ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከደሴ - አዲስ አበባ መስመር የመንገደኞችና የአሽከርካሪዎች እንግልት መፍትሔው ምን ይሆን?
ከደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ ፣ ዋግ ኸምራና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ተነስተው በደሴ - አዲስ አበባ መንገድ ወደ ዋና ከተማዋ የሚጓዙ መንገደኞች እና አሽከርካሪዎች ለሳምንታት እንግልትና መጉላላት እየደረሰባቸው እንደሆነ ተናገሩ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው መንገደኞችና አሽከርካሪዎች እንደሚሉት ረጅም ርቀት አቆራርጠው ወደ አዲስ አበባ መዳረሻ ወደሆነውና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኘው፣ ሰሜን ሸዋ ዞን ሲደርሱ ኬላ ላይ ባሉ የፀጥታ አካላት እንግልትና፣ መጉላላት ይደርስባቸዋል።
ከመጉላላት ባለፈም የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችና ሚኒባሶች ተሳፋሪያቸውን ይዘው ወደ መጡበት ለመመለስ እንደሚገደዱም ይናገራሉ።
“ምክንያቱን በምንጠይቅበት ጊዜም የሚሰጠን የተለያየ ምላሽ ነው” ይላሉ።
በዚህ መጉላላት በርካቶች ከሥራ ቅጥር ፈተና፣ ከሕክምና ቀጠሮ፣ ከሥራ፣ ከዘመድ የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ ከሠርግና ከሌሎች ማኅበራዊ ክንውኖች ተስተጓጉለዋል።
“ሕጻናት፣ እናቶች፣ አረጋውያን፣ ሕሙማን ያሰቡበት ሳይደርሱ በክረምት ዝናብ መሀል መንገድ ላይ ሲንገላቱ ማየት ያሳዝናል” ይላሉ መንገደኞቹ።
ከወራት በላይ እንደዘለቀና ባለፉት ቀናት እንደተባባሰ በተነገረው በዚህ መንገደኞችን የማንገላታትና በአሽከርካሪዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሚጣልን ቅጣትን ተከትሎ ችግሩ እልባት እስከሚያገኝ በሚል ከትናንት በስቲያ ነሐሴ 4/2014 ዓ.ም ደብረ ብርሃን ከተማ ላይ መንገድ ተዘግቶ እንደነበር የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ሠላምና ፀጥታ መመሪያ ምክትል ኃላፊ ሰለሞን አልታየ፤ ሸኖ፣ ለገጣፎ እና አለልቱ ውስጥ ባሉ ኬላዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች መታወቂያ እያዩ “ፀጉረ ልውጥ” ይገባል በሚል ተጓዦች ለእንግልት ሲዳረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ይህንንም ለሚመለከተው አካል ሪፖርት አድርገው ሁለቱ ክልሎች እንዲሁም ተጎራባቾቹ ዞኖች በመነጋጋር ችግሩን ለመፍታት ጥረት ቢደረግም መፍትሔ ሳያገኝ ቆይቷል ብለዋል።
“አንድ ቀን ሰላም ሆነ ሲባል ሌላ ቀን ያው ድርጊት ሲፈፀም ይስተዋላል። በየዕለቱ እስከ ሦስት አውቶብሶች ከመንገድ የሚመለሱበት አጋጣሚዎች አሉ። በተለይ ባለፉት ቀናት ተባብሶ ነበር።”
ምክትል ኃላፊው ጨምረውም የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ከሚመለከተው የፌደራል መንግሥት አካል ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ረቡዕ፣ ነሐሴ 4/2014 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ መንገዱ ክፍት መደረጉን ተናግረዋል።
መንገደኞቹም የአዲስ አበባ መታወቂያ የሌለው ሰው አያልፍም እንደሚባሉና አሽከርካሪዎች ያለምንም ጥፋት ቅጣት እንደሚጣልባቸው፣ “ለምን?” ሲሉ ደፈር ብለው የጠየቁም ድብደባ እንደደረሰባቸው አቤቱታ እንደቀረበላቸው ምክትል ኃላፊው ጠቅሰዋል።
