የኪሊያን ምባፔ መጨረሻ የት ይሆን? ሪያል ማድሪድ ወይስ ሳዑዲ አረቢያ?

የክረምቱ ወራት የዝውውር ወሬ በኪሊያን ምባፔ ስም ተውጧል።

የፈረንሳዩ አምበል ውሉን ለማራዘም አሻፈረኝ ማለቱን ተከትሎ ፓሪ ሳን ዠርማ ተጫዋቹን በውድ ዋጋ ሊሸጠው የተዘጋጀ ይመስላል።

የሳዑዲ አረቢያው አል-ሂላል፣ ምባፔን በ259 ሚሊዮን ረብጣ ፓውንድ ልገዛ ዝግጁ ነኝ ማለቱ የስፖርቱን ዓለም ያናወጠ ዜና ሆኗል።

ለመሆኑ የምባፔ መጨረሻ የት ይሆን? የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግን ትቶ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናል? ወይስ በነፃ ይዘዋወር ይሆን?

እዚህ እንዴት ደረስን?

ምባፔ መጀመሪያ ከሞናኮ በ2017 (እአአ) ወደ ፒኤስጂ ያቀናው በውሰት ነበር። ቀጥሎ 166 ሚሊዮን ባወጣ ዝውውር ክለቡን በዘላቂነት ተቀላቀለ።

ምባፔ ለፒኤስ ጂ በ260 ጨዋታዎች 212 ጎሎች በማስቆጠር ክብረ-ወሰን ጨብጧል።

ምንም እንኳ በአገር ውስጥ ሊግ ተወዳዳሪ የሌለው ተፅዕኖ መፍጠር ቢችልም፤ ምባፔን ጨምሮ ኔይማር እና ሜሲን ቢያስፈርምም፤ የኳታር ባለሃብቶች ንብረት የሆነው ፒኤስጂ የአውሮፓ ዋንጫን ማንሳት ከብዶታል።

ምባፔ የገባው ውል ከክለቡ ጋር በፈረንጆቹ እስከ 2024 የሚያቆየው ነው። ነገር ግን ባለፈው ወር ክለቡን መልቀቅ እንደሚሻ፤ ቢቆይ እንኳ ውሉ እስኪጠናቀቅ እንደሆነ ተዘገበ።

ክለቡ ለቅደመ ውድድር ዘመን ዝግጅት ወደ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ሲያቀና ምባፔን ሳይጭን በረረ።

ፒኤስጂ በጃፓኗ ኦሳካ ከተማ ከክሪስቲያኖ ሮናልዶ ክለብ አል-ናሲር ጋር በነበረው የወዳጅነት ጨዋታ ያለጎል አቻ ተለያየ።

ከጨዋታው በኋላ አስተያየት የሰጠው ተከላካዩ ዳኒሎ ፔሬራ “ምባፔ ታላቅ ተጫዋች ነው። ነገር ግን አብሮን አልመጣም” ሲል የተሰማውን ገልጿል።

“ይህ የክለቡ ውሳኔ ነው። እኔ አስተያየት መስጠት አልችልም።”

የፒኤስጂው ሊቀ-መንበር ናስር አል-ኼላይፋ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲሚወስዱ እና ምናልባት ምባፔ እምቢኝ ማለቱን ከቀጠለ በሚቀጥለው ዓመት ተቀያሪ ወንበር ላይ እንደሚያስቀምጡት ጠቆሙ።

የፈረንሳዩ ክለብ የሳዑዲ አረቢያ ሕዝብ ኢንቨስትመንት ፈንድ ንብረት የሆነው አል-ሂላል፤ ምባፔን እንዲያናግረው ፈቃድ ሰጥቷል።

ፒኤስጂ የአውሮፓ ክለቦች ምባፔን ለመግዛት እንዲጫረቱ ይፈልጋል።

ምባፔ ወደ ሳዑዲ ቢሄድ ምን ያህል ይከፈለዋል?

ፈረንሳዊቷ የእግር ኳስ ጋዜጠኛ ሊሳ ሌሮ፤ የቀረበው 259 ሚሊዮን ፓውንድ “ተጫዋቹ በዘመናት አንዴ ብቅ የሚል መሆኑን ማሳያ ነው። ነገር ግን ይሄ ጉዳይ ለእርሱ የገንዘብ ጉዳይ ስላልሆነ ይሄዳል ብዬ አላስብም” ትላለች።

ምባፔ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሄድ ከወሰነ በዓመት 177 ሚሊዮን ፓውንድ የሚያገኘውን ክሪስቲያኖ ሮናልዶን በመብለጥ የዓለማችን ውዱ ተከፋይ ተጫዋች ይሆናል።

እንደዘገባዎች ከሆነ የምባፔ ዓመታዊ ገቢ 602 ሚሊዮን ፓውንድ ሆኖ፣ ከምስል መብት እና ከማስታወቂያ ተጨማሪ ገቢ ሊያገኝ ይችላል።

