“በተከለከለ የእርግዝና መከላከያ ምክንያት ጸነስኩ”

ነፍሰ ጡር ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሱዛን ዋማይታ ከዓመት በፊት መታመም ስትጀምር ከጥቂት ወራት በፊት የጀመረችው የእርግዝና መከላከያ እንክብል የሚያስከትለው የጎንዮሽ ችግር እንደሆነ ገምታ ነበር ። ነገር ግን ያልጠበቀችው ጉዳይ ተከሰተና የስምንት ሳምንት ነፍሰጡር መሆኗን ተረዳች።

የ32 ዓመቷ ሱዛን በአሁኑ ወቅት የሦስት ልጆች እናት ናት። ሱዛን ሰኔ 2014 አካበባቢ መውሰድ የጀመረችው የእርግዝና መከላከያ በኬንያ መታገዱን አታውቅም ነበር።

በጎዳናዎች ላይ ወይም በተለምዶ ስሙ “ሶፊያ” የሚባለው የእርግዝና መከላከያ እንክብል የሚመረተው በቻይና ነው። ምርቱ በማሸጊያ ላይ ስለአመራረቱም ሆነ ስለያዘው ንጥረ ነገር የተጻፈው ከቻይና ቋንቋዎች በአንዱ ነው።

በማሸጊያው ላይ ከተጻፉት መረጃዎች መካከል መድኃኒቱ የያዘው ንጥረ ነገር ሲሆን፣ ይህም ‘ሌቮኖርጀስትሬል ፋስት ኤስትራዲዮል ታብሌት’ እንደሆነ ተጠቅሷል።

እንክብል ለረዥም ጊዜ የሚያገለግል የእርግዝና መከላከያ እንደሆነ የሚጠቅስ ሲሆን፣ በተጨማሪም ‘ዚዝሁ’ በተባለ የመድኃኒት አምራችም እንደተመረተ ይጠቅሳል ።

የኬንያ ባለሥልጣናት የመድኃኒቱን ሽያጭ ያገዱት ከ10 ዓመት በፊት ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቱ ሌቮንኦርጀስትሬል የተባለው ንጥረ ነገር ከሚመከረው ከ40 እጥፍ በላይ የያዘ በመሆኑ ነው።

ሌቮንኦርጀስትሬል በበርካታ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል የሆርሞን መድኃኒት ነው።

የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስለ ግኝቶቹ ሙሉ የላብራቶሪ ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ አላደረገም። ነገር ግን የእርግዝና መከላከያ እንክብሎቹ ባለመስራታቸው የተጸነሱ ህጻናት ታዳጊ እድሜ ላይ መሆናቸውን አሳውቋል።

ራስ ምታት እና ማቅለሽለሽ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“በእንክብሎቹ ላይ እገዳ መጣሉን አላውቅም ነበር። በርካታ ጓደኞቼ እየወሰዱት ነበር እናም ምንም የጎንዮሽ ጉዳት አልታየባቸውም” ስትል ሱዛን ለቢቢሲ ተናግራለች።

ልክ እንደሌሎች ኬንያውያን ሴቶች፣ የእርግዝና መከላከያ እንክብሉን በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛቷ እና በወር አንድ ጊዜ ብቻ መውሰዷ ምቾት ሰጥቷት ነበር።

ብዙ የመድኃኒት አቅራቢያዎች ‘ሶፊያ’ የተባለውን የእርግዝና መከላከያ እንክብል በጅምላ የማይሸጡ ሲሆን ኬንያውያን ሴቶች በየወሩ መግዛት ይጠበቅባቸዋል።

እያንዳንዱ የእርግዝና መከላከያ እንክብል ከ300 እስከ 400 የኬንያ ሽልንግ ያወጣል፤ ይህም ማለት 2.5 ዶላር የሚገመት ነው።

በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ፕሮግራሞች በየቀኑ የሚወሰዱ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ናቸው።

