"ክርስቲያን ነኝ፤ በባህሌ ውስጥ የለም" በዩኬ በወሲባዊ ትንኮሳ የተከሰሰው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ

በዩናይትድ ኪንግደም፣ ኢሴክስ ግዛት፣ በኤፒንግ ከተማ ወሲባዊ ትንኮሳዎች ፈጽሟል ተብሎ የተከሰሰው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ሀዱሽ ገብረ ሥላሴ ቅባቱ "ክርስቲያን ነኝ፤ ባህሌ አይደለም" ሲል የተከሰሰባቸውን ወንጀሎች እንዳልፈጸመ ለፍርድ ቤት ተናገረ።

በ14 ዓመት ታዳጊ ልጆች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳዎች፣ ህጻንን ለወሲባዊ ድርጊት ማነሳሳት፣ ወሲባዊ ጥቃት የሚሉትን ጨምሮ አምስት ክሶች የቀረበበት ሀዱሽ ይህንን የተናገረው በኮልቸስተር ከተማ ፍርድ ቤት ረቡዕ፣ ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም. በሰጠው ቃል ነው።

ሀዱሽ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መደበኛ ባልሆነ መንገድ የገባው ሰኔ 22/2017 ዓ.ም. ሲሆን፣ በቁጥጥር ስር የዋለውም ከስምንት ቀናት በኋላ ሐምሌ 1 ነበር።

ግለሰቡ የጥገኝነት ጠያቂዎች በሚኖሩበት ቤል ሆቴል ውስጥ ነዋሪ ነበር።

ትንኮሳዎቹንም አደረሰ የተባለው የትምህርት ቤት ጓደኞች ተሳባስበው ተቀምጠውበት በነበረው የኤፒንግ የከተማ ማዕከል ነው።

ግለሰቡ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ በዚህ ሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቤል ሆቴል አቅራቢያ ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ አሰምተዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ዘረኝነትን የሚቃወሙ የድጋፍ ሰልፎች ተደርገዋል።

ከተቃውሞው ጋር ተያይዞ በተነሳው ሁከት 16 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት የዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥገኝነት ጠያቂዎች ከሆቴሉ ወጥተው ወደ ሌላ ስፍራ እንዲዛወሩ እንዲሁም ሆቴሉ እንዲዘጋ በጊዜያዊነት ብያኔ አስተላልፏል።

የስደተኞችን ጉዳይ በበላይነት የሚያየው መሥሪያ ቤት 'ሆም ኦፊስ' እና የሆቴሉ ባለቤት በውሳኔው ላይ አቤቱታ ያስገቡ ሲሆን ውሳኔውም ለዛሬ ተቀጥሯል።

የፍርድ ቤቱ ሂደት ሀዱሽ ጥገኝነት ጠያቂ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም የማኅበረሰቡን እና የሚዲያውን ቀልብ ስቧል።

ማክሰኞ ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም. በዋለው ችሎት በከተማዋ ማዕከል ተቀምጠው የነበሩትን ሁለት የ14 ዓመት ታዳጊዎች ከእነሱ "ልጅ መውለድ እንደሚፈልግ" መናገሩ እና ወዳረፈበት ዘ ቤል ሆቴል እንደጋበዛቸው ፍርድ ቤቱ ሰምቷል። ሊስማቸውም እንደሞከረም ተገልጿል።

ጠበቃው ሞሊ ድያስ ደንበኛቸው በከተማዋ ማዕከላዊ ስፍራ ቢገኝም የቀረበበትን ክሶች ውድቅ አድርገው ተከራክረዋል።

በዚህ ችሎት የሀዱሽ ተርጓሚ ሂደቱን ሁሉ በትግርኛ እየተረጎመ ነበር።

ሀዱሽ በትናንትናው ዕለት በሰጠው ቃል የቀረቡበት ክሶች "ሁሉ የፈጠራ እንደሆነ እና ምንም ስህተት አልሠራሁም" ሲል ራሱን ተከላክሎ ምላሽ ሰጥቷል።

ሀዱሽ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዴት እንደገባ ከዐቃቤ ሕግ የመስቀለኛ ጥያቄ ቀርቦለታል።

ከአገሩ ኢትዮጵያ "ከወጣሁ ዓመታትን፣ በርካታ ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ" ብሏል።

