19 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ያሳለፈው ሳላዲን ስለ እግር ኳስ ሕይወቱ ምን ይላል?

ሳላሃዲን ሠዒድ የእግር ኳስ ፍቅሩን የወሰደው ከቤተሰቡ እንደሆነ ይናገራል። አባቱ ለጅማ ከተማ ተጫዋች ነበሩ። ታላቅ ወንድሙ ለቡና የእግር ኳስ ቡድን እንዲሁም የመን ውስጥ ለሚገኝ ቡድን መጫወቱን ይናገራል። ሳልሀዲን የ12 ዓመት ታዳጊ እያለ በፕሮጀክት ታቅፎ ከ13 ዓመት በታች መጫወት ጀመረ። በ1996 የሙገር እግር ኳስ ክለብ ቢ ቡደንን ተቀላቅሎ ለኢትዮፕያውያን እግር ኳስ አድናቂዎች ተዋወቀ። ከዚያ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሲዳማ ቡና ተጫውቷል። በዋናው ፕሪሚየር ሊግ ወደ 19 ዓመት ገደማ በተጫዋችነት ያሳለፈው ሳልሀዲን ሠዒድ አራት የውጪ አገራት በመሄድ ተጫውቷል። ቢቢሲ እግር ኳስ በቃኝ ያለውን ሳላሃዲን ሠዒድን በስልክ አናግሮታል።

እግር ኳስን ለማቆም የወሰንክበት ምክንያት ለምንድን ነው?

ሳልሀዲን ሠዒድ- እያሰብኩበት ነው። ተደጋጋሚ ጉዳትም አለ ከበፊት ጀምሮ። ያው በዚህ ዓመት [ለማቆም] ወስኜ ነበረ። የተለየ ምክንያት ግን የለኝም።

የነበረብህ ጉዳት እንደ ልብ እንዳትጫወት ምክንያት ሆኗል?

ሳልሀዲን ሠዒድ- ያው እርሱም አለ፤ ነገር ግን በጣም ረዥም ዓመት ተጫውቻለሁ። እግር ኳስ ከውጪ እንደሚባለው አይደለም። ተራራ መሮጥ አለብህ። ጊዜህን መስጠት አለብህ። ያ ደግሞ ቤተሰብ ሲመጣ ከውጪም ስራዎች ስትጀምር ትንሽ ትቸገራለህ። ሌላው ጊዜውም ነው ብዬ ነው የማስበው። እና ያያ ነው።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ ስም ካላቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነህ። እስካሁን በነበረህ የእግር ኳስ ሕይወት ውስጥ የማትረሳው እና የኔ ወርቃማ ጊዜ ነው ብለህ የምትጠቅሰው ጊዜ የቱ ነው?

ሳላዲን ሰይድ- ብዙ አለ። እንደ ግሌ አስቸጋሪ ጊዜን አሳልፌያለሁ በእግር ኳስ ውስጥ። ከዚያ ውስጥ ተቀጥቼ በነበረበት ወቅት አንድ ዓመት ሙሉ አርፌ ነበር ከውድድር።

ለምን ነበር የተቀጣሀው?

ሳልሀዲን ሠዒድ- 2003 ዓ.ም ላይ ነበር የተቀጣሁት፤ ዳኛ ጋር በተፈጠረ ግብግብ እኔ፣ አዳነ ግርማ እና ሚኪ ጣልያን የሚባል ተጫዋች ነበር ሦስታችንን ነበር የቀጡን። በሰዓቱ ቅጣቱም አግባብ አልነበረም። የተደረገው ነገር እና ቅጣቱ ተመጣጣኝ አልነበረም። አንድ ዓመት ለእኔ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር። ያም ሆኖ ግን ልምምዴን አልሀምዱሊላህ ጠንክሬ እሰራ ነበር። ከዚያም አልፎ ከውጪ ሰዎች ጋር ግንኙነት ፈጥሬ ሰርቢያ ሄጄ ከውጪ ቡድን ጋር ነበር ስሰራ የነበረው። እኔ ያን ጊዜ አሳልፌ መጥቼ በተመለስኩ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብሔራዊ ቡድን ከናይጄርያ ጋር ግጥሚያ ነበረብን። እርሱ ጨዋታ ላይ ተሳትፌ ሁለት እኩል ወጥተን ነበር። ሁለት ጎል ያገባሁት እኔ ነበርኩ። ሌላ ደግሞ እንደ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ሱዳንን እዚህ ሁለት ለባዶ አሸንፈን ስናልፍ ለኔ ልዩ ጊዜ ነበር። እነዚህ ሁለቱ የማልረሳቸው ጊዜያቶች ናቸው።

