የጋምቤላ ከተማ የፖሊስ አዛዥ መገደል እና እየተባባሰ ያለው የክልሉ አለመረጋጋት

ባለፉት ተከታታይ ቀናት በጋምቤላ ክልል በተፈጸሙ ጥቃቶች የጋምቤላ ከተማ የፖሊስ አዛዥን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች መገደላቸው የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።

ካለፉት ሳምንታት ወዲህ በዋና ከተማዋ ጋምቤላ እና በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ በሚፈጸሙ ጥተቶች የተነሳ አለመረጋጋት መፈጠሩን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የክልሉ ባለሥልጣናትም ሆኑ ነዋሪዎች ማንነታቸውን በውል ያልገለጿቸው ታጣቂዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች የፀጥታ አባላት እና ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም የነዋሪዎች የዕለት ከዕለት መደበኛ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የክልሉ ዋና ከተማ የፖሊስ አዛዥ በተፈጸመባቸው ጥቃት ሕይወታቸው ማለፉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ እና ምክትላቸው ዶ/ር ጋትሉዋክ ሮን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ይህንንም ተከትሎ በጋምቤላ ክልል፣ ጋምቤላ ከተማ ረቡዕ ታኅሣሥ 8/ 2018 ዓ. ም. ከረፋድ ጀምሮ ተኩስ ይሰማ እንደነበር ነዋሪዎች ምስክርነታቸውን ለቢቢሲ የሰጡ ሲሆን፣ በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን መስማታቸውን ገልጸዋል።

የጋምቤላ ክልል አስተዳደር ረቡዕ ምሽት ባወጣው መግለጫ "የክልሉ ሕዝብ ሰላም እንቅልፍ የሚነሳቸው እና ግጭት እና የሰው ሞት የሚያስደስታቸው" ያላቸው በስም ያልጠቀሳቸው ኃይሎች ከሰሞኑ የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ወረዳዎች ትርምስ ፈጥረዋል በማለት የተከሰተውን ሁኔታ ገልጾታል።

ጨምሮም እነዚህ ኃይሎች "ሰዎችን በመግደል፣ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ እና ሕይወት እንዲጠፋ በማድረግ፣ የፀጥታ አካላትን እና አመራርን ዒላማ በማድረግ" የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረጋቸውን ገልጿል።

መግለጫው የከተማዋ ፖሊስ አዛዥን ግድያ ባይጠቅስም የፀጥታ አካላት እና አመራር በማለት በፖሊሶች እና በአዛዡ ላይ የተፈጸመው ግድያ አመልክቷል።

ቢቢሲ ረቡዕ ዕኩለ ቀን ላይ ያናገራቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ወ/ሮ ዓለሚቱ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም ግድያውን አረጋግጠዋል።

እንዲሁም አመሻሽ ላይ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ምክትላቸው ዶ/ር ጋትሉዋክ፤ በፖሊስ ኣዛዡ ላይ ግድያ መፈጸሙን እና ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመያዝ የፀጥታ ኃይሉ ክትትል እደያረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚሁ የከተማዋ የፖሊስ አዛዥ ግድያ ጋር በተያያዘ ድርጊቱን ፈጽሟል በሚል የተጠረጠው አንድ የፖሊስ ባልደረባ እንደሆነ ተነግሯል።

በተፈጸመው ጥቃት ተጠርጥረው "በጥቆማ የመጡት ፖሊሶች ናቸው" ያሉት ጋትሉዋክ፤ እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ሥር የዋለ አለመኖሩን ተናግረዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥቃት ፈጻሚዎቹ "በቡድን መጥተው ነው ጥቃት ያደረሱት" በማለት ከግጭቱ እና ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ የሚጠረጠሩ የክልሉ የፀጥታ ኃይል አባላት የታጠቁትን የጦር መሣሪያ እንዲያስረክቡ መደረጉንም አመልክተዋል።

በጋምቤላ ክልል የተከሰተው አለመረጋጋት ቀናትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በሌላ ጥቃት አንድ የባንክ ሥራ አስኪያጅ እንደተገደሉ እና በግድያው ተጠርጥሮ የተያዘው የፖሊስ ባልደረባ እንደሆነ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የባንክ ሥራ አስኪያጁ በተገደሉበት ዕለት ከአቦል ከተማ ወደ ጋምቤላ ከተማ ሲጓዝ በነበረ አንድ የወረዳው ፒክአፕ መኪና እና አምቡላንስ ላይም ጥቃት መፈጸሙን ገልጸዋል።

"በጥቃቱ ወደ አራት ሰዎች ተገድለዋል። የቆሰሉም አሉ። ከዚያ በፊትም መኪና ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። መንገድ ላይ ወደ ሦስት መኪና ላይ ጥቃት ደርሷል" ብለዋል።

