ሕይወት ከጦርነት በኋላ፡ በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ

አቶ ማቴዎስ ገብረሕይወት በመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረ ሲሆን፣ በሚያገኘው ደመወዝ ቤተሰቡን ይደግፍ ነበር።

ሆኖም ላለፉት 19 ወራት ምንም ዓይነት ገቢ አልነበረውም። “በጓደኞቻችን እና በወንድሞቻችን እርዳታ ይህን ክፉ ጊዜ አሳልፈናል” ሲል ስላለበት ሁኔታ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ለሁለት ዓመታት የቆየው አውዳሚው ጦርነት እና እሱን ተከትሎ በፌዴራል መንግሥት በተጣለው እገዳ ምክንያት በክልሉ ሁሉም መሠረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጦ ቆይቷል።

ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ እነሆ ሁለት ወር አልፎታል።

ብዙዎች በሰላሙ ስምምነቱ ላይ ተስፋ የሰነቁ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በጥርጣሬ እና በስጋት ይመለከቱታል።

የሰላም ስምምነቱ ተከትሎ መሠረታዊ አገልግሎቶች እየተጀመሩ ሲሆን፣ በነዋሪዎች ሕይወት ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል? ብለን አንዳንድ ነዋሪዎችን እና የመንግሥት ሠራተኞችን ጠይቀናል።

የመንግሥት ተቋማትና ሠራተኞች

የፌዴራል መንግሥት ሠራተኛ የሆነው አቶ ማቴዎስ “ደግነቱ ጦርነት እና ስለ ጦርነት ወሬ መስማት ጋብ ብሏል። ከዚያ ውጪ ግን በሕይወታችን ላይ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፤ እስካሁን የት ናችሁ ብሎ የጠየቀን የለም” ብለዋል።

አቶ ማቴዎስ የሰላም ስምምነቱን መፈረም ተከትሎ ለሁለት ዓመታት በችግር ላይ የቆዩት የመንግሥት ሠራተኞች እና በአጠቃላይ የከተማው ነዋሪ በአሁኑ ወቅት ወደ መደበኛ ሥራቸው ይመለሳሉ ብሎ ጠብቆ ነበር። ያ ግን አልሆነም።

የአይደር ሆስፒታል ክሊኒካል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አብርሃ ገ/እግዚአብሔር በበበኩላቸው “ሠራተኛው ወደ መደበኛ የሥራ ገበታው ይመለሳል፤ እንዲሁም ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለን ጠብቀን ነበር” ብለዋል።

የሆስፒታሉ በጀት ይለቀቃል ብለው ገምተው የነበረ ቢሆንም እስከ አሁን ስለ የሆስፒታሉም ሆነ የክልሉ ባጀት የተባለ ነገር የለም።

በክልሉ ከ200,000 በላይ የመንግሥት ሠራተኞች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል። እነዚህ ሠራተኞች በጦርነቱ ወቅት ለከፍተኛ ችግር እና ረሃብ ተጋልጠው መቆየታቸውን ይናገራሉ።

ስምምነቱ ተከትሎ በአንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች ከረዥም ጊዜ በኋላ የመብራት፣ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች መልሰው ሥራ ጀምረዋል።

መቀለ፣ አዲግራት፣ ሽረ፣ አክሱም፣ አድዋ እና አላማጣ ተጠቃሚ ከሆኑ ከተሞች መካከል ናቸው።

በዚህም መሰረት ብዙዎች ከሁለት ዓመት በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ መገናኘት ችለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች አገልግሎቱ ወደ ክልሉ ሙሉ ለሙሉ እንዲዳረስና መቆራረጥ እንዳይገጥመው ይማጸናሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም በረራውን በመቀለ እና ሽረ የጀመረ ሲሆን በርካቶችን ወደ ክልሉ በማጓጓዝ ላይ ይገኛል።

“ኑሯችን አልተለወጠም”

ማቴዎስ ጦርነት ከመቆሙ ውጪ በኑሮው እስካሁን የተለወጠ ነገር እንደሌለ “በእርግጥ የቤተሰቦቼን እና የጓደኞቼን ድምጽ ሰምቻለሁ፤ ጦርነት እና የጦርነት ወሬም ጋብ ብሏል” ይላል።

ከዚህ ውጪ ግን ገበያው ገና አልተሻሻለም በትግራይ ከተሞች መካከል የሕዝብ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተጀመረ እና “በየብስ የሚገቡ እና የሚወጡ ነገሮች የሉም፤ ገና ብዙ የሚቀሩ ነገሮች” ሲልም ያክላል።

በተለይም ወደ ክልሉ የሚገባው ነዳጅ በቂ ባለመሆኑ እና ዋጋው ከፍተኛ በመሆኑ፣ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ አለመጀመሩን ጨምሮ ገልጿል።

በዚህም ሳቢያ ማቴዎስ አዲግራት ከተማ የሚኖሩ ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ በትራንስፖርት ውድነት ምክንያት መሄድ እንዳልቻለ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከጦርነቱ በፊት ከመቀሌ ወደ ቀርቧ ከተማ ውቅሮ ለመጓዝ 30 ብር ይከፈል የነበር ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን 150 ብር ያስከፍላል።

አቶ ማቴዎች በክልሉ ባለው የትራንስፖረት ዋጋ ውድነት የተነሳ ከመቀሌ እስከ ሽረ፣ አድዋ እና አክሱም ድረስ ቤተሰቦቻቸውን መጠየቅ እንዳልቻሉ ይገልጻል።

የትግራይን ክልል ከአማራ እና አፋር ክልሎች ጋር የሚያገናኙ አውራ መንገዶች ለሕዝብ ትራንስፖረት ክፍት ባለመሆናቸው የተነሳ እንደፈለጉት ተንቀሳቅሰው መገበያየት እንዳልቻሉ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከክልሉ ውጪ በየብስ የሚደረግ የሕዝብ ትራንስፖርት ባለመጀመሩ፣ በአንጻራዊነት ገንዘብ ያላቸው የክልሉ ነዋሪዎች በአውሮፕላን ከክልሉ ወጥተው መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

“የሚጠበቀውን ያህል እየሰራን አይደለም”

ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደሚሉት ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በክልሉ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሆስፒታሎች እና የሕክምና ማዕከላት ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል።

እነዚህ ማዕከላት ምንም ዓይነት የሕክምና አገልግሎት መስጠት በማይችሉበት ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ በጦርነቱ የወደሙትን የህክምና ማዕከላት መሠረተ ልማት እና የህክምና ቁሳቁሶች ለመጠገን ቢያንስ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ጥር 04/2010 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

አክለውም ጦርነቱ ካበቃ በኋላ በርካታ የሕክምና ማዕከላት ተከፍተው ለሠራተኞች ደሞዝ መክፈል መጀመራቸውንም ተናግረዋል።

እስካሁንም በመጀመሪያው ዙር ከ79 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ መድኃኒቶች እና የህክምና መሳሪያዎች ወደ ክልሉ ተጓጉዘዋል ብለዋል።

ዶክተሮች እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግን ምንም እንኳን አንዳንድ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ የሕክምና ማዕከሎቹ አሁንም በጥሩ ሁኔታ ላይ አይደሉም።

በትግራይ ውስጥ ትልቁ ሪፈራል ሆስፒታል እና ባለቤትነቱ የፌደራል የሆነው ዓይደር ሆስፒታል ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብርሃ ገ/እግዚአብሔር “ሆስፒታሉ በጦርነቱ ወቅት ከነበረው በባሰ ሁኔታ” ላይ እንደሚገኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በአጠቃላይ ሁኔታው ​​እንደጠበቅነው አይደለም። ለምሳሌ በመደበኛ ጊዜ እስከ 96 የላብራቶሪ ምርመራዎችን እናደርግ ነበር። ዛሬ ግን አንድ ዓይነት የላብራቶሪ ምርመራ ብቻ ነው የምናደርገው።”

ለዚህም ምክንያቱ፣ ለላብራቶሪ ሥራ የሚያስፈልጉ የኬሚካል እና የመመርመሪያ መሳሪያዎች እጥረት በመኖሩ ነው ብለዋል።

በመድኃኒት ረገድም ከአንዳንድ በውጭ ከሚገኙ የክልሉ ተወላጆች በእርዳታ ያገኙትን መድኃኒቶች ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

እንደ የደም ግፊት፣ የልብ ሕመም፣ የአእምሮ ሕመም እና ካንሰር ያሉ ሥር የሰደዱ በሽታዎች ሕክምናዎች ከሞላ ጎደል ቆመዋል ሲሉ ያክላሉ።

የወባ በሽታ መድኃኒት እስካሁን ወደ ሆስፒታሉ እንዳልደረሰ፣ ነገር ግን በቅርቡ ለኢትዮጵያ መድኃኒት ኤጀንሲ ጥያቄ እንደሚያቀርቡም ተናግረዋል።

የእርግዝና መከላከያ እና ሌሎች ከእርግዝና ጋር የተያያዙ መድኃኒቶችም አይገኙም ብለዋል።

ዶ/ር ሊያ ግን የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ 81 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ መድኃኒቶች ወደ ከተማዋ ገብተዋል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በበኩሉ ለክልሉ 15 አምቡላንስ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ዶ/ር ሊያ ታደሰ እና ምክትላቸው ዶ/ር ደረጀ ዱጉማን ተጨማሪ ጥያቄዎች ይዘን፤ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

“ከማዕከላዊ ባንክ ምንም ገንዘብ አላገኘንም”

ማቴዎስ በአሁኑ ጊዜ የስልክ እና የኢንተርኔት አገለግሎቶች በተወሰኑ ከተሞች ውስጥ አገለግሎት በመጀመራቸው ደስተኛ መሆኑን ይናገራል።

“በአዎንታዊነት ላነሳቸው የምችላቸው ነገሮች እነዚህ ብቻ ናቸው። ለምሳሌ እኔ የመንግሥት ሠራተኛ ነኝ። ላለፉት 19 ወራት ምንም ደሞዝ አላገኘሁም። እስካሁን የት እንዳለን የጠየቀን አካል የለም።”

ያለውንም ገንዘብ ቢሆን ከባንክ አውጥቶ መጠቀም እንዳልቻለ ተናግሯል።

እርግጥ ነው፣ ሁለት የግል ባንኮች በመቀለ ከተማ ሥራ ጀመረዋል። ሆኖም ማቴዎስ እና ሌሎች ብዙዎች ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነበር ያስቀመጡት።

ባንኩ ደግሞ እስካሁን ከሽረ ከተማ ውጪ መስራት አልጀመረም።

ባለፈው ሳምንት በከተማው ሥራ የጀመሩት የወጋገን እና አንበሳ ባንኮች ቢሆኑም፣ ለአንድ ደንበኛ በቀን 2,000 ብር ብቻ ይሰጣሉ።

ነዋሪዎችም ይህ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን በማንሳት ያማርራሉ።

የመቀሌ ከተማ ነዋሪ የሆነው ፀጋይ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ እንደተናገረው ከባንኩ 10 ሺህ ብር ለማውጣት ቢፈልግም በቀን 2,000 ብር ብቻ እንዲያወጣ ተፈቅዶለታል።

የሚፈልገውን ገንዘብ ለማግኘትም ለአምስት ተከታታእ ቀናት መመላለስ እንዳለበት እና ለተጨማሪ የትራንስፖርት ወጪ መዳረጉን ተናግሯል።

የወጋገን ባንክ የመቀለ ዲስትሪክት ኃላፊ አቶ ሃፍቶም ገ/እግዚአብሔር፣ ባንኩ በመቀለ ብቻ 28 ቅርንጫፎች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው ሁሉም አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ይናገራሉ።

አቶ ሃፍቶም አክለውም እስካሁን ከብሔራዊ ባንክ ምንም አይነት የገንዘብ ፈሰስ እንዳልተደረገላቸው ገልፀዋል።

“ስለዚህም ደንበኛችን የፈለገውን ያህል ገንዘብ አያገኝም። ነገር ግን የበዓል ወቅት ስለሆነ እና ማኅበራዊ ኃላፊነት ስላለብን አንድ ኪሎ ሥጋ የሚያስገዛም ቢሆን እንስጥ ብለን ነው የጀመርነው” ብለዋል።።

“ከማዕከሉ ምንም ገንዘብ እስካሁን አልደረሰንም። ከደንበኞቻችን ገቢ የሆነውን ገንዘብን ነው እያከፋፈልን ያለነው። ከደንበኞቻችን ወይም ከማዕከሉ ገቢ ካገኘን ወደ 10,000 እና 50,000 ከፍ እናደርገዋለን” ብለዋል።

እንደ ሞባይል ባንክ እና ኤቲኤም ያሉ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶች እስካሁን ሥራ አለመጀመራቸውንም አቶ ሃፍቶም ተናግረዋል።

በክልሉ ውስጥ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ውድመት በመድረሱ የተለያዩ አገልግሎቶች በፍጥነት ወደ ሥራ ላለመግባታቸው ምክንያት እንደሆነ ባለሥልጣናት መናገራቸው ይታወቃል።