ድርጊቱን የሚፈፅሙት ኬላ ላይ ያሉ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል አባላትና የአካባቢዎቹ ሚሊሻዎች እንደሆኑ መረጃ እንዳላቸውም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
ባለፉት ሳምንታት መንገድ ላይ ሰልፍ ይዘው የቆሙ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች እና ተሳፋሪዎች አውራ ጎዳናዎች ላይ ተኮልኩለው የሚያሳዩ ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች በስፋት ተጋርተዋል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሠላማዊ ካሳ ባለፈው ሳምንት ስለጉዳዩ በሰጡት ምላሽ፣ በህወሓት ተይዘው ከነበሩ የአማራ ክልል አካባቢዎች መታወቂያ ለመስራት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ተለያዩ ሰነዶች መያዛቸውን ጠቅሰው፣ ጉዳዩ ከጥብቅ የፀጥታ ቁጥጥር ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አፈጻጸሙ ላይ ማሻሻያዎች መደረግ እንዳለባቸውና የደኅንነት እና የፀጥታ መዋቅሩን ማጥራት እንደሚያስፈልግ ሚኒስትር ዲኤታዋ አክለዋል።
ቢቢሲ የኦሮሚያ ፖሊስ ም/ኮሚሽነር እና የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ጌታቸው ኢታናን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ቢሞክርም መረጃ ለመስጠት እንደማይመቻቸው ገልጸው ስልክ ዘግተዋል።
ከዚህም ባሻገር የሸኖ ቅምብቢት ወረዳ አስተዳዳሪ እና የኮሙኒኬሽን ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም።
በመንገደኞች ላይ የደረሰ መጉላላት
ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ የክልሎች ሻምፒዮና ውድድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ሐዋሳ ለመጓዝ ከደሴ ተነስቶ የነበረው ወጣት በአካል ታምሩ፣ እሱን ጨምሮ ሌሎች በአውቶብሱ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ ግለሰቦች ለእንግልት ተዳርገው እንደነበር ያስታውሳል።
በአካል ሰንደፋ እና ከዚያ አልፎ ባሉ ኬላዎች መታወቂያ ሲጠየቁ እንደነበር ገልጾ፣ “ሰንዳፋ ስንደርስ ግን የአማራ ክልል መታወቂያ ሲያዩ አስወረዱን” ይላል።
“ለውድድሩ የምንሄደው በቁጥር ወደ 25 እንሆናለን። እኛን ‘ወጣት አያልፍም’ አሉን። ነገር ግን አብረውን የተሳፈሩ በእድሜ የገፉ የሃይማኖት አባቶች፣ ሕጻናት፣ ሴቶችም ነበሩ” ሲል ወጣት በመሆን አለመሆን ሳይሆን የአማራ ክልል መታወቂያ መሆኑን አይተው እንዳስወረዷቸው ይናገራል።
በአካል እንደሚለው ሰንዳፋ ላይ ለአራት ሰዓታት ከተጉላሉ በኋላ ወደ ክልል ስልክ ደውለው፣ ከክልል እስከ እግር ኳስ ፌደሬሽን በተደረገ የስልክ ምልልስ እነርሱ ማለፍ ችለዋል።
በወቅቱ ከፀጥታ አካላቱ የተሰጣቸው ምክንያትም “የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል ውስጥ ደሴ ገብተው ስለነበር እና ቆቦም በርካታ ተፈናቃዮች ስላሉ ‘አማራ’ የሚል መታወቂያ እያሰሩ ወደ አዲስ አበባ ስለሚገቡ ለቁጥጥር ነው” የሚል እንደሆነም ወጣቱ አክሏል።
ሌላኛው ያነጋገርነው በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት በአሽከርካሪነት የሚሰራው መሐመድ ሰይድ፣ ከአንድ ወር ገደማ በፊት ለሥራ ካቀናበት ደሴ ከተማ ሲመለስ የሰዎችን የከፋ እንግልት መመልከቱን ይናገራል።