በፕሮፌሽናል ተዋችነት ዘመንህ ፈታኝ ጊዜያቶች ያሳለፍካቸው የትኞቹ ናቸው?

ሳልሀዲን ሠዒድ- መጀመሪያ ላይ እንዳልኩህ ጉዳቶች ነበሩብኝ። አውሮፓ ሂጄ ተጫውቻለሁ። አልሀሊ ገብቼ ተጫውቻለሁ። ግብጽም ብትሄድ ቤልጅየምም ብትሄድ ሕክምናቸው ጣሪያ የነካ ነው። ሕክምና ታገኛለህ። ያም ሆኖ ግን እዚያም ጉዳት ያስቸግረኝ ነበር። ሕልሜ ትልቅ ነበር፤ ሕልሜ ከአልሀሊም በላይ ነበር። እና አልሀሊ ስገባ አልተቸገርኩም። ተጫዋቾቹን ሳይ ምንም የተለየ ነገር የላቸውም። ያው ለኳስ ልቦናህ ንፁህ መሆን አለበት። ከዚያ በኋላ ደግሞ ጥረት ሲታከልበት ስኬታማ ትሆናለህ፥ እዚያም ጉዳት ነው ያስቸገረኝ እና ያ ጉዳት ባይኖር እንግዲህ የተሻለ ቦታ እደርሳለሁ ብዬ ነበር የማስበው። እንዳሰብኩት አላደረገኝም ያ ጉዳት። እና ያ ነው ያሰብኩት ደረጃ አልደረስኩም ብዬ የማስበው።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተሳተፍክባቸው ጨዋታዎች ግብ ታስቆጥር ነበር። ነገር ግን እንዳልከው በተደጋጋሚ ጉዳት ታስተናግዳለህ። ለምንድን ነው? ጥንቃቄ ስለማታደርግ ነው ወይስ. . .

ሳላሃዲን ሠዒድ- ሊሆን ይችላል። ከትንሽም ከትልቅም ቡድን ጋር ስንጫወት ያለኝን እሰጣለሁ። ምክንያቱም ስራ ይከፍለኛል ብዬ ስለማምን ያለኝን እሰጣለሁ፤ አልቆጥብም። አንድ እርሱ ይመስለኛል። ጉዳት ሲባል እኮ እንደ ሰው ትራመዳለህ፤ ትሄዳለህ። ምንም ሕመሙ ያን ያክል አይደለም። ጉዳት ሲባል አትሯሯጥም። አትዘልም። ከዚያ በላይ ምንድን ነው እግር ኳስ ተጫዋች ሲጎዳ፣ . . . ጉዳት የሚባለው ምን መሰለህ በሦስት ወር ወይንም በአራት ወር ያመጣውን በልምምድ በጨዋታ ያጠራቀመውን ዜሮ እንደመግባት. . . እንደዚያ ነው። ከዚያ በኋላ ከዜሮ ነው የምትነሳው። ሰውነትህ ሟሙቶ ነው የሚነሳው። ከጉዳት ልታገግም ትችላለህ። ነገር ግን ያ ብቃት ላይ ለመድረስ ያሳለፍከውን ጊዜ፣ ያንን ሁሉ ልምምድ መስራት ይጠበቅብሀል። ቶሎ ለመድረስ ደግሞ ተጨማሪ ልምምዶችን ትሰራለህ። እና ጉዳት ሲባል የአካልም ብቻ ሳይሆን አእምሮም ጭምር ነው የሚጎዳው። እና ያ ነው ከባድ የሚያደርገው።

ጉዳቶችንም እያስተናገድክ ቢሆንም ለአገር እንዲሁም ለተሰልፍክባቸው ቡድኖች አስተዋጽኦዎችን አበርክተሃል። የመጀመያውን ያስተናገድከውን ጉዳት ታስታውሰዋለህ?