የአንድ ወር የእርግዝና መከላከያ እንክብሎችን ከመንግሥት ሆስፒታል ለመግዛት ወደ 1.70 ዶላር የሚያስወጣ ሲሆን፣ ነገር ግን ሁልጊዜም አይገኝም። በዚህም ምክንያት በከፍተኛ ዋጋ ከግል የመድኃኒት መደብሮች መግዛት ይገደዳሉ።

በዚህም ምክንያት በርካቶች ለሦስት ወር ያህል በክንድ የሚቀበረውን የእርግዝና መከላከያ ይመርጣሉ። እነዚህ መከላከያዎች በመንግሥት የጤና ተቋማት አምስት ዶላር ሲያስከፍሉ፣ በተጨማሪም ለበርካታ ዓመታት የሚቆዩ ሌሎች መከላከያዎች እስከ 9 ዶላር በማውጣት እንደተሻለ አማራጭ ያዩታል።

ኮንዶም በሕዝብ መሥሪያ ቤቶች እና መጸዳጃ ቤቶች ውስጥ በነፃ የሚታደል ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ግን የሚያልቅበት ወቅት አለ። ሆኖም ኮንዶም በመደብሮች መሸመት ይቻላል።

“የሆርሞን ንጥረ ነገር የሌለው በብልት ውስጥ የሚገባ የኮፐር የእርግዝና መከላከያ ጀርባዬን አሳመመኝ። እናም እሱን አውጥቼ እንክብል ለመውሰድ ወሰንኩ” በማለት ሱዛን ለቢቢሲ ተናግራለች።

‘ሶፊያ’ የተሰኘውን የእርግዝና መከላከያ እንክብል እንድትወስድ ያማከሯት ጓደኞቿ ምንም አይነት ክብደት ባይጨምሩም፣ እሷ ግን እንክብሎቹን መውሰድ ከጀመረች በኋላ ክብደቷ ጨመረ።

ከመጀመሪያው ስለ እንክብሎቹ ጥሩ ስሜት ባይሰማትም ሰውነቷ ከአዲሱ መድኃኒት ጋር ለመላመድ ጊዜ እንደሚወስድ በማሰብ እንክብሎቹን መውሰድ ቀጠለች።

"ራስ ምታት እና ማቅለሽለሽ ጀመረኝ። እንክብሉን መውሰድ በጀመርኩበት የመጀመሪያው ወር የወር አበባዬ መምጣት አቆመ” ትላለች ሱዛን።

ነገር ግን ብዙም አላስጨነቃትም ነበር። በሚቀጥለው ወርም የወር አበባዋ መጣ። በሦስተኛው ወር እንደገና የወር አበባዋ ሲቀር ነበር ጭንቀቷ የጀመረው።

 ሶፊያ የተባለው የእርግዝና መከላከያ

የፎቶው ባለመብት, PPB

ከዚያም ባለቤቷ ስለ እንክብሎቹ ማጠያየቅና መመርመር ጀመረ እናም በዚያን ወቅት ነው መታገዱን የተረዳው።

“የተከለከለ እንክብል በመውሰዴ መደናጥ ጀመርን፣ እናም ነፍሰ ጡር መሆኔን ስረዳም በጽንሱ ላይ ሊያመጣው ስለሚችለው አሉታዊ ተጽእኖ እጨነቅ ነበር” ትላለች።

በአሁኑ ወቅት ጤናማ የሦስት ወር ጨቅላ ልጅ አላቸው። ነገር ግን ጥንዶቹ በመረጃ እጦት እና ልጃቸው እያደገች ስትሄድ ሊመጡ ይችላሉ ብለው የሚያስቧቸው ችግሮች ያበሳጫቸዋል።

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት ዘመናዊ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎች ከሚያስፈልጋቸው ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ ሴቶች መካከል 50 በመቶው ብቻ ናቸው እያገኙ ያሉት።

በኬንያ፣ ስለ እርግዝና መከላከያ በግልፅ መነገጋገር እንደ ነውር ነው የሚታየው።

ይህም በአባታዊ (ፓትሪያርኪ) ሥርዓት ምክንያት ከባህሉ እና ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነው።

አንዳንድ ወንዶች ባለቤቶቻቸው የእርግዝና መከላከያ እንክብል እንዲጠቀሙ አይፈቅዱም። በተጨማሪም አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎችም ይቃወማሉ።

