ቻይና በኦንላይን አጭበርባሪዎች ላይ የከፈተችው አፈሳ እና በወንጀሉ ላይ የሚሳተፉት በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿ

ጎላ ጎላ ያሉ ዓይኖች ያሉት እጆቹ ላይ ካቴና የታሰረለት በጠባብ እስር ቤት ውስጥ የሚገኘው ግለሰብ "ሊፀፅተኝ ይገባል?" ሲል ጠየቀ።

ግለሰቡ ይህን ያለው እንዲገደል ትዕዛዝ ሰጥቷል ስለተባለበት እንግዳ ሰው ጉዳይ በቻይና መርማሪዎች እየተጠየቀ በነበረበት ወቅት ነው።

'ወንድማማቾች ነን' ሲል ቃለ መሃላ የፈጸመለትን የንግድ አጋሩን መስዋዕት ስላደረገው ሰው ነበር የተጠየቀው።

"እሱ ህያው እና እስትንፋስ ያለው ሰው አልነበረም?" ሲል መርማሪው ይጠይቃል።

ግለሰቡም "እንደዚያ ብዙ አልተሰማኝም" ሲል ምላሽ ሰጠ።

ይህ ምልልስ በቀጥታ ወንጀል ነክ ከሆነ ድራማ ላይ የተገለበጠ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን በቻይና መንግሥታዊ ሚዲያ ላይ የቀረበ ዘጋቢ ፊልም አካል ነው።

የፍትሕ ሥርዓቱ ከሕዝብ ዓይን ተሰውሮ በሚከናወንበት አገር የፍትሕ ሂደቱን ለማየት ያስቻለ ዘገባ ነው።

እጁ በካቴና ታስሮ ለጥያቄዎች መልስ የሚሰጠው ቼን ዳዌይ ይባላል።

የምያንማር የድንበር ከተማ ላውካኪንግ ውስጥ ለዓመታት ያለጠያቂ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት በርካታ ኃይለኛ የማፍያ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው።

የእርሱ የእምነት ክህደት ቃል በቻይና ባለሥልጣናት ለወራት የዘለቀ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አንድ አካል ብቻ ነው።

በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚገኙትን እና በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያጭበረብሩትን ለማስጠንቀቅ እንዲሁም የቻይና መንግሥት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በማጥመድ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመስረቅ ከተሰማራው ኢንደስትሪ ጀርባ ያሉ ሰዎች ላይ የወሰደውን እርምጃ ለማጉላት የቀረበ ነው።

ቻይና ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት "ማንም ብትሆኑ፣ የትም ብትሆኑ በቻይናውያን ላይ ይህን የመሰለ ዘግናኝ ወንጀሎች እስከፈፀማችሁ ድረስ ዋጋ ትከፍላላችሁ" የሚል እንደሆነ አንድ መርማሪ ተናግረዋል።

ወይም የቻይናውያን አባባልን ለመጠቀም "ዝንጀሮውን ለማስፈራራት ዶሮውን ግደሉት" ነው ነገሩ።

ለጥፋቱ መቀጣጫ መሆን

አለቆች ከሚባሉት ከዌይስ፣ ሊየስ፣ ሚንግስ እና ቤይስ፣ ከኢስክ ቤተሰቦች ከፍ ያሉ በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ በላኩካንግ ስማቸው የገነነ ኃያል የወንጀል ቡድኖች አሉ።

በእነርሱ ዘመን በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ የነበረው አካባቢ ወደ ቁማር ቤቶች፣ የመጠጥ እና የወሲብ ንግድ ማዕከልነት ተቀየረ።

በጣም የቅርብ ጊዜዎቹ የማጭበርበሪያ ተቋማት ሰዎችን ከፍላጎታቸው ውጪ በመያዝ፣ የማያውቋቸውን ኦንላይን እንዲያጭበረብሩ በማስገደድ፣ ወይም አሰቃቂ ቅጣት አልፎ ተርፎም ሞት በመፈጸም ይታወቃሉ። ከታሰሩት ውስጥ ብዙዎቹ ቻይናውያን ሲሆኑ ቻይናውያንን ዒላማ የሚያደርጉም ናቸው።

ነገር ግን በ2023 በምያንማር ባለሥልጣናት ተይዘው ለቻይና ተላልፈው ሲሰጡ ቤተሰቡ የገነባው ግዙፍ የወንጀል ቡድን ተንኮታኮተ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቻይና ፍርድ ቤቶች በማጭበርበር፣ በሕገወጥ ሰዎች ዝውውር እና ግድያ ወንጀል ክስ መሥርተውባቸዋል።

አሁን ቤተሰቡ መቀጣጫ እየሆነ ነው።

11 የሚንግ ቡድን አባላት እና አምስት የቤይስ አባላት ሞት የተፈረደባቸው ሲሆን፣ በርካቶች ደግሞ ረጅም እስራት ተፈርዶባቸዋል። በሊየስ እና በቫይስ ላይ የቀረበው ክስ አሁንም እየታየ ነው።

ለሕዝብ በተላለፉ ዘጋቢ ፊልሞች ላይ በእጃቸው ካቴና ገብቶ፣ የእስር ቤት የደንብ ልብስ ለብሰው ሲታዩ አሳፋሪ ውድቀታቸው በግልጽ ይታያል።

ከሁለት ዓመት በፊት ይኖሩ ከነበሩት ሕይወት እጅጉን በጣም የራቀ ነው።

በምያንማር ማጭበርበር የሚፈጽመው ቡድን መነሻ

በአሁኑ ጊዜ የምያንማር ወታደራዊ መንግሥትን የሚመሩት ሚን አንግ ኽላይንግ፣ የከተማይቱን ዋና ዋና የጦር አበጋዞች ከሥልጣን ለማባረር ዘመቻ ከጀመሩ በኋላ የላውካኪንግ አለቆች አቅም እያገኙ ኃይል እያደረጁ መጡ።

ወታደራዊ መሪው አጋሮችን ፈልጎ ነበር እና በወቅቱ የጦር አበጋዙ ምክትል የነበሩት ባይ ሱኦቼንግ ይህንን መስፈርት አሟልተው ተገኙ።

ባይ የላውካኪንግ አውራጃ ሊቀመንበር ሆነው ተሾሙ። በዚህም ቤተሰባቸው 2,000 ሚሊሻዎችን ለማዘዝ ወደ ሥፍራው መንቀሳቀሳቸውን የቻይና ሚዲያ ዘገባ ያሳያል።

በእነዚህ ለውጦች መካከል በተገኘ ክፍተት በጣት የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ሥልጣንን በማግኘት እግራቸውን አስገብተዋል።

እንደ ቻይናውያን መርማሪዎች ከሆነ የዋይ ቤተሰብ አንድ የፓርላማ አባል እና ሌላ የጦር ካምፕ አዛዥ ነበራቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሊየስ እንደ ውሃ እና ኤሌክትሪክ ያሉ ቁልፍ መሠረተ ልማቶችን በመቆጣጠር በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ለዓመታት ገንዘባቸውን በቁማር እና በወሲብ ንግድ ከሚያሰማሯቸው ሴቶች ያገኙ ነበር።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ የበይነ መረብ ማጭበርበር እየሰፋ ሄዷል። እያንዳንዱ ቤተሰብ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚወጡ በደርዘን የሚቆጠሩ የበይነ መረብ ማጭበርበሪያ ተቋማትን እና ቁማር ቤቶችን ይቆጣጠራል።

ቤተሰቦቹ በታላላቅ ድግሶች እና የቅንጦት መኪናዎች መካከል ሲምነሸነሹ፣ ከማጭበርበሪያ ተቋማቱ ጀርባ ኢ-ሞራላዊ የሆኑ ወንጀሎች እየጨመሩ መምጣታቸውን የቻይና ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ነጻ ከወጡ ሠራተኞች የተገኙት የምስክርነት ቃላት ወጥነት ያለው ተደጋጋሚ ማሰቃየቶች፣ ጣትን በቢላ መቁረጥ፣ በኤሌትሪክ መጥበስ እንዲሁም ተደጋጋሚ የሆነ ድብደባ ይፈጸማሉ።

የማይተባበሩ ሠራተኞች በአነስተኛ ጨለማ ቤት ውስጥ ይቆለፍባቸው እና እንዲራቡ ይደረጋሉ፤ ወይንም ፈቃደኛ እስኪሆኑ ድረስ ይደበደባሉ።

የቻይና መንግሥት ጥረት

ብዙዎቹ ቻይናውያን ሠራተኞች ጥሩ በሚከፈልበት ሥራ ተታልለው ወደ በይነ መረብ ማጭበርበር ተግባር መግባታቸውን ይናገራሉ።

በቻይና የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እና በከፍተኛ የወጣቶች ሥራ አጥነት ውስጥ እንዲህ ያሉ አጓጊ ክፍያዎች ፈታኝ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም።

እንደነዚህ ያሉ የማጭበርበሪያ ማዕከላት አስፈሪ ታሪኮች በቻይና በየቀኑ በታክሲ ጉዞ ላይ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ እና መዝናኛ ስፍራዎች ድረስ ዘልቀው ይወራሉ።

በ2023 የተሠራው 'ኖ ሞር ቤትስ' (No More Bets) የተሰኘው እና ቻይናውያን ታግተው በውጭ አገር በሚገኙ የማጭበርበሪያ ተቋማት ሲወሰዱ የሚያሳየው ፊልም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቻይናውያን ቱሪስቶች ከታይላንድ እንዲርቁ አድርጓል።