“በእግር ኳስ ታሪክ የትኛውም ተጫዋች ይህን ያህል ገንዘብ ቀርቦለት አያውቅም። ኧረ እንዲያውም በስፖርት ታሪክ ይህ ታይቶ አይታወቅም” ትላለች ሌሮ።

“ይህ ማለት ተጫዋቹ በወር 59 ሚሊዮን ዩሮ ያገኛል። በቀን 2 ሚሊዮን ዩሮ እንደማለት ነው።”

ሌላኛው ፈረንሳዊ የእግር ኳስ ተንታኝ ጁሊየን ሎረንስ እንዲሁ በተመሳሳይ ምባፔ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ያቀናል ብሎ አያስብም።

“ምንም እንኳ ፒኤስጂ፤ ተጫዋቹን አል-ሂላል እንዲያናግር ፈቃድ ሰጥተናል ቢልም፣ እሱ እንደማይፈልግ ያውቃሉ። ለእሱ ገንዘብ ጉዳዩ አይለም” ሲል ለቢቢሲ ራድዮ 5 ይናገራል።

ሳዑዲ ካልሆነ ወዴት?

ሪያል ማድሪድ ለረዥም ጊዜ ተጫዋቹን ለማስፈረም እንደሚሻ ገልጧል። እንዲያውም ከፒኤስጂ ጋር የገባውን ውል ከማራዘሙ በፊት የስፔኑን ክለብ ሊቀላቀል ከጫፍ ደርሶ ነበር።

ነገር ግን እሱ በያዝነው የክረምት የዝውውር መስኮት ወደ ሪያል ማድሪድ ሊያቀና ይችላል ተብሎ የሚወራው “ሐሰት ነው” ይላል።

ቼልሲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ቶተንሃም፣ ኢንተር ሚላን እና ባርሴሎና ፍላጎታቸውን ከገለጡ ክለቦች መካከል ናቸው።

ፒኤስጂ ምናልባት ምባፔ በውሰት ወደ ሌላ ክለብ አቅንቶ ውሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ቢቆይ ቅር እንደማይለው ጋዜጦች ዘግበዋል።

ይህ ማለት ምባፔ ከ12 ወራት በኋላ በነፃ ሪያል ማድሪድን ቢቀላቀልም፣ እስከዚያው ድረስ በውሰት ለፒኤስጂ ገንዘብ ያስገኛል።

ነገር ግን ባርሴሎና በዓመት 72 ሚሊዮን ዩሮ የሚያገኘው የምባፔን ወጪ መሸፈን ባይችል እንኳ በርካታ ተጫዋቾቹን ለፒኤስጂ ለማቅረብ ቃል ገብተዋል ይላል ጁሊየን።

ተንታኙ እንደሚለው ሪያል ማድሪድ ተጫዋቹን በሚቀጥለው ዓመት በነፃ ለማዘዋወር ከሚጠብቅ ይልቅ በያዝነው ክረምት ቢያስፈርመው ይሻላል።

ምባፔ በሚቀጥለው ዓመት ውሉ ተጠናቆ በነፃ ለገበያ ቢቀርብም ክለቦች የእሱን ደመወዝ እና ሌሎች ወጪዎች ለመሸፈን መረባረባቸው አይቀርም።

የሳዑዲ ክለቦች ገንዘብ እንደፈቀዳቸው ማውጣት ይችላሉ?

ወርሃ ሰኔ አራቱ የሳዑዲ ክለቦች ማለትም አል-ኢቲሃድ፣ አል-ሂላል፣ አል-ናስር እና አል-ኢህላል የአገሪቱ የሕዝብ ኢንቨስትመንት ፈንድ ንብረት ሆነዋል።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቡ ኒውካስልም የዚህ ፈንድ ንብረት ነው።

ፖርቹጋላዊው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሊግ ካቀና ጀምሮ የሳዑዲ ፕሮ ሊግ 18 ክለቦች የተጫዋች ግዢውን አጧጡፈውታል።

ካሪም ቤንዜማ፣ ንጎሎ ካንቴ፣ ሩበን ኔቬስ እና ጆርዳን ሄንደርሰንን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ እግር ኳስ ፈርጦች ወደ ሳዑዲ አቅንተዋል።

ፋይናንሻል ፌር ፕሌይ የተሰኘው ሕግ የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ከገቢያቸው በላይ ወጪ እንዳያደርጉ የሚያደርግ ነው።

ይህ ሕግ ለሳዑዲ አይሠራም። የሳዑዲ ፕሮ ሊግ የእስያ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አባል ነው። ይህ ሕግ በእስያ አይሠራም የሚለው የእግር ኳስ ተንታኙ ኪየራን ማጓየር ነው።

“የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች የፈለገ ገንዘብ ቢያቀርቡ የሳዑዲ ክለቦችን ያክል አቅም የላቸውም።”