ኢትዮጵያ ፆታዊ ጥቃት ፈጻሚዎችን ከሥራ እና ከማኅበራዊ ግልጋሎቶች የሚያገል ምዝገባ ልትጀምር ነው

የኢትዮጵያ መንግሥት ፆታዊ ጥቃት ፈጻሚዎችን የሚመዘግብ ሥርዓት ሊጀምር መሆኑን የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ምዝገባው ፆታን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል እና ለመቀነስ ያለመ ነው የተባለ ሲሆን፣ በተለይ “ወሲባዊ ጥቃቶች ላይ ትኩረት” እንደሚያደርግ ተነግሯል።

በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች መብት እና ጥበቃ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ታደሰ፣ የምዝገባ ሥርዓቱን ለመጀመር 10 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፣ ይህ በጀት በተለያዩ አካላት መዋጮ እንደሚሸፈንም ጠቁመዋል።

ይህ ‘ብሔራዊ የፆታዊ ጥቃት ወንጀል ምዝገባ ሥርዓት’ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተደረገ ጥናት ከጠቅላላ የአገሪቱ ሴቶች 35 በመቶዎቹ የተለያዩ ዓይነት ፆታዊ ጥቃቶች እንደሚደርሱባቸው ያሳያል።

‘ብሔራዊ የፆታዊ ጥቃት ወንጀል ምዝገባ ሥርዓት’ የተሰኘው ሥርዓቱ፣ ጥቃት ፈጻሚዎች በሕግ ከታሰሩ እና ቅጣት ከተላለፈባቸው በኋላም ለዘለዓለም ተጠያቂ የሚያደርግ እና “ከተመረጡ” ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግልጋሎቶች የሚያገል መሆኑ ታውቋል።

ቢቢሲ የተመለከተው የምዝገባው መነሻ ጽሑፍ ሥርዓቱ ጥቃት ፈጻሚዎችን መለየት፣ አድራሻቸውን ማወቅ እና መከታተል እንዲሁም ዳግም ጥቃት እንዳያደርሱ ተጠያቂነታቸውን ከፍ በማድረግ ሕዝባዊ ደኅንነትን መጠበቅ አንደኛው ዓላማው ነው።

ለፖሊስ ምርመራ የተደራጀ መረጃ ማቅረብን ሌላ ዓላማ ያደረገው የምዝገባ ሥርዓቱ፤ የፍትሕ ሥርዓቱን ጠበቅ ለማድረግ የሚያግዙ የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፎች ማሻሻያ ለማድረግ የግብዓት ድጋፍ እንደሚያደርግም ይጠቅሳል።

በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተለያዩ የፍትሕ ተቋማትን እና ሌሎች የሚመለከታቸውን ተቋማት ያካተተ ኮሚቴ የምዝገባ ሥርዓቱን እያዘጋጀ ይገኛል።

ሚኒስቴሩ እስካሁን የሌሎች አገራትን ልምድ በመቃኘት እና ግብዓት በማሰባሰብ ምዝገባው ላይ የሚካተቱ ‘አመላካቾች’ መለየታቸውን ተናግሯል።

እንደ ስም፣ አድራሻ፣ የጥቃት ዓይነት እና ደረጃን ጨምሮ ሌሎች መረጃዎች በምዝገባው ላይ አመላካቾች ተብለው እንደገቡ ታውቋል።

የሚኒስቴሩ የሴቶች መብት እና ጥበቃ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ታደሰ፣ በምዝገባው ሁሉም ዓይነት ጾታዊ ጥቃቶች እንደሚመዘገቡ ጠቅሰው፤ ሆኖም ሥርዓቱ በዋናነት ግን ወሲባዊ ጥቃቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“የሚቀርቡ ጉዳዮች በፍትሕ ሥርዓቱ የሚያልፉ ናቸው። የትኛው [የጥቃት ዓይነት] ተገቢ ይሆናል የሚለው ሁሉንም እንዲያካትት ነው። ነገር ግን ለመረጃ አሰባሰብ ገደብ ያለባቸው ወደ ሥርዓቱ ላይገቡ ይችሉ ይሆናል። ከዚህ ውጭ ግን ሁሉንም እንዲያካትት ነው። በተለይ ግን ወሲባዊ ጥቃቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው” ብለዋል።

ሥራ አስፈጻሚው የምዝገባ ሥርዓቱን ጥቅም ሲያስረዱ፣ ምዝገባውን ገቢራዊ ያደረጉ አገራትን ልምድ በመጥቀስ ሥርዓቱ ፆታዊ ጥቃቶችን መከላከል እና መቀነስ፤ ተደጋጋሚ ጥቃት አድራሾችን መረጃ መሰብሰብ እንዲሁም ከማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንደሚያገል ጠቁመዋል።

