“ሊዲያ የሚለው ስም ራሱ ይዳኛል”፡ ‘ፊሽካ የሰቀለችው’ ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ

ኢትዮጵያ አሉኝ ከምትላቸው የእግር ኳስ ዳኞች እንዷ የሆነችው ሊዲያ ታፈሰ ‘ፊሽካ ሰቅላለች።’

እሑድ ሰኔ 18/2015 በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲፋለሙ ለመታደም ሺህዎች ተገኝተው ነበር።

ነገር ግን ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት አንድ ዜና ለታዳሚዎች ተነገረ።

ሊዲያ በባሕል ልብስ ደምቃ፤ በሁለቱ ቡድን ተጫዋቾች እንዲሁም በደጋፊው ጭብጨባ እና የአድናቆት ጩኸት ታጅባ ወደሜዳ ዘለቀች።

የሙያ አጋሮቿ ‘ሊዱ እናመሰግናለን’ የሚል ጽሑፍ ያለበት ካናቴራ ለብሰው ተገኝተዋል።

ነገር ግን ሊዲያ እንባዋን መቆጣጠር አልቻለችም።

አጠገቧ ከቆሙት ዳኞች መካከል አልቢትር ባምላክ ተሰማ ጉንጯን ስሞ ሊያጽናናት ይሞክራል።

የፕሪሚዬር ሊግ አስተዳዳሪ የሆነው አክሲዮን ማኅበርን ጨምሮ ሌሎችም ስጦታ ሲያበረክቱላት በእንባ ታጅባ ተቀብላለች።

‘የሸገር ደርቢ’ የተሰኘው የዳቦ ስም ያለው ጨዋታ በቴሌቪዥን መስኮት ሲተላለፍ ካሜራው በተደጋጋሚ ሊዲያን ያሳይ ነበር።

የምትወደውን ፊሽካ ስትሰቅል በሐዘን ተውጣ እንደሆነ ፊቷ ያሳብቃል።

ለመሆኑ ሊዲያ ፊሽካ ልትሰቅል የወሰነችው ለምን ይሆን?

የ20 ዓመታት ጉዞ

ሊዲያ በልጅነቷ እግር ኳስ ታዘወትር የነበረ ቢሆንም፣ ቀልቧ ግን ከቅርጫት ኳስ ላይ ነበር።

በአንድ ወቅት ስለእግር ኳስ ዳኝነት ሥልጠና ሲሰጣ ራሷን አዳራሹ ውስጥ ታገኘዋለች። ሥልጠናውን እና ሙያውንም ትወደው ጀመር።

ነገር ግን መጀመሪያ ሰሞን ሁሉም አልጋ በአልጋ እንዳልሆነላት የአፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር (ካፍ) ገጽ ላይ የሰፈረው ታሪኳ ያስነብባል።

እነሆ ሊዲያ አሁን ኢትዮጵያ እና አፍሪካ አሉኝ ከሚሏቸው እንስት ዳኞች መካከል አንዷ ናት።

ሁለት ጊዜ የሴቶች የዓለም ዋንጫን ዳኝታለች። በቻን አፍሪካ የወንዶች ውድድርም ላይ ተሳትፋለች። ባለፈው ዓመት የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ሲሰናዳ የፍፃሜው ጨዋታ የዳኘችው. . . ሊዲያ ናት።

የአፍሪካ የሴቶች ዋንጫ፣ ከ17 ዓመት በታች እና ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ. . . ብቻ ሊዲያ ከዳኘችው ያልዳኘችውን መጥራቱ ሳይቀል አይቀርም።

ነገር ግን ሰኔ 18/2015 ዓ.ም. ሊዲያ ታፈሰ እግር ኳስ ዳኝነት ይብቃኝ ብላ ‘ፊሽካ መስቀሏ’ ይፋ ሆነ። ለምን?

“ወደ ኢንስትራክተር ሙያው እንደምመጣ ስለማውቅ፤ ከ2023 (እአአ) በኋላ መቀጠል እንደማልፈልግ አሳውቄ ራሴን እያዘጋጀሁ ነበር” ስትል ሊዲያ ለቢቢሲ ትናገራለች።

ካፍ፤ ለዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ (ፊፋ) ጥያቄ አቅርቦ ሊዲያ የኢንስትራክተርነት ከፍተኛ ሥልጣና (አድቫንስድ ኮርስ) እንድትወስድ ሆኗል።

“የአካል ብቃቴ (ፊትነስ) እንደቀድሞው አይደለም” የምትለው ሊዲያ ዳኝነት እና ኢንስትራክተርነት በአንድ ጊዜ ማስኬድ ከባድ መሆኑን ታስረዳለች።

ይሄኔ ነው ከምትወደው የዳኝነት ሙያ መለያየት እንዳለባት የወሰነችው።

“እርግጥ ነው አስቤ የነበረው በዓመቱ መጨረሻ ላይ ነበር። ነገር ግን የሴካፋ ውድድር ሲራዘም ደጋፊ በተገኘበት [በሸገር ደርቢ] እንዲሆን ተደረገ። ለዚያ ነው እሑድ የሆነው።”

የዳኝነት ሕይወት

ሊዲያ ስለዳኝነት አውርታ ባትጠግብም በተመሳሳይ ቃላት ያጥራታል።

“ዳኝነት ለእኔ ሕይወቴ ነው። ብዙ ነገር ያየሁበት ነው። ደስታም ሐዘንም አይቼበታለሁ። ዳኝነት እንዲህ ነው ብዬ መግለጽ ይከብደኛል” ትላለች።

“እውን ከዚህ በኋላ አልሮጥም? ፊሽካ እና ካርድ ይዤ ወደሜዳ አልገባም?” የሚለው ሐሳብ ለቀናት እንዳስጨነቃት አትደብቅም።

የሚያውቋት ሰዎችም አስተያየትም “እንደው ትክክል አላደረግሽም” የሚል እንደሆነ ትገልጻለች።

“ከደጋፊም ከሌላውም ‘ውሳኔሽ ትክክል አይደለም’ የሚል ተቃውሞ ነው የደረሰኝ። ያው በግዴታ ነው ያጨበጨብ እና ይጮኽ የነበረው ደጋፊው እንጂ ስሜቱ ደስተኛ አልነበረም።”

የሊዲያ ፊሽካ መስቀል ለብዙዎች ያልተጠበቀ ውሳኔ ነው። እሷም ጉዳዩን ለቅርብ ወዳጆቿ እና ለሙያ አጋሮቿ እንጂ ለሌላው አላካፈለችም።

“[ደጋፊዎች] ሊዲያ ታቆማለች የሚል ግምት አልነበራቸውም። እሱም ይመስለኛል ተቃውሞውን ያስነሳው ግን እንግዲህ...ይበቃል። እግዚአብሔር ይመስገን። እግዚአብሔር በፈቀደው መልኩ ደግሞ ሌላውን ነገር ማስኬድ ነው የሚሻለው።

“ለሰው ማሳወቅ ነበረብኝ? በዚህ ሰዓት ላቆም ነው ማለት ነበረብኝ? ብቻ ብዙ ነገር ነበር በሐሳቤ ሲመላለስ የነበረው።”

ሊዲያ በዳኝነት ሕይወት ያልወጣችው ዳገት የለም። በሞቃታማዋ ካሜሩን ከተካሄደው የወንዶች ቻን ጀምሮ በውጥረት ተሞልቶ እስከተካሄደው የባሕር ዳር እና የመቀለ ጨዋታ. . . ሊዲያን ቢፈትኗትም፤ አልበገሯትም።

ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በግብፅ መዲና ካይሮ በተሰናዳው የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ ዳኝታለች።

ያንን ውድድር የፍፃሜ ጨዋታ በመዳኘቷ “እጅግ ደስተኛ” መሆኗን ትገልጣለች።

“ማንም ዳኛ ሲጀምር አገር ቤት ፕሪሚዬር ሊግ አጫውቼ፣ ከዚያም የአፍሪካ ዋንጫ፣ ቀጥሎም የዓለም ዋንጫ ብሎ ይመኛል። እኔ ይህን ሕልም ሳላሳከ ቀርቻለሁ አልልም። እግዚአብሔር ይመስገን ሁሉን አሳክቻለሁ።”

ሊዲያ “ሴትነት እና ዳኝነት ልዩ ግንኙነት አላቸው” ትላለች። ዳኝነት የተለየ ዕይታን እንደሚጠይቅ ታስረዳለች። ምክንያታዊ ሴት መሆኗንም ታክላለች።

“ሙያው ሴቶችን የሚያስከብር፤ አቅም እንዳለን የሚያሳይ፤ የተለየ ዕይታ እንዳለን የሚያሳይ ነው። እንግዲህ ወንዶችን በዕይታ እንበልጣቸዋለን። ይሄን ተግባራዊ አድርጊያለሁ ብዬ አስባለሁ።”

ሴት በመሆኗ ብቻ ከተጫዋችም ሆነ ከደጋፊ ብዙ ለየት ያለ ጉዳይ ገጥሟት እንደማያውቅ ሊዲያ ትናገራለች። “[ደጋፊዎች] እንዲያውም ሊዲያ የሚለው ስም ራሱ ይዳኛል ይላሉ” ትላለች።