ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የብሪታኒያ እና የጀርመን ወታደሮች በገና በዓል መዝሙሮች ምክንያት በድንገት ያደረጉት የተኩስ አቁም
የጨቀየ መሬት፣ ደም እና የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ትርምስ በሞላበት አስከፊው የአውሮፓውያኑ 1914 ክረምት ያልተጠበቀ ነገር ተፈጠረ።
በምዕራባዊው የጦርነት ግንባር ውጊያ ላይ የነበሩ ኃይሎች በድንገት እና በአስገራሚ ሁኔታ የተኩስ አቁም አደረጉ። ቢቢሲ፤ ያንን ልዩ የገና (ክሪስማስ) በዓል መሳሪያቸውን አስቀምጠው ለማሳለፍ ከወሰኑ ወታደሮች መካከል በ1960ዎቹ የተወሰኑትን አነጋግሮ ነበር።
የአምስተኛው ለንደን ራይፍል ብርጌድ አባል የሆነው ግርሃም ዊሊያምስ በ1914 የገና ዋዜማ ተረኛ ዘብ ነበር። በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ወዳለው "የማንም ያልሆነ መሬት" እና ወደ ጀርመኖች ምሽግ በጭንቀት እየተመለከተ ቆሞ ነበር።
የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት መለያ የሆኑትን ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች፣ እልቂት እና ውድመት ለወራት ችሎ አሳልፏል። በመሃል ግን አንድ አስገራሚ ነገር ተከሰተ።
"ድንገት በጀርመኖች ምሽግ በኩል መብራቶች ታዩ። የሚያስቅ ነገር ሆኖ ነበር የታየኝ። ከዚያም ጀርመኖቹ. . .መዘመር ጀመሩ። እኔም ነቃሁ፤ ሌሎች ጠባቂዎችም ይህንን አደረጉ። ሌሎቹም ወታደሮች ምን እየተፈጠረ እንደሆነ እንዲያዩ ቀሰቀስናቸው" ሲል 'ዊትነስ ሂስትሪ' ለተሰኘው የቢቢሲ ራዲዮ ፕሮግራም ተናግሯል።
ምድረ በዳ በሆነው "የማንም ያልሆነ መሬት" ያስተጋቡት ታዋቂ መዝሙሮች ቋንቋን ግንብ አፍርሰው፤ በሙዚቃ በኩል የተፋላሚዎቹ ወታደሮች የጋራ መገለጫ የሆነውን ሰብአዊነትን አሳዩ።
"መዝሙራቸውን ሲጨርሱ አጨበጨብንላቸው። እኛም በምላሹ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብን አሰብን። ከዚያ እኛም የራሳችንን መዝሙር ዘመርንላቸው" በማለት ያስታውሳል።
በ1914 የተደረገው የገና ተኩስ አቁም በትክክል ከየት እንደተነሳ መናገር አስቸጋሪ ነው። በምዕራባዊው ግንባር በሚገኙ በርካታ ቦታዎች በአንድ ጊዜ በድንገት የተነሳ ይመስላል። አንድ ወጥ የሆነው የገና ተኩስ አቁም አልነበረም፤ ይልቁንም በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ትናንሽ ክስተቶች ነበሩ።
በአንዳንድ ምሽጎች የነበሩ ወታደሮች የተኩስ አቁሙ የቆየላቸው ለሁለት ሰዓት ገደማ ነው። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ 'ቦክሲንግ ዴይ' ተብሎ እስከሚታወቀው የገና ማግስት ቀናት ድረስ ቆይቷል። እስከ አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት የቆየባቸው ጥቂት ቦታዎችም ነበሩ።
