ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፓኪስታን ትልቁ ሐይቋ እንዳያጥለቀልቃት ስጋት ላይ ናት
በፓኪስታን የሚገኘውን ትልቁን ሐይቅ ለማስተንፈስ የተደረገው የመጨረሻ ሙከራ መክሸፉን ተከትሎ ውሃው ሞልቶ እንዳይፈስ ለማድረግ ባለስልጣናት እየታገሉ ናቸው።
የማንቻር ሐይቅ በደቡብ ምስራቅ ሲንድ ግዛት ይገኛል።
ለቀናት በአካባቢው በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የሐይቁ የውሃ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
ሐይቁን ለማስተንፈስ በተደረገው ሙከራ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።
ከዚህ ሁሉ ጥረት በኋላ ሰኞ ዕለት የግዛቲቱ የመስኖ ሚኒስትር የሐይቁ የውሃወ መጠን "አልቀነሰም" ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ውየሲንድ ግዛት የሀገሪቱን የምግብ አቅርቦት ግማሹን ያመርታል። በርካቶች ከኢኮኖሚያዊ ቀውስ ጋር በሚታገሉባት ፓኪስታን ጎርፉ ብዙዎች ለከፋ የምግብ እጥረት ይጋለጣሉ የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
በፓኪስታን የደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ 33 ሚሊዮን ሰዎችን ለጉዳት ዳርጓል።
እንደ ፓኪስታን ብሔራዊ የአደጋ መከላከል ኤጀንሲ ከሆነ ቢያንስ 1,314 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ 458ቱ ህጻናትን መሆናቸውን አስታውቋል።
ጎርፉ ቢያንስ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ጉዳት ማድረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ሐይቁ ሁለት የገጠር መንደሮችን ማጥለቅለቁን ተከትሎ የበለጠ ፈንድቶ ህዝብ የሚኖርባቸውን አካባቢዎች እንዳይጎዳ በማሰብ እሑድ ዕለት ባለስልጣናት ለማስተንፈስ ሞክረዋል።
እርምጃው ግን በ400 መንደሮች የሚኖሩ 135 ሺህ ሰዎችን ቤት አልባ ሊያደርጋቸው ይችላል።
በሳምንቱ መጨረሻ ነዋሪዎችን ቀዬአቸውን ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።
ባለስልጣናቱ ሰኞ ዕለት በሐይቁ ላይ ያለው የውሃ መጠን በአደገኛ ሁኔታ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል ።
የአውራጃው የመስኖ ሚኒስትር ጃም ካን ሾሮ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የውሃው መጠን አልቀነሰም። ተጨማሪ የማስተንፈስ ሙከራዎች ይደረጉ እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥበዋል ።
ፓኪስታን በአየር ንብረት ምክንያት የተከሰቱ እጅግ አደገኛ የተፈጥሮ አደጋዎች እያጋጠሟት ነው።
እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በሃገሪቱ ሰሜናዊ ተራራማ አካባቢዎች ከሚገኘው የበረዶ ግግር መቅለጥ ጋር ተደማምሮ የጎርፍ መጥለቅለቅን አስከትሏል።
አንድ ሶስተኛ የሚሆነው የሃገሪቱ ክፍል በውሃ ተሸፍኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ እንዳስታቀው በፓኪስታን በንፁህ ውሃ እጥረት ምክንያት በርካታ ህጻናት በበሽታ የመሞት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
አደጋው ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ባላቸው ሃገራት እና የችግሩን ጫና በሚሸከሙ ሃገራት መካከል ያለውን ልዩነት አጉልቶ አሳይቷል ተብሏል።
ፓኪስታን ከአንድ በመቶ ያነሰ የዓለም ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን ታመርታለች። ያለችበት አቀማመጥ ግን ለአየር ንብረት ለውጥ በጣም የተጋለጠች አድርጓታል።