ሳላሃዲን ሠዒድ- ሙገር ነበር፤ እጄ ነበር የተሰበረው። ጄሶ ለስድስት ሳምንት ወይንም ለሦስት ወር አካባቢ ታስሮልኝ ነበር። አጋጣሚ ጀሶውን የቡና ወጌሻ የሆነው፣ ይስሃቅ የሚባል፣ በስፖርቱ ቤተሰብ ዘንድ ይታወቃል . . . . . እርሱ ጋር ስሄድ ያንን በሁለት ሳምንት ውስጥ ፈትቶልኝ ባደረገልኝ ሕክምና በሀያ ቀን ውስጥ ተመልሻለሁ። እርሱ ነበር የመጀመሪያ ጉዳቴ፣ ሌሎችም ጉልበት ላይ ቀዶ ህክምና አድርጌያለሁ። ጀርባዬ ላይም ትንሽ ጉዳት አለ። ረዥም ጊዜ ያለው እርሱ ነው። ጡንቻዎቼ ላይ ደግሞ በተደጋጋሚ ነው የሚመላለሰው። አንድ ጨዋታ ትጫወታለህ፥ ጥሩ ትሆናለህ፣ ብቃትህ እስኪመጣ ትንሽ ትቸገር ይሆናል፤ እና ደግሞ ድጋሚ ትጎዳለህ። እና በዚህ ዓመት ብቻ ሁለት ጊዜ ነው የተጎዳሁት። ያ ያ እንደፈለግክ እንዳትሆን ያደርግሃል። እድሜህ በጨመረ ቁጥር ደግሞ ከጉዳትህ ዜሮ ገብተህ ብቃትህን ለመመለስ በጣም ጊዜ ያስፈልግሃል። ጌሞች ያስፈልጉሃል። ጌም ላይ ደግሞ እንግዲህ ውጤት ይጠበቃል። እና ሁሌ አክቲቭ የሆነ ተጫዋች ነው የሚፈለገው እና ቦታህ ላይ ያለውም ውድድር እየሰፋብህ ይሄዳል። እና እነዚያ ነገሮች እያስቸገሩኝ ነበር።

ሰርብያ፣ ግብጽ፣ አልጄያ እና ቤልጂየም ተጫውተል። በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በርካታ አገራት ተዘዋውሮ የተጫወተ እና ልምድ ያገኘህ ተጫዋች ነህ። በግልህ በእነዚህ አገራት በነበረህ ቆይታ ምን ልምድ አገኘህ?

