የማላዊው ምክትል ፕሬዝዳንት በሙስና ምክንያት ለእስር ተዳረጉ

የማላዊው ምክትል ፕሬዝዳንት ሳውሎስ ቺሊማ የገንዘብ ጥቅም በመቀበል የመንግሥት ጨረታን ሰጥተዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአገሪቱ የፀረ ሙስና ተቋም አስታወቀ።

የከፍተኛ ባለሥልጣኑን መያዝ አስመልክቶ የወጣው መግለጫ እንደሚለው ግለሰቡ 280,000 ዶላር እና “ሌሎች እቃዎችን” ከአንድ የብሪታኒያ ነጋዴ ተቀብለዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ቺሊማ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ ለእስር በተዳረጉበት ክስ ላይ ግን ያሉት ነገር የለም። ነገር ግን ከሙስና ጋር የተያያዙ ስድስት ክሶች እንደቀረበባቸው ተገልጿል።

የማላዊ የፀረ ሙስና ቢሮ በምክትል ፕሬዝዳንቱ ላይ ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ክስ ባቀረበበት ጊዜ ከሥልጣናቸው እንዲነሱ መደረጉም ተነግሯል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የብሪታኒያ ዜጋ የሆነው ነጋዴ ዙኔት ሳታር ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በቁጥጥር ስር ውሎ በዋስ ከእስር ወጥቷል።

ግለሰቡ ከማላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ፖለቲከኞች ጋር ያለውን ግንኙነት በመጠቀም፣ ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ምርት እና አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚያስችሉ ጨረታዎችን ወስዷል በሚል ክስ ቀርቦበታል።

በስምምነቶቹም ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን፣ የምግብ ምርቶች እና ከፍተኛ ኃይል ያለው ውሃ በመርጨት የአድማ መበተኛዎችን ማቅረብን የተመለከቱ እንደሆነ ፋይናንሺያል ታይምስ ባለፈው ግንቦት ወር ዘግቦ ነበር።

ሳተር ግን ምንም አይነት ጥፋቶች አልፈጸምኩም በሚል የቀረቡበትን ክሶች ያስተባብላል።

አሁን በሙስና በቁጥጥር ስር የዋሉት ቺሊማ በሥልጣን ላይ ካሉት ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻክዌራ ጋር በመሆን ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገው ምርጫ ነበር ወደ ሥልጣን የመጡት።

በምርጫው ወቅት ፕሬዝዳንቱ እና ምክትላቸው የምርጫ ቅስቀሳ ያደረጉት ፀረ ሙስና ዘመቻ እንደሚያካሂዱ በመግለጽ፣ በመንግሥት ውስጥ ያለውን የተበላሸ አሰራር በማብቃት በዓለም ደሃ ከሆኑት አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ማላዊ ውስጥ ያለውን ድህነት ለመቅረፍ ቃል ገብተው ነበር።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሙስና በአገር እና በሕዝብ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት በሚያደርጓቸው ጠንካራ ንግግሮች ይታወቃሉ።