ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጋምቤላ በአንድ ቀን ብቻ 'ከ100 በላይ በጦር መሣሪያ የቆሰሉ ሰዎች' ለሕክምና መምጣታቸውን የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አስታወቀ
በጋምቤላ ክልል በቀጠለው ግጭት ረቡዕ ዕለት ብቻ ከ100 በላይ በጦር መሣሪያ የቆሰሉ ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋማት መምጣታቸውን ዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አስታወቀ።
በጋምቤላ ከሁለት ሳምንት በላይ በዘለቀው ግጭት በርካቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ዓለማቀፉ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) አስታውቋል።
ቡድኑ ታሕሳስ 15/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ረቡዕ ዕለት ብቻ ከ100 በላይ በጦር መሣሪያ የቆሰሉ ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋሙ መምጣታቸውን እና በሚቀጥሉት ቀናት ግጭቱ ከቀጠለ በርካቶች ይመጣሉ ብሎ እንደሚጠብቅ አስታውቋል።
ኤምኤስኤፍ እአአ ከ2014 ጀምሮ በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ለሚገኙ ስደተኞች የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ ለሳምንታት የዘለቀውን አለመረጋጋት ተከትሎ ከትናንት ታሕሳስ 15/2018 ዓ.ም ጀምሮ የፀጥታ ችግር በሚታይባቸው አካባቢዎች ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ የሚቆይ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሏል።
የክልሉ መንግሥት የሰዓት እላፊ ገደቡን ይፋ ባደረገበት መግለጫው ላይ በክልሉ አሁን ስላለው የፀጥታ ሁኔታ ተጨማሪ ያለው ነገር የለም።
በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስ ለመቆጣጠር በሚል ከኅዳር 30/2018 ዓ.ም. አንስቶ ከፀጥታ አካላት ውጪ ማንኛውም ተሽከርካሪ እና ሰው ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ የሚከልክል የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሎ ነበር።
የክልሉ መንግሥት በተጨማሪም ከተፈቀደላቸው የፀጥታ አካላት ውጪ የትኛውም ቦታ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም አስታውቋል።
ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በግጭቱ ለቆሠሉ ታካሚዎች ኩሌ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሕክምና እርዳታ መስጠት በጀመረ በ48 ሰዓት ውስጥ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሠባቸውን 19 ሰዎች ጨምሮ 50 ቁስለኞችን ማከሙን ገልጿል።
አክሎም ባለፉት ሰባት ቀናት ከ150 በላይ ቁስለኞችን ተቀብሎ ማከሙን አስታውቋል።
ኩሌ የስደተኞች መጠለያ ወደ 55,000 የሚጠጉ ደቡብ ሱዳናዊ ስደተኞችን የያዘ ሲሆን በኤምኤስኤፍ በመጠለያ ጣቢያው የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ የጤና አገልግሎቶችን ይሰጣል።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በቁስለኞች ብዛት ሳቢያ የጋምቤላ ከተማ ሆስፒታል ሳምንቱን ሙሉ የተመላላሽ ሕክምና አገልግሎት ማቆሙንና ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችም መስተጓጎላቸውን ጠቅሷል።
ግጭቱ ከጀመረ ወዲህ የበርካቶች ሕይወት መጥፋቱን፣ የአካል ጉዳት መድረሱንና ግጭቱ በዚሁ ከቀጠለ ወደ ሕክምና ጣቢያው የሚገቡ ቁስለኛ ታካሚዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ቡድኑ በመግለጫው ላይ ገልጿል።
በጋምቤላ ስላለው ግጭት እስካሁን የምናውቀው
የጋምቤላ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ሮን ጎይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በክልሉ ታሕሳስ 15/2018 ዓ.ም. የመንግሥት መኪና እና አምቡላንስ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ጉዳት ከደረሰ ወዲህ 19 ሰዎች በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
መኪናው ላይ በተፈጸመ ጥቃት አምስት ሰዎች ሲገደሉ፣ በከተማው ውስጥ በነበረ የጸጥታ መደፍረስ ተጨማሪ አምስት ሰዎች ሞተው ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውን ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።
ታሕሳስ 15 የመንግሥት መኪና እና አምቡላንስ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ከተጎዱት መካከል አራቱ ሴቶች መሆናቸውን የጠቀሱት ኃላፊው ከተማው ውስጥ በተፈጠረው ግጭት ግን የተጎዱት በሙሉ ወንዶች ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ የመኪና እንቅስቃሴ ስለቆመ ከየትኛውም አካባቢ ወደ ሆስፒታላቸው ቁስለኛ እየመጣ አለመሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ከኢታንግ ወረዳ ብቻ ሦስት ሰዎች በጥይት ቆስለው መምጣታቸውን እና ይህም በሆስፒታላቸው በግጭት ተጎድተው የመጡትን ሰዎች ቁጥር 22 እንደሚያደርሰው ተናግረዋል።
የክልሉ ዋና ከተማን ከተለያዩ አካባቢዎች ጋር የሚያገናኙ መንገዶች በፀጥታ ስጋት ምክንያት ዝግ መሆናቸውን ኃላፊው ጨምረው ግለፈዋል።
የክልሉን ፀጥታ የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት ተረክበው እየተቆጠጠሩ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች ተናግረዋል።
በክልሉ ከኅዳር 28/2018 ዓ.ም. ጀምሮ በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ በጋምቤላ ወረዳ ፣ በጋምቤላ ከተማ እና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡመድ ኡጁሉ ጨምሮ በርካቶች ተገድለዋል።
በክልሉ ዋና ከተማ እና በአካባቢው ባሉት ወረዳዎችና ቀበሌዎች በተፈጠረው ግጭት የሰዎች ሕይወት ሲጠፋ የአካል ጉዳት እና የንብረት መውደም ደርሷል።
ይህንንም ተከትሎ ባንኮችንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ማቋረጣቸው የተዘገበው ባለፈው ሳምንት ነበር።
ሰኞ ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የመከላከያ እና የፌደራል የፀጥታ አካላት መሰማራታቸውን ተከትሎ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ መጀመራቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
በጋምቤላ ክልል በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እርዳታ የሚያቀርበው የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ኮሚሽን ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአካባቢው በተፈጠረው ውጥረት ሳቢያ በክልሉ ለሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የምግብ ሥርጭት እና የውሃ አቅርቦት ለጊዜው ተቋርጧል ብሏል።
በጋምቤላ በሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች ዙሪያ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሚነዛው "ሐሰተኛ መረጃ" በአስቸኳይ መፍትሄ ካልተሠጠው ይበልጥ ውጥረት ሊያስከትል እንደሚችል ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ላይ አስጠንቅቆ ነበር።
በክልሉ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል ያሏቸውን አካላት በቁጥጥር ሥር እያዋሉ መሆኑን የገለፀው የክልሉ መንግሥት እስካሁን ድረስ ምን ያህል ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር አንደሚገኙ ያለው ነገር የለም።
ኢሰመኮ ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ወደፊት ተመሳሳይ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የፌዴራሉ እና የክልሉ መንግሥታት ተገቢ እርምጃዎችን ሊወስዱ ይገባል ብሏል።
ድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን ታሕሳስ 15 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የሰላማዊ ዜጎች ደኅንነት "በጥልቅ" እንዳሳሰበው አስታውቆ፣ የታካሚዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና የሕክምና ተቋማት ከጥቃት እንዲጠበቁም ጥሪ አቅርቧል።