በሌሎች አካባቢዎች ግን ምንም ዓይነት ተኩስ አቁም አልነበረም። በ1914 የገና ቀን እንኳ 77 ገደማ የብሪታንያ ወታደሮች ውጊያ ላይ ተገድለዋል።
በወቅቱ ጀማሪ መኮንን የነበሩት እና በሰሜን ፈረንሳይ አርሜንቲየርስ ከተማ አቅራቢያ የተዋጉት ኮሎኔል ስኮት ሸፐርድ እንደሚናገሩት የተኩስ አቆሙ በድንገት የተጀመረ ይመስላል።
በገና ዕለት ማለዳ "የማንም ያልሆነው መሬት" በከባድ ጭጋግ ተሸፍኖ ነበር። "ጭጋጉ በጣም ጥቅጥቅ ያለ ከመሆኑ የተነሳ እጅህን እንኳ ማየት አትችልም ነበር" ሲሉ በ1968 ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውሰዋል።
በዚያ ዕለት ዕቅዳቸው የአየር ሁኔታው የፈጠረላቸውን ሽፋን በመጠቀም እየፈረሱ ያሉትን ምሽጎቻቸውን መጠገን ነበር። ነገር ግን ወታደሮቹ የአሸዋ ከረጢቶችን እየሞሉ እና የምሽጉን ጠርዝ እያስተካከሉ ሳለ በድንገት ጭጋጉ መበተን ጀመረ።
"ጭጋጉ በጣም በፍጥነት ተገለጠ። በዚያ ግንባር ላይ ጀርመኖችም ልክ እንደ እኛ በሜዳ ላይ ሆነው ያንኑ ተግባር ሲያከናውኑ በድንገት አየናቸው። ለተወሰነ ጊዜ ያህል ዝም ብለን ተያየን። ከዚያም አንድ ወይም ሁለት ወታደሮች ወደ እነሱ አመሩ። ተገናኙ፣ ተጨባበጡ፣ ሲጋራ ተለዋወጡ። ወሬ ጀመሩ። ለዚያች ቅጽበት ጦርነቱ ቆመ።"
የራይፍል ብርጌድን ይመሩ የነበሩት ጄነራል ዋልተር ኮንግሬቭ በገና ዕለት ለባለቤታቸው በጻፉት ደብዳቤ፤ የተኩስ አቁሙን "አስገራሚ ነገር" ሲሉ ገልጸውታል። የሁለቱ ተፋላሚዎች ምሽጎች እጅግ የተቀራረቡ ከመሆናቸው የተነሳ ወታደሮቹ ሰላምታ መለዋወጥ እና ወሬ መጀመር ይችሉ ነበር።
"አንድ ጀርመናዊ የአንድ ቀን ተኩስ አቁም ማድረግ እንደሚፈልጉ እና እርሱ ከምሽጉ ቢወጣ እኛም እንወጣ እንደሆነ ጮክ ብሎ ጠየቀ" ሲሉ ጄነራሉ ጽፈዋል።
"ከእኛ ወገን አንዱ በጥንቃቄ ከምሽጉ ብቅ ሲል አንድ ጀርመናዊም እንዲሁ ሲያደርግ አየ። ሁለቱም ወጡ፣ ከዚያም ሌሎቹም ተከተሉ. . .ቀኑን ሙሉ አብረው ሲዘዋወሩ፣ ሲጋራ ሲለዋወጡ እና ሲዘምሩ ዋሉ" ሲሉ የተፈጠረውን ከትበዋል።
ይህ የተኩስ አቁም መደረጉ ወታደሮቹ የወደቁ ጓዶቻቸውን አስከሬን "የማንም ካልሆነው መሬት" ላይ አንስተው ሥርዓተ ቀብር እንዲፈጽሙ ዕድል ሰጥቷቸዋል። ከጥቂት ሰዓታት በፊት እርስ በርስ ለመገዳደል ይሞክሩ የነበሩ ሰዎች ሲጋራ፣ ምግብ እና ከቤታቸው ያመጧቸውን የማስታወሻ ቁሳቁሶችን ተለዋወጡ።
በተፋላሚዎቹ ምሽጎች መካከል ባለው ባዶ ቦታ ላይ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ስለመደረጋቸውም የሚጠቁሙ መረጃዎችን አሉ። ከ33ኛው ሳክሰን ክፍለ ጦር ምክትል ሌተናንት የነበሩት ኮሎኔል ጆሃንስ ኒማን በዚህ ክስተት ውስጥ ከተሳተፉት ወታደሮች አንዱ ነበሩ።