ሳላሃዲን ሠዒድ- እኔ ያየሁትን በተለይ አሁን ያሉ ታዳጊዎች ቢያዩ ደስ ይለኛል። ወይ ደግሞ እዚህ ሙያ ላይ ያለ ሰው ቢያይ ደስ ይለኛል። . . . እኔ አሁን አልሃሊ ስገባ ቡድኑ በጣም ግዙፍ ነው። ገብቼ ከእኔ ጋር የሚጫወቱ አጥቂዎቹን ሳይ፣ ልምምድ ላይ የምናደርገውን ሳይ፣ በቃ እግር ኳስ የሚፈልገው ቅን ልቡና ነው። ትልቁ ትምህርት የተማርኩት ምንድን ነው የተለየ እነርሱ ሰማይ ላይ ይሮጣሉ ማለት አይደለም እንደኛ ሰው ናቸው፣ የተለየ ነገር የላቸውም፣ እና እዚህ ያለውም ተጫዋች መጫወት እንደሚችል ነው የተረዳሁት። እና ምንም የተለየ ነገር የለም። ማንም ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ሄዶ መጫወት ይችላል። እንዳልኩህ ልቦናህ ቅን ከሆነ አእምሮህን በጣም ትንሽ ማሳመን ነው። አሁን በብሔራዊ ቡድን ውጤትም ክለብም ወደ ውጪ ስንሄድ ትንሽ የምንቸገረው ጭንቅላታችንን አለማሳመናችን ነው። ያ እንዲሆን የሚያደርገው በአካል ደሂህ ብታይ ደግሞ ለውጥ ይኖራል ብዬ ነው የማስበው። ኢንተርናሽናል ቲም ስጫወት ውስጤ ምንም የለም። በክለብም ከውጪ ቡድን ጋር ስጫወት ውስጤ ምንም የሚፈጠር ነገር የለም። ስላየሁት ማለት ነው። አብረውኝ የሚጫወቱ ልጆች ያ ስሜት ውስጣቸው ቢኖር ብዬ ነው የምመኘው። ትልቁ የተማርኩት የተለየ ነገር የለም። እዚህ ያየሁት እዚያ አለ። እዚያ ያየሁት እዚህም አለ። ይህንን ነው ትልቁ ከውጪ የተማርኩት።

እግር ኳስ ውስጥ በቆየህበት 20 ዓመት ያህል አሳክቸዋለሁ የምትለው ነገር ምንድን ነው?

ሳላሃዲን ሠዒድ- በእግር ኳስ ብዙ ነገር አግኝቻለሁ። . . . ከምንም ነገር በፊት እግር ኳስን በጣም ነበር የምወደው። አጥንቴ ውስጥ ዘልቆ የገባ በለው። ከልጅነቴ ጀምሮ ማለት ነው። በእግር ኳስ ቤተሰቦቼን አፍርቻለሁ። አጠቃላይ ሕይወቴ እግር ኳስ ዙሪያ ነው። ቢዝነስም ውስጥ የገባሁት በእርሱ ምክንያት ነው። ለእኔ በሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ብዙ ነገር አሳክቻለሁ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ቢያልፍም ተመልሶ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መግባት አልቻለም። እንደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ትላልቅ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ መታየት አልቻለም። አህጉራዊ ውድድር ላይም እንኳ መቅረብ አልቻለም። ረዥም ዓመት በእግር ኳስ ውስጥ በተጫዋችነት ስላሳለፍክ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቁ ችግር በአንተ እይታ ምንድን ነው?

ሳላሃዲን ሠዒድ-ቅድም የተጫዋቾቻችን ልምድ ማጣትን እንደ አንድ ምክንያት አንስቼልሃለሁ። ከምንም በላይ እኔ ብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ በነበርኩበት ሰዓት ሁሌ የምለው ነገር አለ። እርሱም ምንድን ነው ዩኒቨርሳል መሆን። በአጠቃላይ ምንድን ነው እግር ኳስ ትእግስት ይፈልጋል። እና አንድ አሰልጣኝ ይመጣ እና ያለውን አፍርሶ የራሱን ቡድን ይገነባል። ቡድን ደግሞ ሲሰራ ሦስት አራት ዓመት ይፈልጋል። ሦስት ዓመት ፈጅቶ የገነባሀውን ቡድን ሌላ ሰው መጥቶ ሲያፈርስ ከዜሮ እንደመጀመር ነው። ብዙ ጊዜ በእኛ እግር ኳስ ውስጥ የማይሻሻለው እና ሰሚ ያጣው ይህ ነገር ነው። እግር ኳስ እውቀትን ይጠይቃል። ቡድን ስትገነባ ደግሞ ጊዜ ይጠይቃል። ዘንድሮ ምርጥ 15 ተጫዋች ብታመጣ ውጤታማ ላትሆን ትችላለህ። እየተዋሀድክ ስትሄድ ግን ቡድን ትሰራለህ። እኛ አገር ተጫዋች በተፈጥሮው ትንሽ የመደንገጥ ችግር አለበት። የሆነ ነገር ሲፈጠር የመደንገጥ ነገር አለ። እርሱም ተጨማምሮ ዋጋ አስከፍሎናል። እኔ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ በስንት አሰልጣኝ ውስጥ አልፌያለሁ። ጋሽ ሰውነት የገነባውን ቲም፣ የውጪ አሰልጣኝ ሲመጣ የራሱን ይገነባል። እርሱ ሲሄድ ደግሞ የአገር ውስጥ አሰልጣኝ ይመጣል። እርሱ የራሱን ይገነባል። እንዲህ እየተደረገ ነው እግር ኳሳችን ውጤት ያጣው። እንጂ የተጫዋች አቅም ጠፍቶ አይደለም። ይህ ቢስተካከል በሁለት ሶስት አራት ዓመት ጠንካራ ቲም መስራት ይቻላል። አቅም ያለው ተጫዋች አለ።