ሀዱሽ ጉዞውን ሲያስረዳም ከኢትዮጵያ ተነስቶ፣ በሊቢያ ተሻግሮ ወደ ጣሊያን ከዚያም ፈረንሳይ ደርሷል።

ከፈረንሳይም በትንሽ ጀልባ ተሳፍሮ 'ኢንግሊሽ ቻናልን' አቋርጦ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የገባ ሲሆን፣ ለዚህ ጉዞውም 1800 ዩሮ መክፈሉን አስረድቷል።

ሀዱሽ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ወቅት የስፖርት መምህር እንደነበረም ተናግሯል።

ፍርድ ቤቱ የሀዱሽ ዕድሜ 41 ነው ቢልም እሱ ግን ዕድሜው 38 መሆኑን በዚህ ወቅት ገልጿል።

የሀዱሽ ጠበቃ ሞሊ ደይስ "በህጻናቱ ላይ ያደረግከው ነገር አለ ወይ?" ስትል ጠይቃዋለች።

"እኔ አራዊት አይደለሁም፤ እነዚህ ህጻናት ናቸው፣ የነገ ተስፋ፣ የወደፊቱ ትውልድ" ብሏል።

በምስክር መስጫ ሳጥን ውስጥም ሆኖ በተቆጣ መንፈስ "እኔ ወንጀለኛ አይደለሁም" ሲል ለፍርድ ቤቱ አሰረድቷል።

በቁጥጥር ስር ላዋሉት ፖሊሶች ለምን "አዝናለሁ" አልክ ተብሎ በተጠየቀበት ወቅትም፤ "በሌሎች ስደተኞች ላይ ሊመጣ የሚችለው ችግር ስላሳሰበው" መሆኑንም ገልጿል።

በዚህ ችሎትም ከዚህ ቀደም ለፖሊስ የሰጠውን ምስክርነት በመድገም "ታዳጊዋ ልጅ፣ ልጄ ትሆናለች እኮ፤ ህጻን ናት" ሲል ተናግሯል።

ልጆቹን "በጭራሽ አልነካኋቸውም" ብሏል።

ወሲባዊ ጥቃት አድርሶብኛል ያለችውን ሴት አስመልክቶ ሀዱሽ ምስክርነቱን የሰጠ ሲሆን "ቆንጆ ነህ፤ ቤቴ እንድመጣ እፈልጋለሁ አለችኝ" ሲል ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።

"በጣም ተናዳ ቤቴ ካልመጣህ ተማሪዎችን እያናገርክ ነው፤ ፖሊስ እጠራለሁ አለችኝ" ብሏል።

ወሲባዊ ትንኮሳ አድርሷል በተባለበት ሰኔ 30 ከአንድ ጓደኛው ጋር መንገድ ላይ እየሄደ ልጆቹን እንዳያቸው ገልጿል።

በዚህች ወቅት ታዳጊዎቹን ሊስማቸው ሞክሮ እንደሆነ ተጠይቆ "እኔ እንስሳ አይደለሁም። እንዲህ ዓይነት ነገር አላደርግም። ክርስቲያን ነኝ፤ በባህሌ ውስጥ የለም" ብሏል።

ከታዳጊዎቹ ልጅ መውለድ እፈልጋለሁ ብለሃል ወይ ተብሎ ሲጠየቅ "በፍጹም" በሚል ነበር የመለሰው።

ታዳጊዎቹ ከ18 ዓመት በመሆናቸው በዘገባ ወቅት ስማቸው እንዳይጠቀስ የወጣ መመሪያ አለ።

ወሲባዊ ጥቃት ደርሶብናል ያሉት ታዳጊዎች ሀዱሽ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

በፖሊስ ጣቢያ የሰጡት ምስክርነት ቪዲዮ በችሎቱ ታይቷል።

ታዳጊዎቹ በፍርድ ቤቱ ህንጻ ሌላ ክፍል ውስጥ ሆነው ነው ምስክርነታቸውን የሚሰጡት።

ዐቃቤ ሕግ እና የሐዱሽ ጠበቃ ለታዳጊዎቹ በቪዲዮ በቀጥታ ጥያቄ አቅርበውላቸዋል።

በከተማዋ ማዕከል የትምህርት ቤት ጓደኞች ተሰባስበው ባገኛቸው ወቅት ሀዱሽ ስሙን ቶማስ እንዳላቸው እና 2500 ዩሮ ከፍሎ ዩኬ እንደገባ እንደነገራቸው በስፍራው የነበረ አንድ ታዳጊ ገልጿል።

