ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት አስመልክቶ ግብፅ የሰጠችውን መግለጫ ተቃወመች

ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት በተመለከተ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ ላይ ቅሬታዋን ገለጸች።

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ነው “የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከቱርክ አቻቸው ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት በሰጡት አስተያየት የተሰማውን ቅሬታ” ገልጿል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ በዚህ መግለጫቸው “የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጎዳ ማንኛውንም ድርጊት በጽኑ እንቃወማለን” ማለታቸው ተዘግቧል።

ሚኒስትሩ ይህንን መግለጫ የሰጡት ከቱርኩ አቻቸው ሃካን ፊዳን ጋር ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም ሲሆን ይህን ንግግር ተከትሎ ነው ሶማሊላንድ ቁጣዋን የገለጸችው።

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ረቡዕ ነሐሴ 1/2016 ዓ.ም. ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ “በሶማሊላንድ ሪፐብሊክ እና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን የመግባቢያ ስምምነት በተመለከተ የተነገሩት መግለጫዎች የተሳሳቱ፣ አሳሳች እና የሕዝባችንን ሉዓላዊ መብቶች ያላከበሩ ናቸው” ሲል ቁጣውን ገልጿል።

የሶማሊላንድ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ለተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት “ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት በድጋሚ ይገልፃል” ያለው መግለጫው፤ “ስምምነቱ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የጋራ ጥቅም እና መከባበርን የሚያንፀባርቅ ነው። ይህንን አጋርነት እንደ ቀጠናዊ መረጋጋት እና የኢኮኖሚ ትብብር መሠረት ነው የምንመለከተው” ሲል አክሏል።

የሶማሊላንድ ሕዝብ እ.ኤ.አ በ1991 የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱን ተጠቅሞ የሶማሊላንድ ሪፐብሊክን መመሥረቱን ያስታወሰው መግለጫው፤ “ሶማሊላንድ በሞቃዲሾ አስተዳደር አካል አለመሆኗን እና ሆናም እንደማታውቅ ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው” ብሏል።

“የግብፅ መንግሥት የሶማሊላንድ ሪፐብሊክን ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት እንዲያከብር እንጠይቃለን” ያለችው ሶማሊላንድ “የግብፅ መንግሥት ጉልበቱን እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱን በድንበሩ ዙሪያ ባሉ እንደ ሊቢያ፣ ሱዳን፣ ፍልስጤም እና ሊባኖስ ባሉ ቀውሶች ላይ እንዲያተኩር” ጠይቃለች።

ሶማሊላንድ ከስምንት ወራት በፊት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ የአካባቢውን ፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ከትቶት ቆይቷል።

ሶማሊላንድን እንደራሷ ግዛት የምትመለከተው ሶማሊያ በበኩሏ ከዚህ ስምምነት መፈረም ሰባት ወራት በኋላ ከግብፅ እና ከቱርክ ጋር የተለያዩ ወታደራዊ ስምምነቶችን አድርጋለች።

በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የቱርክ መንግሥት ሲሠራ መቆየቱ ይታወሳል። የሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በቱርክ አማካይነት ንግግር ያደረጉ ቢሆንም ከስምምነት ሳይደረስ ሌላ ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

ከውይይቱ ማብቃት በኋላ የሁለቱም አገራት ተወካዮች በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ሁለቱ አገራት መልካም ጉርብትናን እና ቀጠናዊ መረጋጋትን ከግምት በማስገባት መፍትሄዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክክሮችን ለመቀጠል መስማማታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ሚኒስትሮቹ ለሁለተኛ ዙር ውይይት በአንካራ ነሐሴ 27/ 2016 ዓ.ም እንደሚገናኙ ተገልጾ ነበር።

ከዚህ ምክክር አንድ ወር በኋላ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን ለይፋዊ ሥራ ጉብኝነት አዲስ አበባ እና ካይሮ ተገኝተው ነበር።

ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር መተላለፊያ ለመስጠት በምላሹ ደግሞ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅናን ለመስጠት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።

ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ ባለፈው ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ከሶማሊያ በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል።

በዚህም በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ግንኙት የሻከረ ሲሆን፣ ሶማሊያ ኢትዮጵያን ሉዓላዊነቷን በመጣስ ትከሳለች።