ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩኬ ለተቃውሞ መነሻ የሆነው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በወሲባዊ ትንኮሳ ክስ ጥፋተኛ ተባለ
በዩናይትድ ኪንግደም፣ ኢሴክስ ግዛት ኤፒንግ ከተማ ለተቃውሞ መነሻ የሆነው ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ሀዱሽ ቅባቱ በቀረበበት ወሲባዊ ትንኮሳዎች ክስ ጥፋተኛ ተባለ።
የኮልቸስተር ከተማ ፍርድ ቤት ሐሙስ፣ ነሐሴ 29/ 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ሀዱሽን በ14 ዓመት ታዳጊ እንዲሁም አዋቂ ሴት ላይ ወሲባዊ ትንኮሳዎችን በማድረስ ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል።
ሀዱሽ በከተማዋ ማዕከል ተቀምጠው ከነበሩ ሁለት የ14 ዓመት ታዳጊዎች መካከል አንደኛዋን መነካካቱን እንዲሁም ልጅ መውለድ እንደሚፈልግ ተናግሯል ተብሏል።
ታዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳዎች ማድረስን ጨምሮ አምስት ክሶች የቀረቡበት ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ሀዱሽ ገብረ ሥላሴ ቅባቱ ጋር ተያይዞ ባረፈበት ዘ ቤል በተሰኘው የጥገኛ ጠያቂዎች ሆቴል አካባቢ ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።
በትናንትናው ችሎት ሀዱሽ በታዳጊዋ ልጅ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳን በማድረስ፣ ህጻንን ለወሲባዊ ድርጊት በማነሳሳት እንዲሁም በወሲባዊ ጥቃት ሙከራ ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን ዳኛው የእስር ቅጣት እንደሚጠብቀው አስጠንቅቀዋል።
ሀዱሽ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መደበኛ ባልሆነ መንገድ የገባው ሰኔ 22/2017 ዓ.ም. ሲሆን፣ በቁጥጥር ሥር የዋለውም ከስምንት ቀናት በኋላ ሐምሌ 1 ነበር።
ከአገሩ ከወጣ ዓመታትን እንዳስቆጠረ ከሰሞኑ በነበረው ችሎት ያስረዳው ሀዱሽ በሊቢያ አቋርጦ ወደ ጣሊያን ከዚያም ፈረንሳይ መድረሱን ተናግሮ ነበር።
ከፈረንሳይም በትንሽ ጀልባ ተሳፍሮ 'ኢንግሊሽ ቻናልን' አቋርጦ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የገባ ሲሆን፣ ለዚህ ጉዞውም 1800 ዩሮ መክፈሉን አስረድቷል።
ሀዱሽ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ወቅት የስፖርት መምህር እንደነበረ ለፍርድ ቤት ተናግሯል።
ፍርድ ቤቱ የሀዱሽ ዕድሜ 41 ነው ቢልም እሱ ግን ዕድሜው 38 መሆኑን በዚህ ወቅት ገልጿል።
በኮልቸስተር ከተማ ለሶስት ቀናት በነበረው ችሎት "አራዊት አይደለሁም" "እኔ ክርስቲያን ነኝ፤ እንዲህ አይነት ነገሮችን አላደረግም፤ እነዚህ ልጆች ናቸው፤ ንጹህ ልጆች" ሲል የቀረበበትን ክሶች ውድቅ አድርጎ ነበር።
ነገር ግን የፍርድ ቤቱ ዳኛ ክርስቶፈር ዊልያምስ ሀዱሽ "የምስክርነት ቃሉን ለመስጠት ሲል የፈጠራቸው ናቸው" ሲሉ አጣጥለውታል።
በከተማዋ ማዕከል ሰኔ 30/ 2017 ዓ.ም የትምህርት ቤት ጓደኞች ተሰባስበው ባገኛቸው ወቅት ሀዱሽ ስሙን ቶማስ እንዳላቸው እና 2500 ዩሮ ከፍሎ ዩኬ እንደገባ እንደነገራቸው በስፍራው የነበረ አንድ ታዳጊ ከሰሞኑ በዋለው ችሎት ምስክርነቱን ሰጥቶ ነበር።
በተጨማሪም ለአንደኛዋ "አፍሪካ ነይ፤ ጥሩ ሚስት ትሆኛለሽ" እንዳለም ይሄው ታዳጊ ለፍርድ ቤት አስረድቷል።
ታዳጊዎቹ በወቅቱ ፒዛ እየበሉ የነበሩ ሲሆን "ከአንቺ አንድ ልጅ እፈልጋለሁ፤ ከጓደኛሽ ደግሞ አንድ ልጅ" ሲል መናገሩን አንደኛዋ ታዳጊ ለፖሊስ ተናግራለች።
ሀዱሽ በማግሥቱ አንደኛዋን ታዳጊ ቆንጆ አንደሆነች እንዲሁም ሊስማት መሞከሩን እና እጁን ጭኗ ላይ ማሳረፉን ምስክሮች ገልጸዋል።
በዚህ ወቅት ልጅቷ በከፍተኛ ሁኔታ መደንገጧን ለመርማሪዎች ገልጻ "አይ አይሆንም 14 ነው ዕድሜ" ስትለውም "እድሜ ምንም ለውጥ የለውም" በማለት ምላሽ መስጠቱን አክላለች።
ሁኔታው "አጥወለወለኝ። አንድ አዋቂ ሰው እንዴት ይህንን መፈጸም ምንም ችግር የለውም ብሎ የሚያስብ አይመስለኝም ነበር" ብላለች።
ውሳኔያቸውን ሲያስተላልፉ ዳኛ ዊልያምስ "የ14 ዓመት ልጅ እንደነበረች ታውቃለህ" ሲሉ ተናግረው በወቅቱ የትምህርት ቤት ዩኒፎርም መልበሷን አስታውሰዋል።
የእስር ቅጣቱ ላይ ለመወሰን ፍርድ ቤቱ ለመስከረም 18/ 2018 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።
ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተከትሎ በባለፉት ሳምንታት ሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቤል ሆቴል አቅራቢያ ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ አሰምተዋል።በተመሳሳይ መልኩ ዘረኝነትን የሚቃወሙ የድጋፍ ሰልፎች ተደርገዋል።
ከተቃውሞው ጋር ተያይዞ በተነሳው ሁከት 16 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።