"ድንገት አንድ የብሪታንያ ወታደር ኳስ ይዞ መጣ. . .ከዚያም የእግር ኳስ ግጥሚያ ተጀመረ። የጎል አግዳሚዎችን ምልክት ያደረግነው በባርኔጣዎቻችን ነበር። ወታደሮችም እንዲሁ አደረጉ። ብዙ ተጫወትን፤ በመጨረሻም ጀርመኖች 3 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸነፉ" ብለዋል።
ጦርነቱ በድጋሚ ተጀመረ
በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ውስጥ የገናው ተኩስ አቁም ጋር የሚመሳሰል ነገር ዳግመኛ አልተፈጠረም። በተኩስ አቁሙ እና በተስተዋለው ያልተጠበቀ ወዳጅነት የተገረሙት ወታደራዊ መሪዎች፤ ይህ ሁኔታ ወታደሮቹ ለመዋጋት ያላቸውን ፍላጎት ያዳክማል እንዲሁም ጦርነቱን ለማሸነፍ የሚደረገውን ጥረት ያሰናክላል ብለው ሰጉ።
በሁለቱም ወገኖች "ከጠላት ጋር መወዳጀትን" የሚከለክል ትዕዛዝ ወጣ፤ ትዕዛዙን የሚጥሱም በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንደሚቀጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው። ወታደሮች ወደ ምሽጋቸው የሚጠጉ የጠላት ወታደሮች ላይ እንዲተኩሱ ታዘዙ፤ ቀስ በቀስም በየግንባሮቹ ዳግም የጥይቶች ድምጽ መሰማት ጀመረ።
ጦርነቱ ወደ ቀድሞ ጭካኔው ተመለሰ፤ አስከፊነቱ እየጨመረ ሲሄድም በተፋላሚ አገራት መካከል ያለው ጥላቻ እየጠነከረ መጣ።
በቀጣዩ የገና በዓል ድንገተኛ የተኩስ አቁም እንዳይከሰት ለመከላከል እና የገና መዝሙር ሲዘመር እንዳይሰማ ለማድረግ ሲባል በበዓሉ ቀን ሆነ ተብሎ ከባድ መሳሪያዎች እንዲጠመዱ ተደረገ።
የ1914ቱ የገና ተኩስ አቁም የጦርነቱን ሂደት በመሠረታዊነት ቀይሮታል ብሎ ለመናገር እጅግ አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ፤ የታሪክ ምሁሩ ዳን ስኖው በቢቢሲ ፖድካስት እንደተናገሩት፤ ሁኔታው መከሰቱ በራሱ ተአምር የሚመስል ነገር አለው።
"ተኩስ አቁሙ በቢሮክራሲ፣ በከባድ መሳሪያዎች እና በፈንጂዎች ጦርነት ውስጥ የታየች አጭር እና አስደሳች የሰብአዊነት ብልጭታ ነበረች" ሲሉ ክስተቱን ይገልጹታል።
ድንገተኛው ክስተት፤ እንደ ኮሎኔል ስኮት ሸፐርድ ባሉ ወታደሮች ላይም ጥልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ለጥቂት ጊዜም ቢሆን፣ በተቃራኒ ወገኖች የተሰለፉ ወታደሮች አንዳቸው ሌላቸውን መገደል እንዳለበት የማይታወቅ ጠላት ሳይሆን ወደ ቤታቸው እና ወደ ወዳጆቻቸው ለመመለስ የሚናፍቁ አባቶች፣ ወንድሞች እና ልጆች መሆናቸውን መመልከት ችለዋል።
"በርካቶቹ ወታደሮች እንግሊዝኛ ይናገሩ ነበር። በአጠቃላይ ለጦርነቱ ያላቸውን ጥላቻ ገልጸዋል። በጭራሽ ጠበኞች አልነበሩም። አንዳንዶቹ ለንደን እና እንግሊዝ ሄደው እንደሚያውቁ ተናግረዋል፤ እንዲያውም እኛን በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን የሚያሳይ ፍንጭ ሰጥተዋል" ሲሉ ኮሎኔል ስኮት ሸፐርድ የነበረውን ስሜት ገልጸዋል።