ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰው የሚመስሉ 'ሂውማኖይድ' ሮቦቶችን የመገንባት እሽቅድምድም
በሰው ተክለ ሰውነት እና ባህሪ የሚሠሩ ሮቦቶች (humanoid) ዝነኛ እየሆኑ መጥተዋል።
ጂ1 ከእነዚህ አንዱ ሲሆን፣ የተሠራው በቻይናው ተቋም ዩኒትሪ ነው።
በጀርመን፣ ሀኖቨር የሚገኘው ይህ ሂውማኖይድ ሮቦት 130 ሴንቲሜትር ይረዝማል። ከሌሎች ሮቦቶች አንጻር ዋጋው ተመጣጣኝ ነው።
የሰውነት እንቅስቃሴው ቀልጣፋነት በብዙዎች አድናቆት ተቸሮታል። ይደንሳል፣ ማርሻል አርትም ይችላል።
ጂ1 ቁጥጥር የሚደረግበት በርቀት ላይ ካለ ባለሙያ ነው። ባለሙያው ፔድሮ ዠንግ ይባላል።
ጂ1 የሚገዙ ሰዎች ሮቦቱን በፈለጉት መንገድ ያዋቅራሉ። ጂ1 እንደ ሌሎች ሮቦቶች አይደለም። ሰላምታ ሲሰጠው ይጨብጣል፣ ከወገቡ ዝቅ ብሎም ሰላምታ ያቀርባል። ከተጋጨ ይቅርታ ይጠይቃል።
እንደ ዩኒትሪ ያሉ ብዙ ተቋማት ሂውማኖይድ ሮቦቶች ይሠራሉ።
ሂውማኖይድ ሮቦቶች ከሥራ እረፍት እና የደመወዝ ጭማሪ የማይጠይቁ ሠራተኞች ናቸው።
ሂውማኖይድ ሮቦቶች ገና ከፍተኛው የልኅቀት ደረጃ ላይ አልደረሱ ይሆናል። አሁንም በባለሙያዎች ቁጥጥር እየተደረገባቸው ነው የሚንቀሳቀሱት።
ምግብ ቤት ውስጥ እና በሌላም ቦታ እንዲሠሩ ማድረግ ፈታኝ ይሆናል።
ሂውማኖይድ ሮቦቶች ጠንካራ መሆናቸው ጠቀሜታ ቢኖረውም ድንገት ሰዎች ቢወድቁ ጉዳት ሊያስከትሉም ይችላሉ።
ማሽኖቹን የሚቆጣጠር የሰው ሠራሽ አስተውሎት በአግባቡ መበልጸግም ይጠበቅበታል።
የዩኒትሪ ቃል አቀባይ "የሰው ሠራሽ አስተውሎት ልኅቀት ገና የምፈልገው ደረጃ አልደረሰም። ሮቦቶች ምክንያትን በተወሰነ ደረጃ ቢረዱም ገና ውስብስብ ሐሳብን መገንዘብ ላይ አልደረሱም" ይላሉ።
ጂ1 አሁን ላይ በጥናት ዘርፍ ነው ጥቅም ላይ የሚውለው።
ሂውማኖይድ ሮቦቶች በብዛት በፋብሪካ ውስጥ መሥራት በሚችሉበት መንገድ ነው እየተገነቡ ያሉት።
የኢሎን መስክ ተቋም 'ኦፕቲመስ' የተባለ ሂውማኖይድ ሮቦትን እየገነባ ይገኛል።
"በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ተመሳሳይ ሮቦቶች ይሠራሉ። ጠቃሚ ሥራም ይከውናሉ" ሲል መስክ ከወራት በፊት ተናግሯል።
ከቴስላ መኪና አምራች ውጪ ሌሎች ተቋሞችም ተመሳሳይ ሙከራ እያደረጉ ነው።
ቢኤምደብሊው በአሜሪካ ፋብሪካው ሂውማኖይድ ሮቦቶች አስገብቷል። የደቡብ ኮሪያው ሃዩንዳይም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሂውማኖይድ ሮቦቶችን ከቦስተን ዳይናሚክስ አዟል።
