የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዊሊያም ሩቶን አሸናፊነት አጸና

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ነሐሴ 09/2014 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ላይ የቀረበውን ክስ ውድቅ በማድረግ የዊሊያም ሩቶን በፕሬዝዳንትነት መመረጥ አጸደቀ።

ምርጫውን ተከትሎ ተፎካካሪ ዕጩ የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ በምርጫው ሂደት ላይ ማጭበርበር መከሰቱን በመግለጽ ያቀረቡትን ክስ ተከትሎ ነው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው።

ሰባት አባላት ያሉት የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበለትን ክስ ሲመለከት ቆይቶ ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ አምስተኛው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡበት ሂደትን ተቀብሎታል።

ተቀናቃኙ ራይላ ኦዲንጋ እና አጋሮቻቸው በምርጫው ሂደት የውጤት መለወጥን ጨምሮ ከፍተኛ የማጭበርበር ድረጊቶች ተፈጽመዋል በማለት ነው ለአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ ያቀረቡት።

ከፍተኛ ፉክክር በተካሄደበት ምርጫ 50.5 በመቶ የመራጮችን ድምጽ አግኝተው በጠባብ የድምጽ ብልጫ ነበር ዊሊያም ሩቶ ማሸነፋቸው የታወጀው።

በአወዛጋቢው ምርጫ አሸናፊነታቸው በድጋሚ በፍርድ ቤት የጸናላቸው ዊሊያም ሩቶ የኬንያ አምስተኛው ፕሬዝዳንት በመሆን በሚቀጥለው ሳምንት ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ነሐሴ መጀመሪያ ላይ የተካሄደውን የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ በቀረበለት ቅሬታ ዙሪያ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚሰጠውን ውሳኔ በርካታ ኬንያውያን በጉጉት ሲጠበቅ ነበር።

በምርጫው ሂደት ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ የማጭበርበር ድርጊቶችን በተመለከተ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰብሳቢ ማርታ ኮምቤ የቀረቡት ማስረጃዎች “ሐሰተኛ እና በስሜት ላይ የተመሰረቱ ናቸው” በማለት የሰባቱን ዳኞች ውሳኔ ይፋ አድርገው ውጤቱን አጽንተዋል።

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ውሳኔ ተከትሎ በምርጫው የተሸነፉት ራይላ ኦዲንጋ እና ምክትላቸው ማርታ ካሩዋ በተሰጠው ብይን ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።

ኦዲናጋ ባወጡት መግለጫ ካሩዋ ደግሞ ትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ሁለቱም በተመሳሳይ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚያከብሩ ነገር ግን “ፈጽሞ እንደማይስማሙበት” ገልጸዋል።

ይህ ውሳኔ በምርጫው ውዝግብ ላይ የመጨረሻው ብይን በመሆኑ የዊሊያም ሩቶ ፕሬዝዳንትነት እውን ሆኗል።

የአገሪቱ የምርጫ እና ድንበር ኮሚሽን የወቅቱ ምክትል ፕሬዝዳን ዊሊያም ሩቶን አብላጫ ድምጽ አግኝተዋል በማለት ተመራጭ ፕሬዝዳንት ሲል ማወጁ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ የሩቶ ተቀናቃኝ ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ውጤቱን በመቃወም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውታል።

የራይላ ኦዲንጋ ጠበቆች በምርጫው ሂደት ተአማኒነት የጎደላቸው አሠራሮች በማጋጠማቸው ፍርድ ቤቱ የምርጫ ውጤቱን ውድቅ እንዲያደርገው ጠይቀው ነበር።

ለቀናት የሁለቱንም ወገን መከራከሪያ ሲያዳምጥ የነበረው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ በሰጠው ውሳኔ የቀደመውን ውጤት አጽድቆታል።

የዊሊያም ሩቶ እና የምርጫ ኮሚሽኑ ጠበቆች በበኩላቸው ምርጫው ስለመጭበርበሩ ምንም ማስረጃ አልቀረበም በሚል ውጤቱ እንዲጸና ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ እስካለፍነው አርብ ነሐሴ 27/2014 ዓ.ም. ድረስ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ሲያዳምጥ ቆይቶ፤ ዳኞች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት የጋራ ውሳኔ ለማሳለፍ በአንድ ቦታ ተሰብስበው ሲሰሩ ቆይተዋል።

ውሳኔው ከመተላለፉ በፊት የፀጥታ ኃይሎች ዋና ከተማዋ ናይሮቢን ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ተሰማርተው እንደሚገኙ ታይቷል።

ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ በናይሮቢ ውስጥ በሚገኘው በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ህንጻ ዙሪያ ያሉ ዋና ዋና መንገዶች ለትራፊክ ዝግ ሆነዋል።

ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ ጋር በተያያዘ የአደባባይ ተቃውሞ ሊከሰትባቸው ይችላሉ ተብለው በተለዩ አካባቢዎችም የፀጥታ ጥበቃው ጥብቅ እንዲሆን መደረጉን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት በነበረው ምርጫ ተመሳሳይ ውዝግብ ተከስቶ የአሁኑ ከሳሽ ራይላ ኦዲንጋ ጉዳዩን ወደ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መውሰዳቸው ይታወሳል።

በወቅቱም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አሁን የሚሰናበቱት የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን የአሸናፊነት ውጤትን ውድቅ አድርጎ ምርጫው እንዲደገም ወስኖ ነበር።

በተደገመው ምርጫም ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በድጋሚ አሸናፊ ሆነው ለሁለተኛ ዙር አምስት ዓመታት አገሪቱን ሲመሩ ቆይተዋል።