በሁለቱ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠሩ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል።

የጋምቤላ ከተማ የፖሊስ አዛዥ ግድያ የተፈጸመው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለቀናት የዘለቁ ጥቃቶች ከተፈጸሙ እና የባንክ ሥራ አስኪያጅ ከተገደሉ ከቀናት በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።

እነዚህ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ተከትሎ ረቡዕ "ወጣቶች ተነስተው" እንደነበር በመጥቀስ "ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት" እንደፈጸሙም አብራርተዋል።

"ግጭቱ ተነስቶ ወደ ብዙ አካባቢዎች ተስፈፍቷል" ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ጉዳት ደርሷል ብለዋል። ነገር ግን በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ባለመጣራቱ መረጃው እንደሌላቸው ገልጸዋል።

ይህ የክልሉን ሰላም እየፈተነ ያለው ጥቃት የተፈጸመው በማን እንደሆነ የተጠየቁት ጋትሉዋክ፤ ጥቃት አድራሾቹ "በተደራጀ ሁኔታ" የሚንቀሳቀሱ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም ግን "በመጣው ለውጥ ደስ ያላላቸው" ሲሉ ገልጸዋቸዋል። "አንዳንዶቹም ከአሜሪካ ገንዘብ የሚላክላቸው ተራ ሰዎች ናቸው" ብለዋል።

ለጥቃቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ከታጣቂዎች ጋር "በውስጥ በተቀናጀ መንገድ የሚገናኙ ከሆነ አናውቅም" ሲሉም አክለዋል።

በያዝነው ዓመት በሙሉ "በትንሹ ችግር ነበር" ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የዚህ ሳምንት በአጠቃላይ እና በተለይም ረቡዕ ዕለት ያጋጠመው "በጣም የከፋ ሆኗል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ይህንን በተከታታይ የሚፈጸም ጥቃት ማስቆም ያልተቻለው ጥቃት አድራሾቹ "የተደራጁ እና በአንድ የተወሰነ አካባቢ" ላይ ያሉ አለመሆናቸውን እና" በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው" መሆኑን እንደምክንያት ጠቅሰዋል።

የጋምቤላ ክልል ረቡዕ ምሽት ባወጣው መግለጫ "ተጠርጣሪዎችን አድኖ በመያዝ" ላይ እንደሆነ እና "በርካቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው" ተመልክቷል።

በተጨማሪም ከፀጥታ ኃይል አባላት ውጪ የትኛውንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ይዞ በሚገኝ እና በሚንቀሳቀስ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ የፀጥታ አካላት "አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስዱ" አስጠንቅቋል።

ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰነው የጋምቤላ ክልል በተለያዩ ጊዜያት ጋብ እያለ የሚያገረሽ ግጭት እና ጥቃት ሲከሰትበት የቆየ መሆኑ ይታወቃል።

የአሁኑ አለመረጋጋት የጀመረው ከሳምንት በፊት አንስቶ ሲሆን ሰላማዊ ሰዎችን፣ የፖሊስ አባላትን እንዲሁም ተሽከርካሪዎችን ዒላማ ባደረጉ ጥቃቶች ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን እንዲሁም የአካል ጉዳት መድረሱን ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ይህንን የፀጥታ መደፍረስ ለመቆጣጠርም የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከኅዳር 30/2018 ዓ.ም. አንስቶ ከፀጥታ አካላት ውጪ ማንኛውም ተሽከርካሪ እና ሰው ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ የሚከልክል የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሏል።

እንዲሁም የክልሉ ፖሊስ ታኅሣሥ 5 እንዳስታወቀው በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ በጋምቤላ ከተማ፣ በጋምቤላ ወረዳና፣ በላሬ ወረዳ ውስጥ ከኅዳር አጋማሽ ወዲህ በተለያዩ ቀናት በተፈጸሙ ጥቃቶች የተጠረጠሩ 18 የሚደርሱ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልጾ ነበር።

ከክልሉ አስተዳደር እርምጃ በኋላም የዋና ከተማዋ የፖሊስ አዛዥ መገደላቸውን እና እሱንም ተከትሎ ረቡዕ ዕለት ግጭት መቀስቀሱን ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ይህ ግጭት ከዚህ ቀደም በክልሉ ውስጥ እንዳጋጠመው ብሔርን ወደለየ የከፋ ሁከት እንዳያመራ ስጋት ተፈጥሯል።

የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ ለመቆጣጠር አስቸኳይ ስብሰባ ማካሄዳቸውን ጉዳዩን ከሚያውቁ ሰዎች ለመረዳት ተችሏል።