በተጨማሪም ለአንደኛዋ "አፍሪካ ነይ፤ ጥሩ ሚስት ትሆኛለሽ" እንዳለም ይሄው ታዳጊ ለፍርድ ቤተ አስረድቷል።

ማክሰኞ ዕለት በነበረው ችሎት ከሁለቱ ልጆች ጋር ተቀምጦ የነበረ ጓደኛቸው በሰጠው ምስክርነት "ሃይ ሮድ በተሰኘው ስፍራ ላይ ተቀምጠን ግለሰቡን [ሀዱሽን] አየነው" ብሏል።

"ፒዛ እየበላን ነበር እናም አንድ 'ስላይስ' እንድንሰጠው ጠየቀን። ተነስተን የሆነ ነገር ልናመጣ ሄደን ስንመለስም እዛው ተቀምጦ ነበር።"

"ታዳጊዎቹ ቆንጆ ናቸው እናም ወደ ቤል ሆቴል እንሂድ፤ ልጆች እንውለድ" ሲል መናገሩን ይኸው ታዳጊ ለፍርድ ቤት ተናግሯል።

"አንደኛዋን ልጅ እንድትስመኝ [ሀዱሽ] ጠየቃት ከዚያም ጉንጬን ሳመችኝ፤ እኔንም ሳሚኝ ሲል ጠየቃት "ብሏል።

አክሎም "ትንሽ ቆይቶም፤ ፀጉሯን ሊያሻሽ ሞከረ፤ እንዳውም አሻሽቷታል"

ትንሽ ቆይቶ ወደ ሌላ ወንበር ሄዶ አንዲትን ሴት "ከእሱ ጋር እንድትቀመጥ እና ሥራ እንዲያገኝ ሲቪውን እንዲጽፍ እንድትረዳው እየጠየቃት ነበር" ብሏል።

"ከግለሰቧ ጋር ትንሽ ካወሩ በኋላ ተመልሶ መጣና ከታዳጊዋ ጋር ማውራት ጀመረ።"

"ሴትዮዋ ታዳጊዋን ሰላም ነሽ? ብላ ስትጠይቃት ልጅቷም አይ አይደለሁም፤ [ሀዱሽ] እየነካካኝ ነው አለች። ከዚያም ሰውየው ተስፈንጥሮ ተነሳ፤ ሴትዮዋ ለፖሊስ ስትደውል ተንበርክኮ አዝናለሁ እያለ እየለመነ ነበር" ብሏል።

ይህች ለፖሊስ የደወለችው ሴትዮ ለችሎቱ በሰጠችው ምስክርነት ሀዱሽ እያናገራት በነበረበት ወቅት "እጁን የግራ ጭኗ ላይ አሳርፎት ነበር። እጁን ገፈተርኩት፤ ከዚያም ቆንጆ ነሽ፤ በጣም ቆንጆ ነሽ አለኝ" ብላለች።

"መነካት አልፈልግም አልኩት" ብላለች።

ሆኖም ግለሰቧ ሀዱሸን ልትረዳው ፈልጋ ኢሜይል እና ስልክ ካለው ሲቪውን ልታስተካክልለት እንደምትችል ነገረችው።

ምንም እንደሌለው ሲነግራት ማስታወሻ ልትገዛ ሱቅ ደርሳ ተመልሳ ስትመጣ ልጅቷን እያናገረ እንዳገኘችው አስረድታለች።

"ምን እያደረግክ ነው?" ስትለው መጀመሪያ "ልጅቷ ፈልጋኝ ነው" አለ። ከዚያም ልጅቷ ሌላ ምላሽ ስትሰጠኝ ወደ ፖሊስ ስደውል "ስህተት ነው፤ልሄድ ነው እያለ ነበር" ከዚያም ሮጦ ሄደ ብላለች።

የሀዱሽ ጠበቃ በበኩሏ ግለሰቧ በወቅቱ ብዙ የአልኮል መጠጥ ጠጥታ እንደነበርና እንዲሁም "ጥገኝነት ጠያቂዎች ስለሚያናድዷት ነው" የሚሉና ሌሎች ጉዳዮችን ለምስክሯ በመስቀለኛ ጥያቄ አንስታለች።

ሀዱሽ ጥገኛ ጠያቂ እንደመሆኑ ከዚህ ቀደም በሌሎች ወንጀሎች ስለመከሰሱ የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት እርግጠኛ አለመሆናቸውን ዐቃቤ ሕግ ተናግሯል።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ለነሐሴ 29/ 2017 ዓ.ም ሰጥቷል።