ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሶሪያ በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የተከሰተውን ግጭት ለማስቆም እየታገለች ነው
በደቡባዊ ሶሪያ በአገሪቱ ፕሬዝዳንት "አፋጣኝ የተኩስ አቁም" ስምምነት ቢደረግም ሃይማኖት ተኮር ግጭቶች ቀጥለዋል።
የድሩዝ ተዋጊዎች ቅዳሜ ዕለት የቤዶኤን ታጣቂዎችን ከሱዋይዳ ከተማ ገፍተው እንዳስወጡ ዘገባዎች ሲገልፁ፣ በሌሎች የግዛቱ አካባቢዎች ግን ጦርነቱ ቀጥሏል።
ቢቢሲ ይህን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ የተሰማሩት የመንግሥት ኃይሎች በድሩዞች ላይ ጥቃት ለመፈፀም ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ባለፈው ሳምንት ከ900 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። ሁሉም ወገኖች የጭካኔ እርምጃ በመውሰድ ይከሰሳሉ።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ቅዳሜ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ጽሑፍ በሶሪያ "በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን መደፈር እና ግድያ" እንዲቆም ጠይቀዋል።
ሩቢዮ "በደማስቆ ያሉ ባለስልጣናት ከአይኤስ [እስላማዊ መንግሥት] እና ከኢራን ቁጥጥር ነፃ የሆነች፣ አንድነቷ የተጠበቀ እና ሰላማዊ የሆነች ሶሪያን ለማምጣት ያለውን ማንኛውንም ዕድል ለመጠበቅ ከፈለጉ የጸጥታ ኃይላቸውን ተጠቅመው አይኤስአይኤስ እና ሌሎች አማፂ ጂሃዲስቶች ወደ አካባቢው እንዳይገቡ እና እልቂትን እንዳያካሂዱ መከላከል አለባቸው" ሲሉ ጽፈዋል።
እኚሁ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ዲፕሎማት አክለውም "የራሳቸው ባለስልጠናትን ጨምሮ በደል የፈፀመ ማንኛውንም ሰው ተጠያቂ በማድረግ ለፍርድ ማቅረብ አለባቸው" ብለዋል።
ቅዳሜ ማምሻውን የሶሪያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጦሩ በከተማዋ ጣልቃ ከገባ በኋላ በሱዌይዳ የተፈጠረው ግጭት መቆሙን ተናግሯል።
የሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው በሌሎች የሱዋይዳ ግዛት አካባቢዎች ጦርነቱ ቀጥሏል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ እስራኤል ድሩዞችን እንደምትደግፍ በማወጅ ጣልቃ በመግባት የመንግሥት ወታደሮችን እና በዋና ከተማዋ ደማስቆ የሚገኘውን የመከላከያ ሚኒስቴርን መትታለች።
ግጭቱን ለማስቆም የሶሪያ የጸጥታ ኃይሎች ወደ ሱዋይዳ በተሰማሩበት ወቅት ፕሬዝዳንት ሻራ የተኩስ አቁም መደረጉን አስታውቀዋል።
ስምምነቱ የእስራኤል ወታደራዊ ጥቃቶችን ማስቆምን ያካተተ ሲሆን የድሩዝ ማኅበረሰብ ከለላ እስካገኙ ድረስ በዩናይትድ ስቴትስ የተፈረመው ስምምነት በእስራኤል ተቀባይነት አግኝቷል።
ብዙ ሰዎች ወደ ጦርነቱ እንዳይቀላቀሉ ለማድረግ የመንግሥት ወታደሮች ኬላዎችን እያዘጋጁ ነው። ነገር ግን ቅዳሜ ዕለት ቀደም ብሎ በሱዌዳ ውስጥ የተኩስ ድምጽ መሰማቱ ታውቋል።
የኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል በበኩሉ የታጠቁ ሰዎች ሱቆችን ሲዘርፉ እና ሲያቃጥሉ መታየታቸውን ተናግሯል።
በተጨማሪም ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ህዳጣኖችን እና ሁሉንም ሶርያውያንን ለመጠበቅ ፕሬዚዳንቱ ያደሱትን ቃል ጥርጣሬ ላይ ወድቋል ብለዋል።
የድሩዝ ማኅበረሰብ ከሺዓ እስልምና የተቀዳ ልዩ እምነትን የሚከተሉ ሲሆን አሁን በደማስቆ ያለውን መንግሥት አይቀበሉም።
በሶሪያ ውስጥ ቁጥራቸው አነስተኛ ሲሆን በአጎራባች እስራኤል እና ሊባኖስ ውስጥም ይገኛሉ።
በማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ጌዲዮን ሳር የተባለ ግለሰብ በሶሪያ ውስጥ ያሉ ድሃጣን አካል መሆን "በጣም አደገኛ" እንደሆነ እና "ይህ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በተደጋጋሚ የተረጋገጠ ነው" ሲል ጽፏል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሶሪያ የሚገኙት ድሩዞች በእስራኤል ከሚኖሩት ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመከላከል ቃል ገብተዋል።
በሱዌይዳ በድሩዝ እና በቤዶኤ ጎሳዎች መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀው ውጥረት ወደ ደማስቆ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ የድሩዝ ነጋዴ መታፈኑን ተከትሎ ከፍተኛ ወደ ሆነ ሃይማኖት ተኮር ግጭት ተቀይሯል።
መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ድርጅት (SOHR) እንደገለጸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ 940 ሰዎች ተገድለዋል።
በእስራኤል እና በሶሪያ መካከል አርብ የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉን በሶሪያ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ቶም ባራክ አርብ እለት አስታውቀዋል።
"ድሩዝ፣ ቤዶኤ እና ሱኒዎች መሳሪያቸውን እንዲያስቀምጡ እና ከሌሎች ህዳጣን [ማኅበረሰቦች] ጋር በመሆን ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም እና ብልጽግና ውስጥ አዲስ እና አንድነት ያለው የሶሪያ ማንነት እንዲገነቡ እንጠይቃለን" ብለዋል።
የቢቢሲ የመካከለኛው ምሥራቅ ጋዜጠኛ ሊና ሲንጃብ ከሶሪያ እንደዘገበችው በድሩዝ ላይ የሚደርሰው ጥቃት በመላ አገሪቱ እየተስፋፋ ነው።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ቮልከር ቱርክ በግጭቶች ወቅት የተፈጸሙ በደሎችን እና የመብት ጥሰቶችን የሚያመላክቱ ታማኝ ሪፖርቶች ጽህፈት ቤታቸው እንደደረሰው ገልፀው በሱዌይዳ የተፈጸመ ግድያ እና የዘፈቀደ ግድያ እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
ድርጊቱን ፈጽመዋል ከተባሉት መካከል የጸጥታ ኃይሎች እና ከጊዚያዊ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች እንዲሁም በአካባቢው ድሩዝ እና ቤዶኤ የታጠቁ ኃይሎች እንደሚገኙበት ቱርክ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
"ይህ ደም መፋሰስ እና ሁከት መቆም አለበት" ሲሉ አስጠንቅቀው፤ "በዚህም ተጠያቂ የሆኑ አካላት በሕግ መጠየቅ አለባቸው" ብለዋል።
የሶሪያ መሪ ቅዳሜ ማለዳ ላይ በሰጡት አስተያየት መንግሥታቸው "በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ህዳጣን ቡድኖች እና የሃይማኖት ተከታዮች ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነው፤ እናም ሁሉንም አጥፊዎች ተጠያቂ ለማድረግ እየሠራ ነው። ማንም ከተጠያቂነት አያመልጥም" ብለዋል።