በሰው ሰራሽ አስተውሎት(ኤአይ) የተሰሩ የሕጻናት እርቃን ምስሎች በስፔን ድንጋጤ ፈጠሩ

በደቡባዊ ስፔን የምትገኘው አልመንድራሌሆ ከተማ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተሰሩ የታዳጊ ሴቶች እርቃን ምስሎች ከእነርሱ እውቅና ውጭ በማኅበራዊ ሚዲያ ከተዘዋወሩ በኋላ ድንጋጤ ውስጥ ገብታለች።

እርቃን ምስሎቹ የተሰሩት ሙሉ ልብስ ለብሰው የተነሱትን የታዳጊዎቹን ፎቶ በመጠቀም ነው።

በርካታ ምስሎቹ የተወሰዱትም ከታዳጊዎቹ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ነው።

ምስሎቹ ከተወሰዱ በኋላም አንድ ግለሰብ እርቃኑን ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ምናባዊ ምስል የሚፈጥር መተግበሪያ በመጠቀም የታዳጊዎቹ ምስል እርቃን እንዲቀር ተደርጓል።

እስካሁን ዕድሜያቸው በ11 እና በ17 ዓመት መካከል የሚገኙ 20 ታዳጊ ሴቶች፣ የዚህ ድርጊት ሰለባ መሆናቸውን በመግለጽ በደቡብ ምዕራብ ግዛቷ ባዳጆዝ ውስጥ በምትገኘው አልመንድራሌሆ ከተማ እና አቅራቢያው ሪፖርት አድርገዋል።

የ14 ዓመቷ ታዳጊ እናት የሆነችው ማሪያ ብላንኮ ራዮ “ አንድ ቀን ልጄ ከትምህርት ቤት ወጥታ እርቃኗን የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተዘዋወሩ እንደሆነ ነገረችኝ” ትላለች።

ልጄን እርቃኗን ፎቶ ተነስታ እንደሆነ ጠየቅኳት የምትለው ማሪያ፣ “ፎቶዎቹ ሐሰተኛ የታዳጊ ሴቶች ምስሎች ናቸው።በምማርበት ክፍል ውስጥም የሌሎች ታዳጊዎች ምስል በተመሳሳይ ተለቋል” ስትል እንደመለሰችላት ተናግራለች።

ማሪያ እንደምትለው የዚህ ሰለባ የሆኑ የ28 ታዳጊዎች ወላጆች በከተማዋ ድጋፍ የሚሰጥ ቡድን አቋቁመዋል።

ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ፖሊስ ድርጊቱን እየመረመረ ሲሆን ምስሎቹን በመፍጠር ሒደት ውስጥ አሊያም በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ዋትስአፕ እና ቴሌግራም በማጋራት ተሳትፈዋል ያላቸውን ቢያንስ አስራ አንድ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ታዳጊ ወንዶችን መለየቱን አስታውቋል።

መርማሪዎች ታዳጊ ወንዶቹ ሐሰተኛ ምስሎችን በመጠቀም ታዳጊ ሴቶቹን በማስፈራራት ማግኘት የፈለጉት ነገር ስለመኖሩ ለማወቅ ምርመራ እያካሄዱ ነው።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩት ሐሰተኛ የእርቃን ምስሎች በታዳጊ ሴቶቹ ላይ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን አሳድረዋል።

ብላንኮ ራዮ የተባለች እናት ልጇ ሁኔታውን መቋቋም መቻሏን ገልጻ፤ ነገር ግን የተወሰኑ ታዳጊዎች ከቤታቸው ለመውጣት እንደተሳቀቁ ተናግራለች።

ጉዳዩ ወደ አደባባይ የወጣው ከታዳጊዎቹ ሴቶች መካከል የአንዷ እናት በሆነችው የማሕጸን ሐኪሟ ማሪያም አል አዲብ ምክንያት ነው።

አዲብ ማኅበራዊ ሚዲያዋን በመጠቀም ባወጣችው መልዕክት ምክንያት ጉዳዩ የስፔን ሕዝብ መነጋጋሪያ መሆን ችሏል።

አዲብ ታዳጊ ሴቶችንና ወላጆችን ለማረጋጋት ስትል በማኅበራዊ ሚዲያ ባጋራችው ቪዲዮ “ ምንም እንኳን የወጡት የኤአይ ምስሎች የተፈጠሩት በበጋ ወቅት ቢሆንም ጉዳዩ ወደ አደባባይ የወጣው በቅርብ ቀናት ነው” ብላለች።

“ምን ያህል ሕጻናት ምስሎቹ እንደነበራቸው አናውቅም። ምስሎቹ የወሲብ ፊልም በሚጫንባቸው ገጾች ላይ ተጭነው እንደሆነም አናውቅም ነበር። ይህ ሁሉ ስጋት ነበረብን” ብላለች።

በዚህ ድርጊት የተጠረጠሩት ታዳጊዎች ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 14 የሚደርስ ነው።

የስፔን ሕግ፣ አዋቂዎችን በሚመለከት ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ምስሎችን ከመፍጠር ጋር በተያያዘ የሚለው ነገር ባይኖርም፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን በመጠቀም እንዲህ ዓይነቱን ምስል መፍጠር የሕጻናት የወሲብ ምስል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ከዚህም በተጨማሪ የግላዊነት ሕግን በመጣስ ሊያስከስስም ይችላል።

በስፔን ውስጥ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ላይ የወንጀል ክስ ሊመሰረት የሚችለውም ከ14 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ነው።

ክስተቱ በጉዳዩ ላይ ያልተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጭምር ስጋትን ፈጥሯል።

የስፔኗ ውብ ከተማ አልመንድራሌሆ ከ30 ሺህ በላይ ሕዝብ ይኖርባታል።

በወይራ እና በቀይ ወይን ምርቷ የምትታወቀው ከተማዋ፣የተፈጠረው ክስተት የሰሞኑ ብሔራዊ ዜና አርዕስት እንድትሆን አድርጓታል።