ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩክሬኑ ጦርነት ሩሲያ ከሰራዊቷ ይልቅ ሰላዮቿ የበለጠ ውጤታማ እንደሆኑ ተነገረ
በዩክሬኑ ጦርነት ሩሲያ ከጦሯ ይልቅ የደህንነት እና የስለላ አገልግሎቷ የበለጠ ስኬት እንዳስመዘገበ የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ምርምር ተቋም አሳወቀ።
የሩሲያ የስለላ ኤጀንሲዎች ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከአውሮፓውያኑ ሰኔ 2021 ጀምሮ ለወረራው ዝግጅት ያደርጉ እንደነበር ነው የሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት፣ ሩሲ ያስታወቀው።
የሩሲያው የፌደራል ደኅነነት አገልግሎት (ኤፍኤስቢ) በዩክሬን በተያዙ አካባቢዎች ሕዝብን በፍጥነት መቆጣጠር ችሏል ሲል ሩሲ አክሏል።
የዩክሬን የስለላ ባለስልጣናት፣ የተጠለፉ መረጃዎች እንዲሁም መሬት ላይ የተደረጉ ምርመራዎችም በዚህ ሪፖርት ተካትተዋል።
ተመራማሪዎች እንደሚሉት የሩስያው የስለላ ተቋም የመንግሥትን ኮምፒውተሮች በመፈተሽ የዩክሬን ደጋፊ ግለሰቦችን ለመለየት እንዲሁም ለመያዝና ለመመርመር ጥቅም ላይ አውለዋቸዋል ተብሏል።
በተጨማሪም ሩሲያ የተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን ግዛቶችን በመገናኛ ዘርፉ ከዓለም ለማቆራረጥም ይህንን የሚመራ የዲጂታል ጦር ክፍል ተሰማርቶ እንደነበር ነው ሩሲ ያስታወቀው።
የሩሲያ የውጭ መረጃ ድርጅት፣ ኤስቪአር ኃላፊ ለፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወረራውን እንዲያዘገዩትና ለዝግጅትም ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋል ብለዋቸው እንደነበር ተገልጿል። ነገር ግን ጥያቄያቸው ተቀባይነት አላገኘም።
ከአውሮፓውያኑ የካቲት 2022- እስከ የካቲት 2023 ሩሲያ ያደረገችውን የጦርነት ዘመቻ የሰነደው ይህ ሪፖርት 39 ገጾች ያሉት ሲሆን ሩሲያ ኢላማ ባደረገቻት ዩክሬን ምን ያህል የተሰወረ ጥቃት እያደረገች እንደነበር ምዕራባውያን መንግሥታት ለማስጠንቀቅ ያለመ ነው።
የሪፖርቱ ዋና አዘጋጅ ጃክ ዋትሊንግ በቅርቡ ከፍተኛ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለሩስያ አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል ክስ አንድ ከፍተኛ የጀርመን የደኅነት ባለስልጣን መታሰራቸውን አመልክተዋል።
"የሩሲያ የደኅነት አገልግሎት ከወረራው በፊት በዩክሬን ውስጥ ሰፊ የስለላ ኔትወርክ በመዘርጋት ምልመላ ማካሄዱን እንዲሁም ከወረራው በኋላ ለጦሩ ትልቅ ድጋፍ ሰጪ ሆኖ መቀጠሉ ግልጽ ሆኗል። ይህም በደህንነቱ ዘርፍ ለሩሲያ ኃይሎች የማያቋርጥ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል።