ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምያንማር ውስጥ የሳይበር ማጭበርበሪያ ካምፖችን በመምራት የሚታወቀው ቤተሰብ አባላት በቻይና የሞት ፍርድ ተላለፈባቸው
የቻይና ፍርድ ቤት ምያንማር ውስጥ የበይነ መረብ ማጭበርበር ተግባር ላይ ተሰማርተው በነበሩ አምስት ዋና የውንብድና ቡድን አባላት ላይ የሞት ፍርድ አስተላለፈ።
ባይ የተባለው ቤተሰብ አባላት እና አጋሮች የሆኑ 21 ሰዎች በማጭበርባር፣ በነፍስ ማጥፋት፣ በሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ እና በሌሎች ወንጀሎች የጥፋተኝት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው የቻይና መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ያመለክታል።
ይህ ቤተሰብ በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹ ላይ ኃይላቸውን እያጎለበቱ ከመጡ በጣት የሚቆጠሩ የውንብድና ቡድኖች መካከል አንዱ ነው። ቤተሰቡ፤ በድህነት እና ኋላ ቀርነት ትታወቅ የነበረችውን የምያንማሯን ላውካኢንግ ዞንን ዋነኛ የቁማር እና የወሲብ ንግድ መናኸርያ አድርጓታል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ከተዘዋወሩ በኋላ በኦንላይን የማጭበርበር ተግባር ላይ እንዲሰማሩ ተገድደዋል። በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በሚገኝበት የማጭበርበር ሥራ ላይ በግዳጅ ሠራተኛ ከሆኑት ውስጥ አብዛኛዎቹ ቻይናውያን ናቸው።
በቻይና ፍርድ ቤት የፍርድ ውሳኔ ከተላለፈባቸው አምስት ዋነኛ ሰዎች መካከል የውንብድና ቡድኑ አለቃ ባይ ሱቸንግ እና ልጁ ባይ ዩንግካንግ ይገኙበታል። ያንግ ሊ ቺያን፣ ሁ ሲያውጃንግ እና ቼን ግዋንዩ ቀሪዎቹ ፍርደኞች ናቸው።
ከቤተሰቡ አባላት ውስጥ ሁለቱ የሞት ፍርድ ከተላለፈባቸው በኋላ የቅጣት ውሳኔው ታግዷል። አምስት ሰዎች በዕድሜ ልክ እስራት የተቀጡ ሲሆን ዘጠኝ ሰዎች ከሦስት እስከ 20 ዓመት የሚደርስ እስራት ተፈርዶባቸዋል።
የራሱ ታጣቂ ሚሊሻ ያለው የባይ ቤተሰብ፤ ለሳይበር ማጭበርበር ተግባር እና ለቁማር የሚውሉ 41 ካምፖችን ማቋቋማቸውን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የቤተሰቡ የወንጀል እንቅስቃሴ 4.1 ቢሊዮን ዶላር የሚዘዋወርበት እንደሆነም ተገልጿል። እንደ ቻይና መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ቤተሰቡ ለስድስት ቻይናውያን ሞት፣ ለአንድ ሰው ራስ ማጥፋት እና በበርካታ ሰዎች ላይ ለደረሱ የአካል ጉዳቶች ተጠያቂ ናቸው።
የቻይና ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ይህ ጠንካራ ቅጣት አገሪቱ በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት ውስጥ የተንሰራፋውን የማጭበርበሪያ ካምፖችን መረብ ለመበጣጠስ የምታደርገው ዘመቻ አካል ነው። ውሳኔው በሌሎች የወንጀል ቡድኖችን ዘንድ እንደ ማስጠንቀቂያ እንደሚወሰድም ይጠበቃል።
ባለፈው መስከረም ላይ በተመሳሳይ የቻይና ፍርድ ቤት ላውካኢንግ ዞን በዚሁ ተግባር ላይ በተሰማራ ሚንግ የተባለ ቤተሰብ አባላት ላይ የሞት ፍርድ አስተላልፏል።
ይህ ቤተሰብ በ2000ዎቹ ወደ ኃይል ማማ የወጣው አሁን የምያንማርን ወታደራዊ መንግሥት በሚመሩት ሚን አውግ ህላኢንግ እርዳታ ነው። የአሁኑ ወታደራዊ መሪ ለቤተሰቡ ድጋፍ የሰጠው፤ በወቅቱ በአካባቢው የነበረውን የወንበዴ አለቃ ካስወገደ በኋላ አጋር ለማግኘት ሲያደርግ በነበረው ጥረት ነው።
ምያንማር ውስጥ በወንጀል ቡድንነት ከተደራጁ ቤተሰቦች ውስጥ "ያለ ጥርጥር ቁጥር አንድ" ላይ የሚቀመጥ መሆኑን ልጅየውን ባይ ዩንግካንድ ከዚህ ቀደም ተናግሮ ነበር።