ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ በቅርቡ ያባረረቻቸው የደቡብ አፍሪካው አምባሳደር ማን ናቸው?
አምባሳደር ኢብራሂም ራሱል የሰውን ልጅ ከሰብዓዊነት ማማ ያወረደውን ጨቋኙን የደቡብ አፍሪካን አፓርታይድን ስርዓት የታገሉ ናቸው።
የአናሳ ነጮች አገዛዝ የሆነው ስርዓትንም መታገል ብቻ ሳይሆን እሳቸውም ተጠቂ ናቸው።
የፖለቲካ ህይወታቸው የአፓርታይድን ስርዓት በመታገል የሚቀዳው አምባሳደሩ የትራምፕን አስተዳደር ከመተቸት ወደ ኋላ አላሉም።
አስተዳደሩን በሰላ በመተቻተው "ጸረ አሜሪካ" በሚል ተፈርጀው ከአገር ቢባረሩም ዲፕሎማቱ በተረጋጋ መልኩ ነው ለቤተሰቦቻቸው እና ለጓደኞቻቸው መልዕክት የላኩት።
"ሻንጣችንን ሸክፈናል እና ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመመለስ ዝግጁ ነን" ያሉት አምባሳደሩ አክለውም "ያለምንም ጸጸት" አሜሪካን ለቀው እንደሚሄዱ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር እሳጣ ገባ ያስገባቸው ከዚያ ቀደም ብሎ አንድ የደቡብ አፍሪካ ቲንክ ታንክ ያዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ላይ የሰጡት አስተያየት ነው።
የ62 ዓመቱ ዲፕሎማት የዶናልድ ትራምፕን ፖሊሲ እንዲሁም በአህጉሪቷ ላይ ስለሚኖረው አንድምታ ትንታኔያቸውን ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ የሰጡት አስተያየት ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ያጸደቀችው የመሬት ፖሊሲ በተወሰኑ "ማኅበሰረሰቦች" ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ለአገሪቱ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጣቸውን ተከትሎ በአገራቱ መካከል ውዝግብ መነሳቱን ተከትሎ ነው።
ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ የአፓርታድ ስርዓት ከ30 ዓመታት በፊት ብትላቀቅም አሁንም አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬቶች አነስተኛ በሆኑት ነጮች እንደተያዘ ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የመሬት ባለቤትነት በአገሪቱ አከራካሪ እና አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ የቆየ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የጸደቀው የመሬት ፖሊሲ ይህንን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ያለመ ነው ተብሏል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአንዳንድ ሁኔታዎች ያለ ካሳ መሬት መውረስ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ እንዲሆን ፈርመዋል። የአሜሪካ መንግሥት በደቡብ አፍሪካ አናሳ ነጮች ኢ-ፍትሃዊነት እየተፈጸመባቸው ነው ሲል ከሷል።
አምባሳደር ራሱል በበኩላቸው ትራምፕ "የበላይነትን ለማስፈን እየሞከሩ ነው" ብለዋቸዋል።
አክለውም በአሜሪካ ነጮች አናሳ የመሆናቸው አዝማማሚያ መታየቱን ተከትሎ "ነጮችን ተጠቂ አድርጎ በመሳል ለማስጮህ እየሞከሩ ነው" ብለዋቸዋል።
አምባሳደሩ የሰጡት አስተያየት የዲፕሎማሲውን "መስመር" ያለፈ ነው ወይ በሚል በአሜሪካ እንዲሁም በአለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው "አሜሪካን የሚጠላ ዘር ላይ የሚያተኩር ፖለቲከኛ" ብለው ከፈረጇቸው በኋላ፤ በአገሪቱ ተቀባይነት የላቸውም ሲሉ ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጽህፈት ቤት በበኩሉ አሜሪካ የአምባሳደሩን የማባረር ውሳኔ "የሚያሳዝን" ብሎታል።
አምባሳደሩ ከመባረራቸው በፊት የሁለቱን አገራት ግንኙነት በማሻሻል ረገድ "ጥሩ እመርታ አሳይተዋል" ሲሉ ራማፎሳ ደግፈዋቸዋል።
ራማፎሳ "ይህ ለማስተካከል እየሞከርነው ያለው መሰናክል ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
ሆኖም አንዳንድ ባለስልጣኖቻቸው "ዲፕሎማቶች ማለፍ የሌለባቸውን መስመር ተሻግረዋል" ሲሉ መተቸታቸውን የደቡብ አፍሪካው ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ አስነብቧል።
