በአዲስ አበባ አንድ ታዳጊ በጅብ ጥቃት ዐይኑን ጨምሮ ግማሽ ፊቱን አጣ

በአዲስ አበባ አንድ የ10 ዓመት ታዳጊ በጅብ ጥቃት አይኑን ጨምሮ ግማሽ የቀኝ ፊቱ ክፉኛ እንደተጎዳ ቤተሰቡና ህክምናውን እያከናወኑ ያሉ ሐኪም ለቢቢሲ ተናገሩ።

ክስተቱ የተፈጠረው ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም. ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ሲሆን ቦታው ደግሞ የካ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ ዘጠኝ፣ ወንድማማች ቀጠና ጅፋራ በር የሚባል ስፍራ አካባቢ ነው።

ስንታየሁ ግርማ የተባለው ታዳጊ በጅቡ ጥቃት የቀኝ ፊቱ እንደተበላና በአሁኑ ወቅትም የመተንፈሻ ቱቦ ወደ ሳንባው ገብቶለት በማሽን እየተነፈሰ እንደሆነ፣ በአለርት ሆስፒታል የድንገተኛ እና የጽኑ ህሙማን ክፍል የህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ብሩክ ከበደ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ለሕይወቱ የሚያሰጋ አይደለም”

ለአምስተኛ ቀን ህክምና እየተደረገለት ያለው ታዳጊው ስንታየሁ ግርማ ከፍተኛ ጉዳት ቢደርስበትም “በዚህ ሰዓት ለሕይወቱ የሚያሰጋው” እንዳልሆነ ዶክተር ብሩክ ተናግረዋል።

ጉዳቱ የደረሰው በፊቱ በቀኝ በኩል ሲሆን ግማሽ ፊቱንም በሙሉ ይሸፍናል። ግማሽ ፊቱ ላይ ያለው ጉንጩ፣ ከንፈሩ፣ ጡንቻው እስከ አንገቱ ድረስ በሙሉ በጅብ የተበላ ሲሆን፣ ታዳጊው ቀኝ አይኑን ከማጣት በተጨማሪ የመተንፈሻ አካሉ ላይ ጉዳት ደርሶበታል።

በቀዶ ህክምና የተጎዱ የፊቱ ክፍሎችን ማስወገድ የተቻለ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ የሚሰጠው ህክምና ቁስሉ ኢንፌክሽን እንዳይፈጥር ንጽህናውን መጠበቅ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር ብሩክ በየስምንት ሰዓቱም እየተጸዳ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት ልጁ የነቃ ሲሆን ቁስሉ በተወሰነ መልኩ መሻሻል ካሳየ ቆዳ ከሌላው የሰውነት ክፍሉ ተወስዶ ግልጽ የሆኑ የፊቱን አካላት ለመሸፈን የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና የሚሰራለት እንደሆነም ዶክተር ብሩክ አስረድተዋል።

የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ክፍል የታዳጊውን ህክምና እየመራ ሲሆን ግማሽ ፊቱን ያጣው ታዳጊ የፕላስቲክ እና መልሶ የመጠገን ቀዶ ህክምና ያስፈልጋዋል ተብሏል።

“መከላከል የምንችላቸው ነገሮች በህጻን ልጅ ላይ ሲከሰቱ ሁልጊዜም ከባድ ናቸው። ስሜትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚነኩ ናቸው” ብለዋል ዶክተሩ።

በተጨማሪም በአገሪቱ ከፕላስቲክና መልሶ አካልን የመጠገን ቀዶ ህክምና የደረሰበት ደረጃ ያን ያህል የላቀ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ እንዲሁም የህክምና ግብዓቶች አለመኖራቸው እና የባለሙያዎች እጥረት ሁኔታውን እንደሚያከብደውም አስረድተዋል።

“ህክምናው ከባድ ነው ህጻን በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ውስጥ ለዚህ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ስለሌሉና የባለሙያዎችን እጥረት ጭምር ሁኔታውን የበለጠ አስቸጋሪ ያደርገዋል” ብለዋል።

