል ተብሏል።

ኪሊፊ በሚባለው የኬንያ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ ግዛት ውስጥ ሻካሆላ ተብሎ በሚታወቀው በጣም ሰፊ ጫካ ውስጥ ተቀብረው በተገኙ አስከሬኖች ላይ ባለሥልጣናት ባስደረጉት የአስከሬን ምርመራ፣ ሟቾቹ ላይ የረሃብ፣ የመታፈን እና የድብደባ ምልክቶች እንደተገኘባቸው አመልክቷል።

በፓስተር ፖሊ ማኬንዚ በሚመራው የምጽአት ቀን የእምነት ቡድን ውስጥ አባል የነበሩ ከ600 በላይ ሰዎች አስካሁን የደረሱበት እንዳልታወቀ ተዘግቧል።

የእምነት ቡድኑ መሪ ፓስተር ማኬንዚ ግን ይመራው የነበረው ‘ጉድ ኒውስ ኢንተርናሽናል ቸርች’ ለ20 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ካገለገለ በኋላ ከአራት ዓመት በፊት መዘጋቱን ገልጿል።

ነገር ግን ቢቢሲ ባደረገው ምርመራ ቤተ ክርስቲያኑ ተዘጋ ከተባለ በኋላ የተካሄዱ የእምነት ሥነ ሥርዓቶችን የሚያሳዩ አንዳንድ ቪዲዮዎችን በበይነ መረብ ላይ ለማግኘት ችሏል።

ከሳምንታት በፊት ፓስተር ማኬንዚ ‘ዴይሊ ኔሽን’ ከተባለው የኬንያ ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ ተከታዮቹን እራሳቸውን አስርበው እንዲሞቱ አስገድዷል መባሉን አስተባብሏል።

ነገር ግን ፓስተር ማኬንዚ “ከእግዚአብሔር ተገልጦልኛል” በማለት ትምህርት መማር ሰይጣናዊ ነው በማለት ይሰብክ እንደነበረ ምክትሉ የነበረው ታይተስ ካታና ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግሯል።

ፖሊስ እያደረገ ባለው ምርመራ ላይ እገዛ እያደረገ ያለው ካታና ከእምነት ቡድኑ ሊወጣ የቻለው፣ የፓስተር ማኬነዚ ትምህርቶች “በጣም ወጣ እያሉ በመምጣታቸው” መሆኑን አመልክቷል።

ፓስተሩ በተጨማሪም ነፍሰጡር እናቶች መውለጃቸው ሲቃረብ የሐኪሞች ድጋፍ እንደማያስፈልጋቸው እና ልጆቻቸውንም ማስከተብ እንደሌለባቸው ያበረታታቸው ነበር ተብሏል።

አብዛኛው የፓስተር ማኬንዚ ስበከቶች በመጽሐፍ ቅዱሳዊው የምጽአት ቀን ትንቢቶች እንዲሁም ከዓለም ፍጻሜ እና ከሳይንስ አደገኝነት ጋር የተዛመዱ እንደነበሩ የእምነት ቡድኑ በበይነ መረብ ላይ ያሰራጫቸው ይዘቶች ያመለክታሉ።

በተጨማሪም ሁሉንም መጥፎ ነገሮች የሚያደረግ ሰይጣናዊ ኃይል በዓለም ከፍተኛ የሥልጣን ቦታዎች ላይ ሁሉ መግባቱን በተደጋጋሚ ለተከታዮቹ ያስጠነቅቅ ነበር።