ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩናይትድ ኪንግደም እና በፈረንሳይ ስምምነት የመጀመሪያው ኤርትራዊ ስደተኛ ከዩኬ ተባረረ
ከዩናይትድ ኪንግደም እንዳይባረር ለፍርድ ቤት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ የተደረገበት ኤርትራዊው ስደተኛ፤ ከአገሪቱ እንዲጣ ተደርጎ ወደ ፈረንሳይ ተላከ።
ኤርትራዊው ከዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) እንዲወጣ መደረጉ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሕገወጥ ያላቸውን ስደተኞች ለማስወጣት ባቀረበው ክስ በፍርድ ቤት ሲረታ የመጀመሪያው ነው።
ምንም እንኳን አሁንም ስደተኞች በትናንሽ ጀልባዎች እየተሳፈሩ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመግባት መሞከራቸውን ቢቀጥሉም ዩኬ እና ፈረንሳይ ስደተኞችን ለመመለስ ተስማምተዋል።
እንዳይባረር ለፍርድ ቤት ያቀረበው ጥያቄ ያልተሳካለት ኤርትራዊው ስደተኛ ውሳኔውን ተከትሎ በአገር ውስጥ ጉዳይ ባለሥልጣን ታጅቦ ወደ ፈረንሳይ ከተወሰደ በኋላ ለፖሊስ ተስጥቷል።
ስደተኛው ወደ ፈረንሳይ እንዲመለስ ባደረገው ውሳኔ "መጥፎ ስሜት እንደተሰማው" የተናገረ ሲሆን፣ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ግለሰቡ ወደ ስደተኞች ማቆያ ማዕከል እንደሚገባ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በፈረንሳይ ሕግ መሠረት በሚቀጥሉት ስምንት ቀናት ውስጥ የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረብ ወይም ወደ አገሩ የመመለስ ዕድል አለው።
በዩኬ እና በፈረንሳይ መካከል የተደረሰው "አንድ ለአንድ" የተባለው ስምምነት ከፈረንሳይ ተነስተው በባሕር እንግሊዝ የሚገቡ ሰዎች ወደ ፈረንሳይ እንደሚባረሩ አውቀው ባሉበት እንዲቆዩ ለማድግ ያለመ ነው።
በአሠራሩ መሠረት አንድ ስደተኛ ከዩኬ ወደ ፈረንሳይ እንዲመለስ ሲደረግ፣ ፈረንሳይ ውስ ሆነው በዩኬ ጥገኝነት ለማግኘት ከጠየቁ ስደተኞች መካከል አሳማኝ ምክንያት ያለው ሌላ ስደተኛ እንዲገባ ይደረጋል።
በዚህ ስምምነት መሠረት ከዩኬ ሲባረር የመጀመሪያ በሆነው ኤርትራዊ ምትክ ሌላ ስደተኛ በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ዩኬ እንዲጓዝ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የዩኬ ንግድ ሚኒስትር ፒተር ካይሊ ይህ አሠራር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሲገልጹ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት ክሪስ ፊሊፕ ግን "ዛሬ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ባሕር ተሻግረው እየገቡ ሁለት ስደተኞችን ለዚያውም በሌላ የሚተኩ ስደተኞችን በማባረር" መንግሥት አድናቆት ይፈልጋል ሲሉ ተችተዋል።
አርብ ዕለት ከዩኬ እንዲወጣ የተደረገው ኤርትራዊ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላን በመሸሽ በአውሮፓውያኑ 2019 ከአገሩ መውጣቱን እና ባለፈው ነሐሴ በትንሽ ጀልባ ተሳፍሮ ወደ ኢንግላንድ መግባቱን ለፍርድ ቤት ተናግሯል።
ግለሰቡ ከአገሩ ከወጣ በኋላ ወደ አውሮፓ ከመግባቱ በፊት በኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በሊቢያ ቆይቷል። ፈረንሳይ ውስጥ ጎዳና ላይ እየኖረ ቆይቶ በእንግሊዝ ቻናል በኩል በትንሽዬ ጀልባ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መግባቱን ገልጿል።
ከዩናይትድ ኪንግደም እንዲወጡ የሚደረጉ ስደተኞች ፈረንሳይ ውስጥ ሆነው የጥገኝነት ጥያቄያቸውን በማቅረብ መከታተል የሚችሉ ሲሆን፣ ፈረንሳይም ደኅንነታቸው የሚጠበቅባት ቦታ መሆኗን ይናገራሉ።