ተጫዋቾች ከተጫዋችነት ከራቁ በኋላ ችር ላይ ወድቀው ይታያሉ። አንተ አስተማማኝ ገቢ ኖሮህ ነው ስራ የለቀቅከው?

ሳላሃዲን ሠዒድ- እሰራለሁ፤ ትንሽ ኮንስትራክሽን ላይ እንቀሳቀሳለሁ። አንድ ትንሽ ሕንጻም አለኝ። በግሌም እንቀሳቀሳለሁ። አልሃምዱሊላሂ ለእኔም ለቤተሰቤም በቂ ነው (ሳቅ). . . ጥሩ ላይ ነው ያለሁት።

ከዚህ በኋላ ከእግር ኳስ ጋር በተያያዘ የምታስበው ነገር ምንድን ነው?

ሳላሃዲን ሠዒድ- በእግር ኳስ ውስጥ ረዥም ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። እና የአእምሮም የአካልም ድካም አለብኝ። . . . እና አሁን ላይ ረዥም እረፍት ነው የሚያስፈልገኝ ብዬ አስባለሁ። ከዚያ በኋላ የሚሆነውን አእምሮዬም አካሌም በቂ እረፍት አድርጎ ጠንካራ ሆኜ ስመለስ ከላይ የተቀመጠልኝ ነገር ካለ አይቀርም። እኛ ምክንያት መሆን ብቻ ነው። አሁን ግን መቶ በመቶ የማስበው እረፍት ብቻ ነው።

አሰልጣኝ ስለመሆን አስበህ አታውቅም?

ሳላሃዲን ሠዒድ- በፍፁም የለኝም፤ በጣም ፍቅሩ የነበረኝ ለመጫወት ነው። አሁን ልጆች አሉኝ። ልጆቼም እግር ኳስ ተጫዋች ቢሆኑ ደስ ይለኛል።

ከአገር ውስጥ ሆነ ከባህር ማዶ የምትደግፋቸው ክለቦች የትኞቹ ናቸው?

ሳላሃዲን ሠዒድ- ከአገር ውስጥ ጊዮርጊስ፣ ከውጪ ደግሞ አርሰናል እና የሪያል ማድሪድ ደጋፊ ነኝ።

ከተጫዋቾችስ?

ሳላሃዲን ሠዒድ- ከአገር ውስጥ ብዙ ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾች አሉ። ብጠቅስ ብዙ ይሆናል። ቅድም እንዳልኩህ አእምሮ ላይ ከተሰራ ሁሉም አቅም አለው ብዬ ነው የማስበው። ከውጪ የቴሪ ኦነሪ አድናቂ ነኝ። አሁን ካሉት የሮናልዶ አድናቂ ነኝ። ሮናልዶን ከሜዳ ውጪ ያለው ሕይወት የበለጠ እንዳደንቀው አድርጎኛል።