ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
70 ሺህ የሚሆኑ ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን አሜሪካ ሄደው ጥገኝነት ለመጠየቅ ፍላጎት አላቸው
70 ሺህ ገደማ የሚሆኑ ደቡብ አፍሪካዊያን ከዋሺንግተን በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት ወደ አሜሪካ ማቅናት ይፈልጋሉ ሲል አንድ የቢዝነስ ቡድን አስታወቀ።
በአሜሪካ የደቡብ አፍሪካ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ (ሳኩሳ) የተባለው ድርጅት በድረ-ገፁ አማካኝነት በአስር ሺህ የሚቆጠሩ አፍሪካነር የሚባሉ ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን ምዝገባ እያደረጉ እንደሆነ ገልጿል።
ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው የካቲት ባወጡት መመሪያ አፍሪካነር የሚባሉት ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን ወደ አሜሪካ መጥተው ጥገኝነት መጠየቅ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
አፍሪካነሮች በ17ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ደቡብ አፍሪካ ከመጡ የደች ሰዎች ዘራቸው የሚመዘዝ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ በወርሀ ጥር ሥልጣን ከጨበጡ ወዲህ በደቡብ አፍሪካ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል።
ትራምፕ ነጭ ደቡብ አፍሪካዊያን "ፍትሐዊ ያልሆነ የዘር መድልዎ ተጠቂ ናቸው" ይላሉ።
ሳኩሳ "ወሳኝ እርምጃ" ባለው ሂደት ወደ አሜሪካ መሄድ የሚፈልጉ ደቡብ አፍሪካውያንን ስም ዝርዝር ፕሪቶሪያ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አስረክቧል።
የኤምባሲው ባለሥልጣን የሆኑ ግለሰብ የስም ዝርዝር መቀበላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የሳኩሳ ድረ-ገፅ ላይ ከተመዘገቡ 67 ሺህ 42 ሰዎች መካከል አብዛኛዎች የአፍሪካነር አሊያም የእንግሊዝ ስም ያላቸው ናቸው ይላሉ የድርጅቱ ፕሬዝደንት ዲል ዳይመንድ።
አሜሪካ የሚኖሩ የደቡብ አፍሪካ የቢዝነስ ሰዎችን የሚወክለው ሳኩሳ እንደሚለው አብዛኛዎቹ ወደ አሜሪካ ለማቅናት ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች ዕድሜያቸው ከ25-45 የሆኑ እና ሁለት እና ሶስት ቤተሰብ ያላቸው ናቸው።
ይህ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገ ድርጅት ኦፊሴላዊ የመንግሥት ተቋም ባይሆንም በርካታ ሰዎች ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው ምዝገባ የጀመረው ይላሉ ዳይመንድ።
አንዳንድ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያን መድልዎ እየደረሰባቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ቅሬታ አሜሪካ የሚገኙ ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞችን ቀልብ የሳበ ሆኗል።
በደቡብ አፍሪካ አነስተኛ ቁጥር ያለው ጎሳ የሆኑት ነጭ ዜጎች የሀገሪቱን አብዛኛውን የግል መሬት ይዘዋል።
ደቡብ አፍሪካ ከዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት ነፃ ከወጣች ከ30 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።
የአሜሪካና በደቡብ አፍሪካ ግንኙነት መሻከር የጀመረው፤ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ መንግሥት ያለምንም ካሳ መሬት ከግል ባለሀብቶች መውሰድ ይችላል የሚል ሕግ ማፅደቃቸውን ተከትሎ ነው ።
ሕጉ ተግባራዊ የሆነው ለዓመታት ነጭ አናሳ ጎሳ ደቡብ አፍሪካዊያን ያላቸውን ሰፊ የእርሻ መሬት እንዲያካፍሉ ሲጠየቅ ከከረመ በኋላ ነው።
"በአሁኑ ወቅት ለመኖር አስቸጋሪ የሆነ ቦታ" ሲሉ ደቡብ አፍሪካን የነቀፉት ትራምፕ አፍሪካነሮች በጥገኝነት ወደ አሜሪካ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፈው ወር ትራምፕ ሀገራቸው ለደቡብ አፍሪካ የምታደርገውን ድጋፍ አቋርጠዋል።
ራማፎሳ የመሬት ሕጉ "በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይተገበራል" ብለው መንግሥት እስካሁን ምንም ዓይነት መሬት እንዳልነጠቀ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት አሜሪካ በዋሺንግተን የደቡብ አፍሪካ አምባሳደርን ከሀገሯ ማባረሯ ይታወሳል።