ከዚህ በፊት አንድ ጎልማሳ ሰው ፊቱን በካንሰር ህመም ምክንያት ፊቱ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶበት እንዳጋጠማቸው የሚያስታውሱት ዶ/ር ብሩክ፣ በድንገተኛ አደጋ በጅብ ተበልቶ ፊቱን ያጣ አጋጥሟቸው እንደማያውቅ ያስረዳሉ።

“ህጻን ልጅ ነው። መላው ህይወቱ ከፊቱ የሚጠብቀው ነበር። ቢተርፍ እንኳን ፊቱ ላይ ያለው አደጋ ከማኅበረሰቡ ጋር መልሶ መቀላቀል ይችላል ወይ? እሱ ላይ የሚኖረው ሥነ ልቦናዊ የሆነው ጉዳት በጣም ከባድ ነው” ብለዋል።

ዶክተሩ ራሳቸው በታዳጊው ላይ የተከሰተው ሁኔታ በጣም የተሰማቸው ሲሆን እንቅልፍ ለመተኛት እንደተቸገሩ ተናግረዋል።

“እግዚአብሔር ይርዳው፤ እኛ የተቻለንን ሁሉ ነገር እናደርጋለን። የኢትዮጵያ ሕዝብም ቢረዳው” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

“ልጅህን ጅብ በላልህ፣ ብለው ነገሩኝ”

በቀን ሥራ የሚተዳደሩት የስንታየሁ አባት አቶ ግርማ ፀጋዬ ልጃቸው ጅብ በተበላባት በዚያች “የተረገመች ዕለት” ለሥራ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደው ነበር።

የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት የሚማረውና ወደ ሦስተኛ ክፍል የተዛወረው ብቸኛ ልጃቸውንም ራቅ ብለው ስለሚሄዱ መውሰድም ፈልገው ነበር።

ነገር ግን ስንታየሁ ፈተና እንዳለው ስለነገራቸው ፈተናውን ሲጨርስ ከጓደኞቹ ጋር እንዲጫወትና ጫካ እንዳይሄድ፣ እሳቸው እስኪመለሱም አብሮ ከእነሱ ጋር እንዲውል ጠየቁት።

ልጃቸው ከጓደኞቹ ጋር እየተጫወተ ሳለ ጅብ ሊያጠቃቸው እንደመጣና አብረውት የነበሩት ጓደኞቹ ሮጠው ሲያመልጡ ስንታየሁ ግን አንሸራትቶት ወደቀ።

ከዚያም ከመኖሪያቸው ርቀው የነበሩት አባት መጥፎውን ክስተት “ልጅህን ጅብ በልቶታል ብሎ ጎረቤት ደወለልኝ” በማለት በሐዘን ያስረዳሉ።

ጎረቤታቸው ወይዘሮ ሲሳይ ደርብ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ጩኸት ሰምተው ከስፍራው ላይ ሲደርሱ፣ ጎረቤት ታዳጊውን ከጅቡ አስጥለውት ፊቱ ተሸፍኖ ነበር ከቦታው የደረሱት።

“ሙሉ ፊቱ የለም። በአንድ በኩል ዐይኑም፣ አገጩም ምንም ፊቱ የለም” ብለዋል።

ከዚያም ለፖሊስ ተደውሎ በአንድ ግለሰብ ትብብር ከባድ ጉዳት የደረሰበት ታዳጊ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ተወሰደ።

አባትየው አቶ ግርማ በደረሱበት ወቅት ልጃቸው ምኒልክ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር። ምኒልክ ሲደርሱም ደሙን እየጠራረጉት ነበር። በኋላም ለተሻለ ህክምና ጴጥሮስ ሆስፒታል ተላከ።

እዚያም አንድ ቀን ካደሩ በኋላ አሁን ህክምና እያገኘ ወደሚገኝበት አለርት ሆስፒታል ተወስዶ በመተንፈሻ ማገዣ መሳሪያ እየተረዳ ይገኛል።

