የዲሞክራቲክ ኮንጎ አማጺያን በአሜሪካ ጥያቄ መሠረት የያዟትን ቁልፍ ከተማ ለቀው ሊወጡ ነው

በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚንቀሳቀሰው አማጺ ቡድን መሪ በአሜሪካ ጥያቄ መሠረት ተዋጊዎቹ ቁልፍ የሆነችውን ኡቬራ ከተማን ለቀው እንደሚወጡ ገለጹ።

ኮርኔል ናንጋ ይህን ያሉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኡቬራ በአማጺያኑ መያዟ የሰላም ስምምነትን የሚጥስ እንደሆነ እና ለፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የተገባውን ቃል ለማስጠበቅ አሜሪካ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ከገለጹ ከቀናት በኋላ ነው።

የአማጺያኑ መሪ ናንጋም "እምነት ለመፍጠር" በሚል ተዋጊዎቻቸው ከከተማዋ ለቅቀው እንደሚወጡ ገልጸዋል።

አሜሪካ ሩዋንዳን አማጺያኑን በመደገፍ ትከሳለች።ሩዋንዳ ግን ክሱን ያስተባበለች ቢሆንም ፕሬዝደንቷ ፖል ካጋሜ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ አቻቸው ፌሊክስ ቲሼስኬዲ ጋር በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ በትራምፕ አደራዳሪነት የሰላም ስምምነት ፈርመዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ስምምነቱን "ታሪካዊ" እና "ለአፍሪካ ትልቅ ቀን" ሲሉ አወድሰውታል።

አማጺያኑ በዚህ ሰላም ስምምነቱ ላይ ባይፈርሙም፣ ጎን ለጎን የአሜሪካ አጋር በሆነችው እና ከሩዋንዳ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ባላት ኳታር አማካኝነት በተካሄደ የሰላም ስምምነት ሒደት ላይ ተሳትፈዋል።

ናንጋ አሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት በሩዋንዳ ይደገፋል የሚሉትን ኤም 23ን ጨምሮ የአማጺያን ጥምረት የሆነው የ'አሊያንስ ፍሉቭ ኮንጎ' አስተባባሪ ነው።

የዲሞክራቲክ ኮንጎ ጦር ደግሞ በጎረቤት አገሯ ብሩንዲ ወታደሮች የሚደገፍ ሲሆን፣ ኤም23 ከብሩንዲ ዋና ከተማ ቡጃምቡራ 27 ኪሎ ሜትር የምትርቀውን ኡቬራ ከተማን መቆጣጠሩም ለመንግሥት ጦር ትልቅ ውድቀት ሆኗል።

ኤም23 በአሜሪካ ጥያቄ መሠረት ተዋጊዎቹ ከተማዋን ለቀው እንደሚወጡ ናጋን በሰጠው መግለጫ ላይ ጠቅሷል። ጨምሮም ውሳኔው በኳታር አደራዳሪነት የተካሄደው የሰላም ሒደት ስኬታማ እንዲሆን የተወሰደ የመጨረሻው ጥረት እንደሆነ ገልጿል።

ይህ መቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ባይጠቅስም፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለመቆጣጠር እና የዲሞክራቲክ ኮንጎን ጦር ከይዞታው ውጪ የሆኑ ግዛቶችን መልሶ አንዳይቆጣጠር ለመከላከል "ገለልተኛ ኃይል" እንዲሰማራ ጠይቋል።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳስታወቀው በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ እንደ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት 200 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ቀያቸውን ለቀው ወጥተዋል።

በአብዛኛው ሰላማዊ ሰዎች የሆኑ ቢያንስ 74 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 83 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝም የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።

ምሥራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ላለፉት 30 ዓመታት በግጭት ውስጥ ትገኛለች። ግጭቱን ለማስቆም የተካሄዱ በርካታ የሰላም ጥረቶችም ሳይሳኩ ቀርተዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ያደረገው የሰላም ጥረት እንደሚሰምር እና የአሜሪካ ኩባንያዎች በተፈጥሮ ሃብት በበለጸገችው ኮንጎ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት እንዲያሳድጉ መንገድ እንደሚጠርግ ተስፋ አድርጓል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንደ አውሮፓውያኑ በ2023 እንደገለጸው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 25 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት የማዕድን ክምችት አላት።

ይህም ኮምፒዩተር፣ የኤሌክትሪክ መኪናዎች፣ የስልክ ቀፎዎች፣ የነፋስ ኃይል ማመንጫ እና የጦር መሣሪያ ለመሥራት የሚያገለግሉ ኮባልት፣ መዳብ፣ ሊቲየም፣ ማግኒዢየም እና ታንታለምን ማዕድናትን የሚያካትት ነው።

አማጺ ቡድኑ ትልቅ ግስጋሴ ያሳየው ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በሩዋንዳ ድንበር ላይ የምትገኘውን እና የሰሜን ኪቩ ግዛት መዲና የሆነችውን ጎማ ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ ነበር።

በወቅቱ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች የዲሞክራቲክ ኮንጎን ጦር ለመደገፍ የተሰማሩ ሲሆን፣ ኤም23 ጥር ላይ ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ ለቅቀው ወጥተዋል።

ከዚያም ብዙም ሳይቆይ አማጺው የደቡብ ኪቩ ግዛት ከተማን ቡካቩ እና ኡቬራን መቆጣጠር ችሏል።

የአፀፋ ጥቃቱ የጀመረውም ካጋሜ እና ቲሺስኬዲ ለሰላም ስምምነቱ ወደ ዋሽንግተን ከማቅናታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነበር።