በርካታ ኖርዌያውያን በስህተት ሚሊዮኖች በሎተሪ ማሸነፋቸው ከተገለጸ በኋላ ቁጣ ተቀሰቀሰ

በርካታ ኖርዌያውያን ረብጣ ገንዘብ አሸንፋችኋል የሚል መልዕክት በመንግሥት ባለቤትነት ከሚተዳደረው አቋማሪ ኩባንያ ከደረሳቸው በኋላ ሚሊየነር ሆነናል ብለው አስበው ነበር።

ይህ ደስታ ግን አብሯቸው የቆየው ስህተት መሆኑ እስኪታወቅ ድረስ ብቻ ነው።

በዩሮጃክፖት ሽልማቶችን ያሸነፉ "በርካታ ሺህዎች" አርብ ዕለት ላይ የተሳሳተ መጠን የያዘ መልዕክት እንደደረሳቸው ኖርስክ ቲፒንግ አስታውቋል።

ኩባንያው ምን ያህል ሰዎች የተሳሳተ መልዕክት እንደደረሳቸው ለቢቢሲ ከመናገር ተቆጥቧል።

የኖርስክ ቲፒንግ ዋና ኃላፊ ቶንጄ ሳግስቱኤን ስለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ጠይቀው ከአንድ ቀን በኋላ ሥራቸውን ለቅቀዋል።

ኩባንያው ከዩሮሴንት ወደ ኖርዌይ ክሮነር በመቀየር ሂደት በተፈጠረ ስህተት ሽልማቱ "ከመጠን በላይ ከፍተኛ" እንዲሆን አድርጓል ሲል ገልጿል።

ገንዘቡ በ100 ከመካፈል ይልቅ ለ100 ተባዝቷል ሲል የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

ኖርስክ ቲፒንግ የሽልማት መጠኑን ከጀርመን በዩሮ ከተቀበለ በኋላ ወደ ኖርዌይ ክሮነር ይለውጠዋል።

ትክክለኛው የሽልማት መጠን ቅዳሜ ምሽት ላይ ተስተካክሎ ተገልጿል።

አቋማሪ ድርጅቱ ምንም የተሳሳቱ ክፍያዎች አልተፈጸሙም ብሏል።

"ብዙዎችን ስላሳዘነን በጣም አዝኛለሁ፤ ሰዎች በእኛ ላይ መናደዳቸውን ተረድቻለሁ" ብለዋል ሳግስቱኤን በመግለጫቸው "የእምነት ጥሰት" በመሆኑ "ትችታቸው ተገቢ ነው" ብለዋል።

ለመዝናናት ወጣ ለማለት ያቀዱ፣ ቤታቸውን ለማደስ ወይም አፓርታማ ለመግዛት ካሰቡ ሰዎች በርካታ መልዕክቶች እንደደረሷቸውም ተናግረዋል።

"ለእነርሱ ማለት የምፈልገው ይቅርታ ነው! ይህ ትንሽ ማጽናኛ እንደሆነ እረዳለሁ" ብለዋል።

አንዲት ቤቷን ለማሳደስ እያቀደች የነበረች ለኖርዌይ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኤንአርኬ) 1.2 ሚሊዮን ክሮነር (119,000 ዶላር) ማሸነፏን የሚገልጽ መልዕክት እንደደረሳት ገልጻ፣ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ከተጠቀሰው ገንዘብ የተወሰነውን ብቻ ማግኘቷን ተናግራለች።

የኖርስክ ቲፒንግ ቦርድ ቅዳሜ ዕለት የኩባንያውን ሥራ ከሚቆጣጠረው ከባሕል ሚኒስቴር ጋር ለአስቸኳይ ስብሰባ ተገናኝቶ ነበር።

ከስብሰባው በኋላ ሳግስቱኤን ከዋና ኃላፊነታቸው ተነስተዋል። ኃላፊዋ በዚህ ሥልጣን ላይ ከመስከረም 2023 ጀምሮ የሠሩ ሲሆን ከ2014 ጀምሮ በኖርስክ ቲፒንግ ውስጥ አገልግለዋል።

"እዚህ፣ ነገሮች በተለያዩ ቦታዎች ተበላሽተዋል፤ ይህ ደግሞ የእኔ ኃላፊነት ነው" ብለዋል።

ከሥራ በመልቀቃቸው "አዝኛለሁ" ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን በተደረጉት "የማሻሻያ ለውጦች" እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።

የባህል እና የእኩልነት ሚኒስትር ሉብና ጃፈርይ ለኤንአርኬ እንደተናገሩት "እንደዚህ ዓይነት ስህተቶች መከሰት አልነበረባቸውም" በተለይም ኖርስክ ቲፒንግ በአገሪቱ ውስጥ የጨዋታ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ልዩ መብት የተሰጠው ኩባንያ ነው።

"ቦርዱ የቁጥጥር አሠራሮችን ለማሻሻል በትጋት እንዲሠራ እንጠብቃለን" ብለዋል።

ኖርስክ ቲፒንግ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ራሱን ሲያገኝ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከቅርብ ወራት ወዲህ "በርካታ ከባድ ስህተቶች ተገኝተዋል" እንዲሁም "ባለፈው ዓመት በርካታ የቴክኒክ ችግሮች አጋጥመዋል" ብሏል ኩባንያው።

በተቆጣጣሪው እና በደንበኞቹ "ከባድ ትችት" እንደቀረበበት ገልጾ፣ ትችቱ "ተገቢ ነበር" ሲል አምኗል።