ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ያሳፈረች አነስተኛ ጀልባ የዩኬ ቻናልን አቋረጠች
ቅዳሜ ዕለት አንዲት አነስተኛ ጀልባ 125 ሰዎችን አሳፍራ የእንግሊዝ ቻናልን ማቋረጧ ተሰማ።
በአንድ ጀልባ ውስጥ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው በርካታ ስደተኞች ሲጓጓዙ ይህ የመጀመርያው ነው ተብሏል።
በነሐሴ ወር 106 ሰዎች በአንድ ጀልባ ለመጓዝ ሞክረው የነበረ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በአንድ ጀልባ ሲጓዙ ይህ የመጀመርያው ነው።
ከአገር ውስጥ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ቅዳሜ ዕለት ብቻ 895 ስደተኞች ቻናሉን በ12 ጀልባዎች ሲያቋርጡ፣ እአአ ከ2025 መጀመርያ ጀምሮ 33,000 ሰዎች ወደ ዩኬ በአነስተኛ ጀልባዎች ገብተዋል።
በሰሜን ፈረንሳይ ቦሎኝ ሱር-ሜር አቅራቢያ በሚገኝ የባህር ዳርቻ ላይ ቻናሉን ለማቋረጥ ሲሞክር የሞተ ስደተኛ አስከሬን እሁድ ጠዋት መገኘቱን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የግለሰቡ ዕድሜ እና ዜግነት እስካሁን ድረስ ያልታወቀ ሲሆን የፈረንሳይ ሚዲያዎች ሟቹ ወጣት ነበር ብለዋል።
ከቦሎኝ ሱር-መር በስተሰሜን ትንሽ ራቅ ብሎ በሚገኘው ኢኩሄን-ፕላጅ አቅራቢያ ወደ ዩኬ ለማቋረጥ በተደረገ ሙከራ እና አሁን በተገኘው አስከሬን መካከል ግንኙነት መኖር አለመኖሩ ላይ ምርመራ እንደሚደረግ የወደብ ከተማው አቃቤ ሕግ ሲሲል ግሬሲየር ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
በዚያ አካባቢ የ49 ዓመቷ ሴት በከፍተኛ ቅዝቃዜ (ሃይፖተርሚያ) ስትሰቃይ ተገኝታ ወደ ሆስፒታል መወሰዷ ተገልጿል።
ቅዳሜ ዕለት ሁለት የሶማሊያ ሴቶች ጊዜያዊ ጀልባቸው ችግር አጋጥሞት ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን በዚህ ዓመት ከፈረንሳይ ወደ ዩኬ በሕገወጥ መንገድ ለመሻገር በተደረገ ሙከራ የሞቱት ሰዎች ቁጥር በትንሹ 27 ደርሷል።
ቅዳሜ ዕለት የነበረው የተመቻቸው የአየር ሁኔታ ስደተኞቹ ከፈረንሳይ ወደ ዩኬ ለማቋረጥ ያደረጉትን ጉዞ ቀለል ያደረገው ሲሆን 14 ሰው ብቻ የአደጋ ጊዜ ድጋፍን በባህር ተቆጣጣሪዎች ማግኘታቸው ተገልጿል።
ምንም እንኳን ስደተኞች አደገኛ በሆነ ሁኔታ ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ በባህር እንዳያቋርጡ ለመከላከል ፈረንሳይ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች ብትመጣም፣ ዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ብታደርግም ሙከራዎች ምንም የመቀነስ አዝማሚያ አላሳዩም።
ሌበር ፓርቲ እአአ በ2024 ሐምሌ ወር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ከ50,000 በላይ ሰዎች በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ዩኬ በመግባት የጥገኝነት ጥያቄ በማቅረባቸው የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ጫናዎች በርትተውበታል።
የአገር ውስጥ ጉዳዩች ሚኒስትሯ ሻባና ማሕሙድ ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች "በድንበሮቻችን ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሱ ነው" በማለት "የኢሚግሬሽን ስርዓታችንን ወደነበረበት እንመልሳለን" ብለዋል።