በምዝገባ ሥርዓቱ ጥቃት አድራሾች (ምንም እንኳ የመጨረሻ ውሳኔ ባይደረስበትም) በተለይም እንደ ትምህርት ቤቶች፣ ህጻናት የሚገኙባቸው እና ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ሥራ እንዳይቀጠሩ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል።

“ትምህርት ቤቶች፣ በተለይ ህጻናት ያሉባቸው፣ ጥቃት ሊደርስባቸው የሚችሉ አካባቢዎች፣ የተለያዩ ተቋማት፣ ማሳደጊያዎች ሊሆኑ ይችላሉ ዳግም ጥቃት እንዳያደርሱ መከላከል ነው” ብለዋል።

ይህን የምዝገባ ሥርዓት በዋናነት ፖሊስ እና ፍትሕ ሚነስቴር እንደሚያስፈጽሙትም ተናግረዋል።

ሆኖም ሥርዓቱን መጠቀም የሚችሉ እንደ ቀጣሪ ያሉ ተቋማት እንደሚኖሩ ኃላፊው ጠቁመዋል።

በዚህ ሥርዓት መነሻ ጽሑፍ መመዝገቢያ ሶፍትዌሩ በሦስት መንገዶች ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን ይጠቅሳል።

አስፈላጊ የተባሉ መረጃዎች ለሁሉም መረጃ ፈላጊዎች ክፍት የሚሆኑበት ገጽ ቀዳሚው ሲሆን፣ ከሳሾች ክስ የሚያቀርቡበት እንዲሁም ቀጣሪዎች የሚቀጥሯቸው ሠራተኞች የፆታዊ ጥቃት ወንጀል ታሪክ እንዳላቸው የሚያጣሩበት ገጾች ይኖሩታል ይላል።

ብሔራዊ የጾታዊ ጥቃት ወንጀል ምዝገባ ሥርዓት የግላዊ መብት እና ሥራ የመሥራት የመሰሉ የኢትዮጵያ ሕጎች ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ መቃኘቱን አቶ ስለሺ ገልጸዋል።

እ.አ.አ በ2016 በተደረገ ጥናት 23 በመቶ የኢትዮጵያ ሴቶች አካላዊ ጥቃት እና 10 በመቶዎቹ ደግሞ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። የምዝገባ ሥርዓቱ ፆታዊ ጥቃት ከባድ ፈተና መሆኑ በቀጠለባት አገር “ለውጥ ያመጣል” የሚል ተስፋ ተሰንቆበታል።

“ለምሳሌ አንድ ጥቃት ፈጻሚ አራቴም፣ አምስቴም ወንጀሉን የሚፈጽም አለ። መረጃው ስለማይያዝ አይታወቅም። እንዲህ መደረጉ [መመዝገቡ] እንዲቀንስ የማድረግ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ለዚህም ነው የመረጃ ሥርዓቱ የሚያከማቸው [መረጃ] አስፈላጊ የሚሆነው። ሲነሱ ለነበሩ ችግሮች ምላሽ የሚሰጥ ስለሆነ ውጤት ያመጣል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ ይህ ፆታዊ ጥቃት አድራሾችን የሚመዘግበው ሥርዓት ሊጀመር ነው ከተባለ ሦስት ዓመታት በላይ አልፈዋል።

የምዝገባ ሥርዓቱን ለመጀመር ምን ችግር ገጠማችሁ ሲል ቢቢሲ የጠየቃቸው በሚኒስቴሩ የሴቶች መብት እና ጥበቃ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስለሺ ታደሰ፤ ሀብት የማሰባሰብ ችግር እክል እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

ሥራ አስፈጻሚው የምዝገባ ሥርዓቱን ለመጀመር 10 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተናግረዋል።

ሥርዓቱን መንደፍ በመደበኛ በጀት እንደተከናወነ የሚጠቅሱ ሲሆን፤ ሥርዓቱ “የአንድ አካል ብቻ አይደለም” ሲሉም የምዝገባ ሥርዓቱ በጀት በመዋጮ እንደሚሸፈን ጠቁመዋል።

ፖሊስ ካለው የወንጀለኞች ምዝገባ ሥርዓት ጋር “ራሱን ችሎ” ይዋሃዳል የተባለው ‘ብሔራዊ የፆታዊ ጥቃት ወንጀል ምዝገባ ሥርዓት’፤ በሚቀጥለው ዓመት ተግባራዊ መሆን ይጀምራል ተብሏል።