የኤስቲአይኪው መሥራች ቶማስ አንደርሰን እንደሚለው፣ 49 ተቋማት ሂውማኖይድ ሮቦቶች እየገነቡ ነው።
ሂውማኖይድ ሮቦቶቹ እጅ እና እግር ያላቸው ሲሆን፣ በጎማ እየተሽከረከሩም የሚጓዙ ሂውማኖይድ ሮቦቶች የሚሠሩ ተቋማት ደግሞ 100 ይደርሳሉ።
የቻይና ተቋማት ገበያውን ይቆጣጠራሉ ብሎ ያምናል።
"በቻይና ከፍተኛ ፍላጎት አለ። ጥናት እና ምርምር በስፋት የሚደረግበት አገርም ነው" ይላል።
ዩኒትሪ የሠራወ ሮቦት 16,000 ዶላር ይሸጣል።
ሂውማኖይድ ሮቦቶች ላይ ከተደረገ ኢንቨስትመንት 60 በመቶው በእስያ መሆኑን ቶማስ ያስረዳል።
የተቀረው ኢንቨስትመን ያለው በአሜሪካ ውስጥ ነው።
በቻይና ሻንጋይ በመንግሥት የሚደገፍ ሂውማኖይድ ሮቦቶች ማሠልጠኛ ተቋም ተከፍቷል።
በጣም ውስብስብ የሆነ ድርጊት እንዴት መፈጸም እንደሚቻል ሂውማኖይድ ሮቦቶቹ ይማራሉ።
በብሪስትል የሚሠራው በርን ፒርስ፣ ኪንሲ የሚባል ተቋም አለው። ኬአር1 የተባለ ሮቦት ነው የሚያመርተው።
ሮቦቱ በዩናይትድ ኪንግደም ቢሠራም በጅምላ የሚመረተው እስያ ነው።
"የአውሮፓና አሜሪካ ተቋሞች የእስያን ተቋሞች መግዛት ይጠበቅባቸዋል። ሞተር ወይም ባትሪ ብቻ ቢገዛ ሌላው ግብዓት ስለማይኖር ሁሉንም ጠቅልሎ መግዛት የግድ ይሆናል። ስለዚህ ወደ እስያ እንሄዳለን" ይላል በርን።
ዋጋቸው ርካሽ እንዲሆንም በእስያ መሠራታቸው ይረዳል።
ኬአር1 ሮቦቶች እግር የላቸውም።
"እግር መጨመር ተጨማሪ ወጪ ያስፈልገዋል። ያለ እግር ሮቦቱ እየተሽከረከረ መንቀሳቀስ ይችላል" ይላል ባለሙያው።
በኤሌክትሪክ ሳይክል ላይ ያለውን ጎማ የሚመስል ጎማ ለሮቦቱ ይገጠምለታል።
ሁለቱ ሂውማኖይድ ሮቦቶች ተቋማት ፉክክር ውስጥ ናቸው። በሮቦቶቹ መካከል ያለው ልዩነት የሚወሰነው የትኛው የሮቦት ዓይነት ከሰዎች ጋር መሥራት የሚያስችለው መተግበሪያ ተገጥሞለታል የሚለው ሲፈተሽ ነው።
"በቀላሉ አገልግሎት የሚሰጥ ሮቦት ነው የምንሠራወ። የፋብሪካ ሠራተኛ በሁከት ሰዓት ውስጥ እንዴት ሮቦቱን መጠቀም እንደሚችል ይማራል" ይላል በርን።
ኬአር1 የሰዎችን ሥራ በ20 ወይም 30 እጥፍ አሻሽሎ ይሠራል።
ሮቦቶች ከፋብሪካ አገልግሎት ወጥተው በየቤታችን የሚገቡበት ቀን እምብዛም እንደማይርቅ ባለሙያዎቹ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
"ያለፉት 20 ዓመታት ህልሜ ሁሉንም ነገር ሮቦት አድርጎ መሥራት ነው። ቀላል ሥራ አይደለም። ፒኤችዲዬን ሠርቼበታለሁ። ከ10 ወይም 15 ዓመታት በኋላ ሮቦቶች በየቤታችን ይገቡ ይሆናል" ሲል በብሪስትል የሚሠራው በርን ይገልጻል።