“በአብዛኛው ትኩረት የሚያደርጉት በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች እና ሚኒባሶች ላይ ነው” የሚለው አሽከርካሪው፣ ሥራ ለመቀጠር የጽሑፍ ፈተና አልፈው ለቃለ መጠይቅ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የነበሩ ወጣቶች እንዳሳፍራቸው ተማጽነውኝ ነበር ይላል።
እርሱ እንደሚለው ለመተባበር ቢሞክርም የፀጥታ ኃይሎቹ ሳይፈቅዱለት ቆይተው፣ከብዙ ልመና በኋላ አንደኛውን ማሳፈር ችሏል።
የአዲስ አበባ መታወቂያ የያዙና ከፀጥታ ኃይል አባላት ጋር ተነጋግረው ጉቦ የሚሰጡም ያለምንም ችግር ሲያልፉ መታዘቡንም አክሏል።
የአንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ድርጅት አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ኩራባቸው ታደሰ በበኩላቸው በተለይ ከአንድ ወር ወዲህ ተሽከርካሪዎቻቸው በተለያየ ጊዜ መንገድ ላይ ለሰዓታት እንዲቆሙ እና በአንድ ቀን አዲስ አበባ መግባት የነበረባቸው ደብረ ብርሃን ላይ ለማደር መገደዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህም ተሳፋሪውን ለእንግልትና ለአላስፈላጊ ተጨማሪ ወጪ እንዲሁም ድርጅቱን ለኪሳራ ዳርጓል ይላሉ።
ከትናንት በስቲያ [ነሐሴ 4/ 2014 ዓ.ም] ሙሉ በሙሉ መንገድ ዝግ ስለነበረም የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶቻቸው ደብረ ብርሃን ከተማ ለማደር መገደዳቸውን አስረድተዋል።
“በደሴ መስመር በተደጋጋሚ እንዲህ ዓይነት ነገር እየገጠመን ነው። መንገደኞች እጅግ እየተሰቃዩ ነው። የውጪ አገር በረራ ያለው፣ የሕክምና ቀጠሮ ያለው፣ የመድረሻ ገንዘብ ብቻ ይዘው ሚወጡ ሰዎች ካሰቡበት ሳይደርሱ ሜዳ ላይ እየቀሩ ነው” ይላሉ።
ለችግሩ መፍትሔ
በአማራ ክልል፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ሠላምና ፀጥታ መምሪያ ምክትል ኃላፊ፣ በአገሪቱ ከነበረው ሁኔታ ጋር ተያይዞ መስመሩ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያስፈልገው እንደሚያምኑ ገልጸው፤ “ነገር ግን ያለው የፀጥታ መዋቅር የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት ሳይጥስ፣ ሕጋዊ መታወቂያ የያዘን ሰው ለይቶ ማገልገል ግዴታው ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
ምክትል ኃላፊው፣ ከአጎራባቹ የኦሮሚያ ክልል ዞን ጋር በተነጋገሩበት ወቅት “እስኪ እናጣራለን። ስለ ጉዳዩ አናውቅም” እንደሚሏቸው ጠቅሰው፣ “የመንግሥትን የፀጥታ ኃይል የደንብ ልብስ ለብሶ የሌሎችን አጀንዳ የሚያስፈጽም ጫፍ የረገጠ የፀጥታ መዋቅር አለ” ሲሉም ይከሳሉ።
አቶ ሰለሞን አክለውም አካባቢዎቹን የሚያስተዳድረው ክልል ችግሩን መፍታት ካልቻለም መንገዱ የፌደራል መንግሥት የሚያስተዳድረው በመሆኑ በፌደራል የፀጥታ ኃይል መጠበቅ አለበት ይላሉ።
የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ድርጅት አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ኩራባቸው በበኩላቸው ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ማድረጋቸውን ገልጸው፣ የመንግሥት አካል መፍትሔ እስከሚሰጥ ድረስ እየጠበቅን ነው ብለዋል።
* ያነጋገርናቸው ግለሰቦች ስም ለድኅንነታቸው ሲባል ተለውጧል።