አገሪቱ በምያንማር እና በካምቦዲያ ውስጥ ወደሚገኙ የማጭበርበሪያ ማዕከላት ለሚወሰዱ ሰዎች መሸጋገሪያ በመሆን ትታወቃለች።

ባለፈው ዓመት በጥር ወር የአገሪቱ ትኩረት በዋንግ ዢንግ ላይ ነበር።

ይህ ቻይናዊ ተዋናይ ለሥራ ወደ ታይላንድ በሄደበት የምያንማር ድንበርን አቋርጦ ወደሚገኝ የማጭበርበሪያ ማዕከል ተወሰደ።

ቤተሰቦቹ ሲያፈላልጉት የነበረው ይህ ተዋናይ ታሪክ በስፋት ከተሠራጨ በኋላ ወደ አገሩ በሰላም መመለስ ችሏል።

ዋንግ ግን ዕድለኛ ከሆኑ ጥቂቶች መካከል አንዱ ነው።

ብዙ ቻይናውያን አሁንም በደቡብ ምሥራቅ እስያ የማጭበርበሪያ ማዕከላት ተወስደው የጠፉ ዘመዶቻቸውን እየፈለጉ ነው።

"የአክስቴ ልጅ ከአራት ወይም ከአምስት ዓመታት በፊት ወደ እዚያ ተታልሎ ሄዶ ነበር። ከዚያ በኋላ ከእርሱ ምንም አልሰማንም። አክስቴ በየቀኑ ታነባለች፤ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ለመግለጽ በጣም ከባድ ነው" ሲል በቻይናውያን ማኅበራዊ ሚዲያ ዌይቦ ላይ ባለፈው ወር ጽፏል።

በሲንጋፖር ዩኒቨርሲቲ በቻይና ፖለቲካ ላይ ትኩረት ያደረጉት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሴሊና ሆ ለቢቢሲ "መንግሥት እየወሰደ ባለውን እርምጃ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ የዜጎቹን ስሜት ለማርገብ እና የተጎጂዎችን ቤተሰቦች ለማረጋጋት አልሟል" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም በዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ማጭበርበሪያ ማዕከላት ታግተው እንደሚገኙ ይገምታል።

ብዙዎቹ የበይነ መረብ የማጭበርበሪያ ማዕከላትን የሚመሩት ሰዎች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ቻይናውያን ናቸው።

ይህ በቻይና ዜጎች ዘንድ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው። በዌይቦ ላይ "አንድ ጊዜ ውጭ አገር ከሆንክ ማመን የሌለብህ የራስህ አገር ሰዎችን ነው" የሚል አስተየየት ሰፍሯል።

በደቡብ ምሥራቅ በሚገኙ የበይነ መረብ ማጭበርበሪያ ተቋማት ላይ መጽሐፍ የጻፈው ኢቫን ፍራንቼሺኒ "ከእነዚህ ሥራዎች ጀርባ የቻይና ዜጎች መኖራቸው አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ገፅታ በእጅጉ የሚጎዳ ነው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

በአገር ውስጥ የዜጎች ጭንቀት እየጨመረ ሲሄድ፣ የቻይና ባለሥልጣናት እነዚህን ግዙፍ የማጭበርበሪያ ተቋማት ለማጥፋት ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ቋምጠዋል።

ከ2023 ጀምሮ የቻይና እና የምያንማር ባለሥልጣናት ከ57,000 በላይ የቻይና ዜጎችን በበይነ መረብ ማጭበርበር ወንጀሎች ላይ ባላቸው ተሳትፎ የተነሳ ማሰራቸውን የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የቻይና ባለሥልጣናት የሚከታተሏቸው የማዕከላቱን አለቆች ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ አድርገዋል።

በጥቅምት ወር ቻይና በላኩካኪንግ እንደ ታዋቂዎቹ የወንጀል ቡድኖች "አደገኛ የሆነ" ሌላ "አዲስ ትውልድ" ስትል የጠራችው ቡድን ላይ ክስ መመሥረቱን አስታውቃለች።

በሌላ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ላይ በቀረበ ዘጋቢ ፊልም ላይ ይህንን የወንጀል ቡድን የመረመረ አንድ የቻይና ባለሥልጣን አለቃው "ይህንን ጉዳይ መፍታት ካልተቻለ በሙያህ ላይ ዘላቂ ጠባሳ ይኖረዋል" ሲል እንዳስጠነቀቀው ገልጿል።

ቻይና የምታደርገውን ጥረት ተከትሎ የመጣው ይፋዊ መረጃ አንዳንድ ብሩህ ተስፋዎችን ይሰጣል።

በቻይና የተዘገቡት የበይነ መረብ ማጭበርበሮች ካለፈው ዓመት ጀምሮ ቀስ በቀስ እየቀነሱ መምጣታቸውን እና ባለሥልጣናቱ እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎችን "በውጤታማነት መከላከል" መቻሉን ተናግረዋል።

አንድ ባለሥልጣን ዘጋቢ ፊልሙን ለሚመለከቱ በምያንማር የበይነ መረብ አጭበርባሪ ቡድኖችን መመርመር "በቻይና ምን ያህል ደስተኛ እንደሆንን እና የደኅንነት ስሜት ለቻይናውያን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ" እንዲገነዘቡ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።