የአሜሪካ የሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ጂም ሪሽ የአምባሳደሩን "አጸያፊ" አስተያየት አውግዘዋል ያሏቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አወድሰዋል።
ሆኖም የዋይት ሃውስ ፖሊሲዎችን እንዲህ መተቸታቸው አምባሳደሩን በሚያውቁ ደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ ግርምት አልፈጠረም።
በአፓርታይድ ስርዓት ያደጉት ራሱል በከተማዋ ማዕከል ከነበረው መኖሪያ ቤታቸው በዘረኛው ስርዓት እንዲወጡ የተገደዱት ገና ልጅ እያሉ ነው።
መኖሪያ ስፍራዎችን ዘርን መሰረት ባደረገ ዞን የከፋፈለው አፓርታይድ ነጭ ያልሆኑ ደቡብ አፍሪካውያን መሰረተ ልማቶቻቸው ባልተሟሉ ስፍራዎች በከፋ ሁኔታ እንዲኖሩ ያደርጉ ነበር።
ራሱል እና ቤተሰቦቻቸውም ማዕከላዊ ኬፕታውን ከሚገኘው ቤታቸው እንዲወጡ እና ራቅ ወዳለ ስፍራ እንዲሄዱ ተደረጉ።
የራሱል ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የጀመረው ትምህርት ቤት እያሉ በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ነው።
"የመጀመሪያ አስለቃሽ ጭስ እስክቀምስ፣ ጥይት እስካይ፣ ሁለተኛ ደረጃ ገብቼ በፖሊስ ዱላ ተመትቼ እስክሸሽ ድረስ ምን እያደረግኩ እንደነበር አላውቅም ነበር" ማለታቸውን በአውሮፓውያኑ 2015 አምባሳደሩን ዋቢ አድርጎ የጆርጅ ታውን ዩኒቨርስቲ አስፍሯል።
"ይሄ ተሞክሮ ህይወቴን ቀየረው። በፖለቲካ ላይ በአቋራጭ ትምህርት የሰጠኝ ነበር" ብለዋል።
ይህንን ትግላቸውን ዝም ብሎ ያላየው የአናሳ ነጮች ዘረኛ ስርዓት ኬፕታውን አቅራቢያ እስር ቤት አስገባቸው። በዚህ ወቅት ከሌላኛው የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ጋር ተገናኝተው ነበር።
ራሱል በገዢው ፓርቲ የአፍሪካ ናሺናል ኮንግረስ በተለያዩ የስልጣን ቦታዎች አገልግለዋል።
ከዚያም ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ስልጣን ላይ ከመጡ በኋላ ከአውሮፓውያኑ 2010-2015 ድረስ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ።
አምባሳደሩ ከዚህ ቀደም ባላቸው ልምድ እንዲሁም ከዋሽንግተን ጋር ባላቸው ሰፋ ያለ ግንኙነት ድጋሚ በአውሮፓውያኑ 2024 አምባሳደር እንዲሆኑ ተሾመዋል።
ራሱልን ከአፓርታይድ ትግል ጀምሮ እንዲሁም በኤኤንሲ ፓርቲ የሚያውቋቸው ፋይዝ ጃኮብስ አምባሳደሩን ውዝግብ ውስጥ የከተታቸውን አስተያየት ደግፈዋል።
ይህንን ውዝግብ ያስነሳውን የበይነ መረቡን ዝግጅት የተከታተሉት ጃኮብስ፣ አምባሳደሩ በአሜሪካ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ትንታኔ እንዲሰጡ ተጠይቀው "ተጨባጭ እና አካዳሚያዊ" ገለጻ አድርገዋል ይላሉ።
ዲፕሎማቱ የሚያምኑበት አመለካከታቸውን ቢያንጸባርቁም፤ እንዲሁም ችግር ለመፍጠር ባይሞክሩም እንዲህ አይነት ውዝግብ የተነሳባቸው በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ነው ይላሉ።
"እሱ ሙስሊም መሆኑ አገራችን በፍልስጤም ላይ ያላትን አቋም መወከሉ ኢላማ ለመደረጉ ትክክለኛ ምክንያቶች ናቸው" ሲሉ ጃኮብስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው በሚል በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የከሰሰቻት ሲሆን ይህም ጉዳይ በጦር መሳሪያ ጭምር እየደገፈቻት ያለችውን አሜሪካን አስቀይሟል።
በጆሃንስበርግ ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ግንኙት ኤክስፐርት የሆኑት ኦስካር ቫን ሔርደን በበኩላቸው አምባሳደሩ በአሁነኛው ሹመታቸው እንዳልተፈለጉ እና "እሳቸውን ለማስወገድ ቀድሞውኑ ይፈለግ ነበር" ይላሉ።
ኦስካር ቫን ሄርደን ራሱልን የሚያውቋቸው ተማሪ እያሉ እንዲሁም አምባሳደሩ የሁለተኛ ደረጃ መምህር በነበሩበት በአውሮፓውያኑ 1985 ነበር። አምባሳደሩ የፍልስጤምን በአገርነት መመስረት የሚደግፉ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት የአምባሳደሩን ምትክ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ቢሆንም ዶ/ር ቫን ሄርደን የትራምፕን አስተዳደር ለማስደሰት ምንም አይነት ልምድም በቂ እንደማይሆን እና የሚስማሙበት ሰው ብቻ ሊሳካላት ይችላል ብለዋል።