“መናደድ፣ ብስጭት ነው። አንድ ልጄን እንደዚህ ሲያደርገኝ ምን ዋጋ አለው፤ ለፍቼ እንዴት እንዳሳደግኩና ያለ እናት ብቻዬን የተሰቃየሁት በቃ ሁሉም ነገር ተሰማኝ” ይላሉ አባት ያሉበትን ሁኔታ ሲገልጹ።

ይህ በልጃቸው ላይ የደረሰው ከባድ ጉዳት ሐዘናቸውን አበርትቶት ራሳቸውን ጭምር ለመጉዳትም አስበው እንደነበር ለቢቢሲ የተናገሩት አባት “የሚተርፍልኝ ከሆነ የሚያገላብጠው ሰው ይቸግረዋል ብዬ እንደገና አሰብኩኝ” ይላሉ።

አባት ከልጁ እናት ጋር የሦስት ዓመት ህጻን እያለ የተለያዩ ሲሆን፣ እሱም ላይ ትኩረት በማድረግ ያገኙትን ተባራሪ የቀን ሥራ እየሰሩ ብቻቸውን ለማሳደግ ደፋ ቀና እያሉ ነበር።

“እግዚአብሔር ደርሶ፤ ከአምላክ በታች ሕዝቡ ቢረዳኝ” በማለት ሁሉም የሚችለውን በማድረግ ልጃቸውን እንዲረዳላቸው ይማጸናሉ።

ስንታየሁ አዲስ አበባ ነው ተወልዶ ያደገው። አባትየው ስለ ልጃቸው ሲናገሩ “እኔ ያልኩት ይሁን ማለት ይወዳል። ጨዋታ በጣም ይወዳል” ይላሉ።

የጎረቤት ሴቶች ሲሄዱም ጫካ ተከትሎ መሄድ የሚወድ ሲሆን፣ በተደጋሚም “አንተ ተው እውቀት የለህም፤ ጅብ ይበላሃል። ሌሎቹ ትልልቆች ናቸው። ጅብ ብቻ ሳይሆን ሌላም ሌላም ችግር ይደርስብሃል፤ ተው እኔ የምልህን ስማኝ። አንተ ከሌለህ ጓደኛም ጨዋታም የለም እያልኩ እመክረው ነበር” ይላሉ።

“ጫካ ውስጥ ነው የምንኖረው”

ከቀናት በፊት በጅብ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ታዳጊ አባት የሆኑት አቶ ግርማ፣ ከዚህ በፊትም በሚኖሩበት ሰፈር በተመሳሳይ ሁኔታ በጅብ ጉዳት የደረሰበት ሰው እንዳለ ያስታውሳሉ።

አባት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከእሳቸው ልጅ በቀደመ ጊዜ በቤተሰቦቿ ቃ ከሱቅ እንድትገዛ የተላከች የስድስት ዓመት ህፃን በጅብ ተነክሳ ተጎትታ ወስዷት ነበር ብለዋል።

በወቅቱ በስፍራው በአቅራቢያ የነበሩ ራጮች ከጅቡ ጋር ታግለው ለማስጣል የቻሉ ቢሆንም፣ በጅቡ በደረሰባት ከባድ ጉዳት ሳቢያ ሆስፒታል ደርሳ ህይወቷ አልፏል።

ሰፈሩ በደን የተሸፈነ ሲሆን ጅብ “ጉሬው ነው” የሚሉት አቶ ግርማ አንዳንዴም ህፃናትንም እንደሚተናኮል ያስረዳሉ።

በርካታ ጊዜም “እንተያያለን፤ እንተላለፋለን” ይላሉ።

በአካባቢው ጅብ የተለመደ ቢሆንም መተናኮል ያልተለመደ መሆኑን የሚያስረዱት የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሲሳይ፣ በቤት ኪራይ ውድነት ምክንያት ጫካ አካባቢ ነው የምንኖረው ይላሉ።

ግለሰቧ እንደሚሉት በአካባቢው ወደ 45 ዓመታትም የኖሩ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ቦታው መብራት ያልገባለት እንዲሁም በርካቶች በኩራዝ ብርሃን የሚኖሩበት ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።