ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ በእግር ኳስ ጨዋታ ላይ የነበሩ ተጫዋቾች በመብረቅ መሞታቸው ተሰማ
በሰሜናዊ ኬንያ ኪሲ በተባለች ግዛት ሁለት ተጨዋቾች በመብረቅ ከተመቱ በኃላ ህይወታቸው ማለፉን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ተጫዋቾቹን ለሞት የዳረገው መብረቅ የተከሰተው ባለፉት የእረፍት ቀናት ሲካሄድ በነበረ ጨዋታ ላይ ነው። በመብረቁ ሌሎች ሁለት ተጫዋቾች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን የድንገተኛ ህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።
የኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሃላፊዎችን ጠቅሰው የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ የመብረቅ አደጋ የተከሰተበት የእግር ኳስ ጨዋታ የወዳጅነት ግጥሚያ ነው።
ጨዋታው እየተካሄደ በነበረበት ጊዜ ዝናብ መዝነብ እንደጀመረም ተገልጿል።
የኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አከባቢያዊ ሃላፊ ኢቨንስ አካንጋ “ይህ ፈጽሞ አለመታደል ነው፣ አጅግ የሚወዱትን እግር ኳስ ሲጫወቱ ህይወታቸውን አጥዋል። እንደ ፌዴሬሽን አመራር ለሟች ቤተሰቦች የተሰማንን ሀዘን ገልጸናል” ማለታቸውን ዴሊይ ኔሽን የተባለው የኬኒያ ጋዜጣ ዘግቧል።
የእግር ኳስ አመራሩ መሰል አደጋዎችን ለመቀነስ ጨዋታዎች በሚካሄድባቸው እንደ ትምህርት ቤት ያሉ ስፍራዎች ላይ የመንግሥት ባለስልጠናት የመብረቅ መከላከያ እንዲገጥሙም አሳስበዋል።