ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሞ ፋራህ ወደ ዩናትይድ ኪንግደም ስለገባበት ሁኔታ ፖሊስ ምርመራ ሊያደርግ ነው
ታዋቂው አትሌት ሞ ፋራህ ልጅ እያለ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በሕገወጥ መንገድ እንዲገባ መደረጉን ይፋ ካደረገ በኋላ የአገሪቱ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ ማድረግ ጀመረ።
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ፖሊስ ኃይል እንዳለው ሞ ፋራህ በቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ላይ ይፋ ባደረጋቸው መረጃዎች ዙሪያ ልዩ የፖሊስ መኮንኖችን መድቦ ምርመራ አደርጋለሁ ብሏል።
ሞ ልጅ እያለ ሶማሊያ ውስጥ የነበረውን የእስር በርስ ጦርነት ለመሸሽ አገሩን ከለቀቀ በኋላ በሐሰተኛ ስም ወደ ዩኬ መግባቱን ተናግሯል።
አሁን የ39 ዓመት ጎላማሳ የሆነው ሞ፣ በማያውቃት ሴት ወደ ዩኬ ተወስዶ ቤቷ ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት የጉልበት ብዝበዛ እንደተፈጸመበትም ገልጿል። ቀደም ሲል ግን ከቤተሰቦቹ ጋር በስደት መምጣቱን ሲናገር ቆይቷል።
የለንደን ፖሊስ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው “ሰር ሞ ፋራህን በሚመለከት በመገናኛ ብዙኃን ላይ የወጣውን ዘገባ እናውቃለን። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ለፖሊስ ኃይሉ ምንም አይነት የቀረበ ክስ የለም።
“ባለሙያ የሆኑ ልዩ የፖሊስ መኮንኖች በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ ጀምረው የወጡ መረጃዎችን እየገመገሙ ናቸው” ብሏል።
የዓለማችን ኮከብ አትሌት በሆነው ሞ ፋራህ ዙሪያ የተዘጋጀውና ረቡዕ ዕለት የቀረበው ዘጋቢ ፊልም ላይ፣ ፋራህ እንዴት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንደገባ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ከ22 ዓመታት በፊት ያገኘውን ዜግነት ሊያጣ እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።
ነገር ግን የዩናይትድ ኪንግደም የአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ ሞ ወደ አገሪቱ የገባው በልጅነቱ እንደሆነና ዜግነት በማግኘቱ ሂደት በተፈጸመው ማጭበርበር ውስጥ ተሳታፊ ባለመሆኑ ምንም አይነት እርምጃ አይወሰድበትም ብሏል።
በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ሞ ፋራህ ትክክለኛ ስሙ ሁሴን አብዲ ካህን እንደሆነ እና ከሶማሊያ ነጻነቷን ባወጀችው ሶማሊላንድ ውስጥ እንደተወለደ ተናግሯል።
የአራት ዓመት ልጅ ሳለም አባቱ አብዲ በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅት ይካሄድ በነበረው ውጊያ ምክንያት በተባራሪ ጥይት ተመትቶ ተገድሎበታል።
ስምንት ወይም ዘጠኝ ዓመት ሲሆነውም ጂቡቲ ውስጥ ወደ ሚገኙ ቤተሰቦቹ ተወሰደ። ከዚያ በኋላ አይቷት በማያውቃት እና ዝምድና በሌላት ሴት አማካይነት አውሮፓ ውስጥ ከዘመዶቹ ጋር እንደሚኖር ነግራው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ይዛው ሄደች።
እዚያም ከደረሱ በኋላ ሴትየዋ ምዕራብ ለንደን፣ ሆንስሎው ውስጥ ወደ ሚገኝ የመኖሪያ ህንጻዋ ከወሰደችው በኋላ የዘመዶቹን አድራሻ ይዞ የነበረን ወረቀት እንደነጠቀችው ተናግሯል።
አሁን የሚታወቅበት ሞሐመድ ፋራህ የሚለው ስምም የተሰጠው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ባመጡት ሰዎች አማካይነት ነበር።
ሞ በልጅንቱ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከገባ በኋላ ምግብ ለማግኘት ህጻን ልጅ መንከባከብን ጨምሮ የተለያዩ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለመሥራት ይገደደ ነበር።
ወደ ዩኬ የወሰደችው ሴትም “ቤተሰቦችህን ለማየት ከፈለግክ፣ ምንም ነገር ትንፍሽ እንዳትል” ስትል አስጠንቅቃዋለች።
“ዘወትርም መታጠቢያ ቤት ውስጥ ገብቼ በመቆለፍ አለቅስ ነበር” ሲል የነበረበትን ሁኔታ ፋራህ ያስታውሳል።
በትምህርት ቤት በሩጫ መሳተፍ ሲጀምር ለስፖርት መምህሩ ስላለበት ሁኔታ ከነገረው በኋላ፣ የማኅበራዊ አገለግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር በመነጋገር ሌላ ሶማሊያዊ ቤተሰብ በጉዲፈቻ እንዲያሳድገው በማድረግ ከነበረበት ሁኔታ እንዲወጣ ረድቶታል።
የተሳካለት ሯጭ በመሆን ለዩናይትድ ኪንግደም በርካታ ሜዳሊያዎችን ያስገኘው ሞ በአገሪቱ ታላቅ የሆነውን ‘ሰር’ የተባለውን የክብር ማዕረግ አግኝቷል።
ሞ ፋራህ ወደ ዩኬ እንዴት እንደጋባ፣ ስለልጅነቱ እና በአንድ የኦሊምፒክ ውድድር ስላገኛቸው ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ተናግሯል።