በምሥራቅ ኬንያ የሚገኘው የካቮኖኪያ እምነት ሁሉንም ዘመናዊ ህክምናዎች አይቀበልም፤ ለሁሉም ነገር መልሱ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያዘው መስረት ጸሎት ነው ይላል።

የሕዝብ እና እና ልማት ኤክስፐርት ዶክተር ጆሴፊን ኪባሩ፣ የዘመናዊ የቤተሰብ ምጣኔ ዘዴዎች ተቀባይነትን ለማግኘት ወደ ሕዝቡ ወርዶ መስራቱ የተሻለ እንደሆነ ይመክራሉ።

“የማኅበረሰብ ጤና በጎ ፈቃደኞች መረጃ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም አንዲት ሴት በጤና ማዕከላት ከተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች ይልቅ ጎረቤቷን እና ጓደኛዋን ነው የምታምነው” ይላሉ።

የማህፀን ሐኪም የሆኑት ብሪጂድ ሞንዳ እንደሚናገሩት ሴቶች ለእነሱ የሚሆናቸውን የተሻለ የቤተሰብ ምጣኔ ለማወቅ የጤና ባለሙያዎች እንዲያማክሩ ምክራቸውን ይለግሳሉ።

አንዳንድ ሴቶችም በተለይም በገጠሪቷ ኬንያ የእርግዝና መከላከያ ወጥ የሆነ አቅርቦት ባለመኖሩ የተለያዩ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን እንዲቀላቀሉ ተገድደዋል።

ሆኖም ‘ሶፊያ’ የተሰኘው እንክብል እገዳ ቢጣልበትም በቀላሉ ይገኛል። ሴቶች መታገዱን አለማወቃቸው በሕብረተሰብ ጤና ላይ ያለውን ክፍተት የሚያሳይ ነው ይላሉ ዶክተር ጆሴፊን።

‘ሶፊያ’ አሁንም ለታመኑ ደንበኞች ይሸጣል

ፋርማሲስቶች ‘ሶፊያ’ እንደታገደ ያውቃሉ። የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለፈው ወር ሌላ ማስጠንቀቂያ ቢያወጣም አሁንም በርካቶች እንክብሉን ስለሚፈልጉት ይሸጣሉ።

ሆኖም በመደርደሪያዎች ላይ የማያስቀምጧቸው ሲሆን ነገር ግን በየወሩ ለሚመጡ ታማኝ ደንበኞች በድብቅ ይሸጡታል።

ቢቢሲ ‘ሶፊያ’ የእርግዝና መከላከያ እንክብል ለማግኘት የናይሮቢ መድኃኒት መደብሮችን ቢጎበኝም እንደማይሸጥ ተነግሮናል።

ሆኖም ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ሻጭ እንክብሉ በመደርደሪያዎች ላይ እንደማይሰቀልና ፋርማሲዎችም ከጎረቤት አገር ካመጡ አቅራቢዎች መግዛት መቻላቸውን አስረድተው፤ አለ ብለውናል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ፋርማሲዎችን የሚቆጣጠረው ባለሥልጣን በኡጋንዳ ድንበር ላይ የ‘ሶፊያን’ ጭነት መያዙን ለኬንያ ስታንዳርድ ጋዜጣ ተናግሯል።

ሱዛን ራሷ እነዚህን እንክብሎች የገዛችው ከእነዚህ አቅራቢዎች በጅምላ ከምታገኝ ጓደኛዋ እንደሆነ ተናግራለች።

ይህች ጓደኛዋ እንክብሉ እንደተከለከለም ታውቅ እንደነበር ለቢቢሲ አስረድታለች።

የእሷ እርግዝናም ሆነ በተለያዩ ፌስቡክ ገጾች የሚለጠፉ ቅሬታዎች እነዚህን ሽያጮች አላገዷቸውም ትላለች። በእነዚህ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በተካሄዱ ውይይቶች በርካታ ሴቶች እርግዝናን እንዳልተከላከለላቸውና ነፍሰ ጡሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።